ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 2013፡ ቦርዱ ለ54 የምርጫ ክልሎች የታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ጉድለቶች አለባቸው አለ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ54 የምርጫ ክልሎች በታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ የተለያዩ ጉድለቶችን ማግኘቱን አስታወቀ።
ቦርዱ ረቡዕ ሰኔ 2/2013 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ባደረገበት ወቅት ይህንን ማሳወቁን በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
የድምፅ መስጫ ወረቀት ህትመትን አስመልክቶ ያጋጠሙ ችግሮችን ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሪፖርት አቅርቧል።
የዕጩዎችን ቁጥር መሰረት አድርጎ በተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ወቅት ፓርቲዎች የዕጩዎች ቁጥር ላይ ባቀረቡት አቤቱታ፣ በድምፅ መስጫ ወረቀት እና በውጤት ማሳወቂያ ፎርሞች ላይ የማስታረቅ ሥራ ሲሰራ በድምፅ መስጫ ወረቀቶቹ ላይ ጉድለቶች መገኘታቸውን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ መግለፃቸው ተጠቅሷል።
ቦርዱ ባደረገው ማጣራት ጉድለት የተገኘባቸው የድምፅ መስጫ ወረቆች ድጋሚ ህትመት ያስፈልጋቸዋልም ተብሏል።
ጉድለት የተገኘባቸው የምርጫ ክልሎች በአፋር ስድስት፣ በአማራ 11፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 2፣ በጋምቤላ 3፣ በኦሮሚያ 2፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች 15፣ በሶማሌ 14 እና በድሬዳዋ 1 ድጋሚ ህትመት የሚያስፈልጋቸው ምርጫ ክልሎች መሆናቸው ተመልክቷል።
በዚሁ ምክክር ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ለተፈጠረው ችግር በቦርዱ የተወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን አቅርበዋል።
ጉድለቶች በተፈጠሩባቸው ምርጫ ክልሎች የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን አትሞ ለማድረስ የሚኖረው ችግርና የሚያመጣውን የእሸጋ እና የስርጭት ተፅእኖንም በተመለከተ ብርቱካን አብራርተዋል።
በእነዚህ 54 የምርጫ ክልሎች የድምጭ መስጫ ወረቀቶችን ሰኔ 14 ለሚደረገው ምርጫ ለማድረስ የሚደረጉ ጥረቶችንም በተመለከተ ፓርቲዎች ሃሳብ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል።
ፓርቲዎቹ በበኩላቸው የድጋሚ ህትመቱ በአገር ውስጥ ቢደረግ እንዲሁም ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ምርጫ የማይደረግባቸው የምርጫ ክልሎች ጋር አብረው ድምፅ እንዲሰጡ ቢደረግስ የሚሉ አማራጭ ሃሳብ ማቅረባቸውም ተገልጿል።
ይህንንም መሰረት በማድረግ ቦርዱ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ላይ ያጋጠመውን የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ጉድለት ችግር ለመፍታት በመጀመሪያ ደረጃ የድምፅ መስጫ ወረቀቶቹን አገር ውስጥ ማሳተም ሲሆን በሌላ አማራጭ ደግሞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ድምፅ ከማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ጋር አብሮ ማካሄድ የሚሉትን አቅርቧል።
በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ምርጫ የማይካሄድባቸው ቦታዎችን ዝርዝር ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በእነዚህ ስፍራዎች ምርጫ የማይካሄደው በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባለመጀመሩ፣ የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ በመቋረጡና የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበ መሆኑን ቦርዱ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ ጉልህ የአሰራር ችግር በማየቱ ማጣራት እንዲካሄድ የወሰነባቸው ቦታዎችም እንዲሁ ምርጫው እንደማይከናወን አስታውቋል።
ግንቦት 28/2013 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ብሔራዊ ምርጫ፣ የመራጮች ምዝገባ እና ሌሎች ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠነቃቀቸው የተነሳ ምርጫው ለሁለት ሳምንታት እንዲገፋ ሆኖ ሰኔ 14 እንዲካሄድ ተወስኗል።
ኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ የምታካሂደው ምርጫ መካሄድ የነበረበት ባለፈው ዓመት ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም መደረጉ የሚታወስ ነው።