በካናዳ በጥላቻ በተነሳሳ ጥቃት የአንድ ሙስሊም ቤተሰብ አባላት ተገደሉ

በካናዳ በአንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ቤተሰብ ላይ ባነጣጠረ ጥቃት አራት አባላት በመኪና ተገጭተው ተገደሉ።

ቤተሰቡ የተገደለው ሆን ብሎ በተቀነባበረ ጥቃት እንደሆነ ፖሊስ አጋልጧል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ኦንታሪዮ ግዛት ሲሆን የቤተሰቡ አንደኛው ልጅ ብቻ ሊተርፍ ችሏል።

የዘጠኝ አመቱ ታዳጊ በሆስፒታል ህክምና እየተደረገለትም ይገኛል።

በዚህ ጥቃት የ74ና 44 አመት ሁለት ሴቶች፣ አንድ የ46 አመት ወንድና የ15 አመት ታዳጊ ህይወታቸው ጠፍቷል። በቤተሰቡ ጥያቄ መሰረት ስማቸው አይገለፅም ተብሏል።

ይህንን የተቀነባበረ ግድያን በመፈፀም አንድ የ20 አመት ካናዳዊ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በአራት ሰዎች ግድያ ወንጀልና በታዳጊው ደግሞ በግድያ ሙከራ ክስ ቀርቦበታል።

ጥቃቱን የፈፀመው ናትናኤል ቬልትማን የተባለ ግለሰብ ሲሆን ቤተሰቡን ከገደለበት ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ባለው የገበያ ማዕከልም ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።

ይህ ግለሰብ በወቅቱም የጥይት መከላከያ ጃኬት አድርጎ ነበር ተብሏል።

ግለሰቡ ከገደላቸው የቤተሰብ አባላት ጋር ምንም አይነት ትውውቅ እንደሌላቸውም ፖሊስ አስታውቋል።

ግድያው የእስልምና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው በጥላቻ ተነሳስቶ እንደሆነ ተገልጿል።

ነገር ግን ግለሰቡ ከሌሎች የጥላቻ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ይኑረው የታወቀ ነገር እንደሌለ ፖሊስ ገልጿል።

በካናዳ በኩቤክ ከተማ ከአራት አመት በፊት በመስጊድ ላይ ከተገደሉት ስድስት ሙስሊሞች ቀጥሎ የከፋ ጥቃትም ነው ተብሏል።

"ቤተሰቡ ሙስሊሞች ስለሆኑ ነው የተገደሉት ብለን እናምናለን" በማለት የፖሊስ ኃላፊው ፖል ዌይት ሰኞ እለት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

ኃላፊው ይህ በጥላቻ ተነሳስቶ የተፈፀመ ግድያ ከመሆኑ አንፃር ግለሰቡን በሽብር ለመጠየቅ ፖሊስ እየመረመረ ነው ብለዋል።

ግድያው በርካቶችን ያስደነገጠና ያሳዘነ ሲሆን በሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ ጅምላ ግድያና በማይነገር ጥላቻ የተሞላ በማለት የግዛቲቱ ከንቲባ ኤድ ሆልደር አውግዘውታል።

ከንቲባው በግዛቲቱ ለሶስት ቀናት ያህልም የኃዘን ቀን በማስመልከት ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዘዋል።