ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማሊ መፈንቅለ መንግሥት መሪ የሽግግር አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ተሰየሙ
የማሊ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታን የሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰየመ።
ኮሎኔል ጎይታ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለተኛውን መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣን ከያዙ ከሁለት ቀናት በኋላ ባለፈው ረቡዕ የማሊ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝደንት አድርገው እራሳቸውን ሾመዋል።
በምርጫ ሥልጣን ይዘው የነበሩትን ፕሬዝዳንት ቡባካር ኬይታን ከመንበራቸው ባለፈው ነሐሴ ወር ያስወገዱት ወታደራዊ መሪው፤ የፕሬዝደንትነት ቦታውን እንዲይዙ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ከመጀመሪያው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ማሊን ወደ ሲቪል መንግሥት የሚመልሰውን አስተዳደር በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የነበሩት ባህ ዳዋ እና ሞክታር ኦኔ በሁለተኛው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ተይዘው ታስረዋል።
ኮሎኔል ጎይታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል እንዲታሰሩ አድርገዋል።
ነገር ግን ሁለቱ መሪዎች ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ ሐሙስ ዕለት ከእስር ተለቀዋል።
አርብ እለት በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ኮሎኔል ጎይታ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው "የአገሪቱን የሽግግር ሂደት አስከፍጻሜው እንዲመሩ" ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አመልክቷል።
የባለፈው ዓመት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የሽግግሩ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
መፈንቅለ መንግሥቱ የተካሄደው ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአገሪቱ ጦር ሠራዊትን ሁለት ከፍተኛ መኮንኖችን ከሥልጣናቸው በማንሳት በሌላ ከተተኩ ከሰዓታት በኋላ ነበር።
ይህን ተከትሎ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሹም ሽር በማድረጉ ኮሎኔል ጎይታ ቅሬታ አድሮበት ነው እርምጃውን የወሰደው ተብሏል።
አርብ እለት ኮሎኔሉ ሥልጣን በኃይል ከያዙ በኋላ ለሕዝቡ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው "በጦር ሠራዊቱና በጸጥታ ኃይሉ መካከል ሊከሰት ከሚችለው ሥርዓት አልበኝነት ይልቅ መተባበርን መርጣናል" ሲሉ ለመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያታቸውን ጠቅሰዋል።
ኮሎኔል ጎይታ ጨምረውም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾምና ምርጫ በሚቀጥለው ዓመት በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የወታደራዊ ቡድኑ መሪ ኮሎኔል ጎይታ ባለፈው ዓመት የመሩትን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የ18 ወራት የሽግግር ምክር ቤት ተሰይሞ ነበር።
ኮሎኔል ጎይታ የአገሪቱን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ባቦካር ኬይታን ከሥልጣን በኃይል ሲያስወግዱ የአገሪቱ በርካታ የአገሪቱ ሕዝብ በደስታ አደባባይ ወጥቶ ነበር።
ሆኖም ባለፉት 9 ወራት የታየው አዝጋሚ የለውጥ ሂደት ዜጎችን ቅሬታ ውስጥ ከቷቸው ነበር። የሠራተኛው ማኅበር የጠራው የሥራ ማቆም አድማም የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ማሽመድመድ ይዞ ነበር።
ባለፈው ዓመትም መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ማኅበር የሆነው ኢኮዋስ በዚያች አገር ማዕቀብ እጥላለሁ በማለቱ ነበር የሽግግር መንግሥት መመሥረት የተቻለው።
በአገሪቱ እጇ ረዥም ነው የምትባለውና ማሊን ለዓመታት በቅኝ የገዛችው ፈረንሳይ፤ የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ እንዲጥል አስደርጋለሁ ስትል ዝታለች።
የባሕር በር አልባዋ ማሊ በአፍሪካ ድሃ አገራት ተርታ የምትመደብ ሲሆን የአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች ልማት የማያውቃቸው ናቸው።