ባራክ ኦባማ የእንግሊዙ እና የማንቸስተር ዩናይትዱን አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድን አወደሱ

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንና የማንቸስተር ዩናይትዱ አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድ በጸረ ድህነት ዘመቻው ከባራክ ኦባማ አድናቆት ተቸረው።

በዙም አማካይነት በኢንተርኔት በተካሄደው ውይይት ላይ ራሽፎርድን "እኔ በእሱ ዕድሜ ከነበርኩበት ቀድሞ የሄደ" ሲሉ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት አወድሰውታል።

ማንቸስተር ከሚገኘው መኖሪያው ማዕድ ቤት ሆኖ በውይይቱ የተካፈለው የ23 ዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች ከኦባማ ጋር መነጋገሩን "የማይታመን" ነው ብሏል።

ኦባማ እንደ ራሽፎርድ ያሉና "በማኅበረሰባቸው አዎንታዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ" የሆኑ ወጣቶችን ደግፈዋል።

ፔንግዊን በተባለው አሳታሚ በተዘጋጀው ውይይት ላይ በቀድሞው ፕሬዝዳንት 'ማስታወሻ' ላይ በመወያየት፤ በእናት እጅ ብቻ ስለማደግ እና በማኅበረሰብ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስለመሳተፍ ያሉት ልምዶች ተነስተዋል።

'መከራ እና እንቅፋቶች'

"በአነስተኛ ደረጃ አዎንታዊ ነገር ብታደርጉ እንኳ ለውጥ እያመጣ ነው። ከጊዜ በኋላም አዎንታዊ ነገሮችን የሚያደርጉ ሰዎች መጨመር ካለፈው ትውልድ ትንሽ እንድንሻል ያደርገናል" ብለዋል ኦባማ።

በተጨማሪም ወጣት በነበሩበት ጊዜ ፕሬዝዳንት የመሆን ተስፋ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል። "የበለጠ ችሎታ ቢኖረኝ ኖሮ እንደ ማርከስ ስፖርተኛ መሆን እመርጥ ነበር" ብለዋል ኦባማ።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለማርከስ ራሽፎርድ "ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ብዙውን ጊዜ የሚጀምሩት በወጣቶች ነው" ሲሉ ነግረውታል።

የእግር ኳስ ተጫዋቹ ግን ብዙውን ጊዜ "ድምጻቸው ምን ያህል ኃይል እንዳለው አይረዱም" ብሏል።

የህጻናትን ረሃብ ለመከላከል ከፍተኛ ዘመቻ የሚያካሂደው የማንችስተር ዩናይትዱ አጥቂ "ፕሬዝዳንት ኦባማ ሲናገሩ ማድረግ የምትፈልገው ማዳመጥ ብቻ ነው" ሲል ተናግሯል።

"ማለቴ ማንቸስተር ውስጥ በሚገኘው ማዕድ ቤቴ ተቀምጬ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር እየተነጋገርኩ ነው። ግን ወዲያውኑ እንድረጋጋ አደረገኝ። በጣም የማይታመን ነው አይደል?" ብሏል።

"ለአሁኑ ማንነታችን መፈጠር ልጆች እያለን ያጋጠሙንን ልምዶች ምን ያህል እንደሚመሳሰሉ የተረዳሁት ብዙም ሳይቆይ ነበር" ሲል ገልጿል።

የምግብ ድህነት

በዚህ ሳምንት ቡድኑ ማንቸስተር ዩናይትድ በዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ መሸነፉን ተከትሎ ራሽፎርድ "የዘረኝነት ጥቃቶች" በማኅበራዊ የትስስር ገጾች እንደገጠሙት ሲገልጽ ቡድኑ ደግሞ "አሳፋሪ የዘረኝነት ጥቃት" ብሎታል።

ሁለቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች በመጽሐፍትን እና በንባብ አስፈላጊነት ዙሪያ ተወያይተዋል።

እናታቸው "የንባብ ፍቅር እንደዘሩባቸው" የተናገሩት ባራክ ኦባማ ሲሆኑ ራሽፎርድ በበኩሉ መጻሕፍት የራሱን ሃሳብ የመከተል ነፃነት እንደሰጠው ተናግሯል።

"ሰው ይህን አድርግ ያንን አድርግ ከሚለኝ ይልቅ መጽሐፍት በራሴ መንገድ እንድፈጽም ረድቶኛል" ብሏል ራሽፎርድ።

ችግረኛ ወጣቶችን የንባብ ችሎታን ለማሻሻል የእግር ኳስ ተጫዋቹ ባለፈው ዓመት የራሱን የልጆች መጽሐፍ ክበብ አቋቁሟል።

ራሽፎርድ ከቴሌቪዥን የምግብ አብሳዩ ቶም ኬሪጅዝ ጋር በመሆን የምግብ ድህነትን የዘመቻው አካል በማድረግ የተመጣጠነ እና በቀላሉ የሚገኝ ጤናማ ምግቦች አዘገጃጀት ዙሪያ ምክሮችንም ይሰጣል።

ራሽፎርድ በልጅነቱ ስለመራብ እና በልጅነት በነጻ የትምህርት ቤት ምገባ ላይ ጥገኛ ስለመሆን ተናግሯል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ትምህርት ቤቶች በነጻ ምግባቸው እንዲቀጥሉ ሃሳብ በማቅረብ ከመንግሥት ጋር የተሳካ ጥረት አድርጓል።

የቀድሞው የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ዶሚኒክ ኩሚንግስ ለተመረጡት የፓርላማ አባላት እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከራሽፎርድ ጋር ጠብ አትምረጡ" የሚል ምክር እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።