ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡በኦሃዮ ግዛት የኮቪድ ክትባት ሎቶሪ አሸናፊዋ 1 ሚሊዮን ዶላር ተሸለመች
የአሜሪካ ግዛት ኦሃዮ ለኮቪድ ተከታቢዋ 1 ሚሊዮን ዶላር ሸለመች፡፡
ኦሃዮ ይህን ያህል ገንዘብ ለኮቪድ ተከታቢ የሸለመችው ነዋሪዎቿ ክትባቱን እንዲወስዱ ለማበረታታት ባዘጋጀችው የሎቶሪ መርሐ ግብር ነው፡፡
ኦሃዮ ይህ የኮቪድ ሎቶሪ የመጀመርያ እንጂ የመጨረሻ እንደማይሆን ቃል ገብታለች፡፡
አሸናፊዋ አቤጌል በጀነስኪ የምትባል ሲሆን ከሲልቨርስተን፣ ሲንሲናቲ ሰፈር አንድ ሚሊዮን ዶላሩን ተረክባለች፡፡
በፍጹም አሸናፊ እሆናለሁ ብላ ያልጠበቀችው አቢጌይል ለእናቷ ሊዛ በመደወል ደስታ የምታደርገው እንዳሳጣት ተናግራለች፡፡
ክትባቱን የወሰደችውም በጭራሽ ሎቶሪ የማሸነፍ ዕድልን አስባ እንዳልሆነ ተናግራለች፡፡
በሌላ የሎተሪ መርሐግብር አዳጊ ጆሴፍ ካስቴሎ ከዳይተን አካባቢ የመጀመርያውን የኮቪድ ስኮላርሺፕ አሸንፏል፡፡
በዚህ መርሐግብር የታቀፉ ወጣቶች ክትባት በመውሰዳቸው የኮሌጅ ስኮላርሺፕ የማሸነፍ ዕጣ ውስጥ ይገባሉ፡፡
ይህ የኮቪድ ሎቶሪ የተጀመረው የኮቪድ ክትባትን ለማበረታታት ነው፡፡
ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ለሌሎች አራት ሳምንታት ሎቶሪው እንደሚወጣ የተገለጸ ሲሆን በአራቱም ሳምንታት አራት የተለያዩ ዕድለኞች እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ዶላር አሸናፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃሉ፡፡
ሌሎች አራት አዳጊዎች ደግሞ የኮሌጅ ስኮላርሺፕ አሸናፊ ይሆናሉ፡፡
በዚህ ሎቶሪ ለመታቀፍ 2.7 ሚሊዮን ነዋሪዎች ክትባት ወስደው ተመዝግበዋል፡፡
መቶ ሺህ አዳጊዎች ደግሞ የአራት ዓመታት ነጻ የትምህርት ዕድል ለማግኘት በእጣ መርሐግብር ተካተዋል፡፡
ሪፐብሊካኑ የኦሃዮ ገዥ ማይክ ድዋይን ይህን ሎቶሪ ያስጀመሩት በግንቦት 12 ነበር፡፡
የሎቶሪው መርሐግብር መጀመር በርካታ ዜጎች የኮቪድ ክትባት እንዲወስዱ እንዳበረታታ የገዥው ቢሮ በአሐዝ አስደግፎ ይፋ አድርጓል፡፡
የባይደን አስተዳደር የሎቶሪውን ሐሳብ ያደነቀ ሲሆን አንዳንድ የሕዝብ እንደራሴዎች ግን አላስፈላጊ የገንዘብ ብክነት ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡
ይህ የኮቪድ ሎቶሪ ሐሳብ አሁን ከኦሃዮ ሌላ በኒውዮርክ፣ በሜሪላንድ፣ በኦሪገን እና ኮሎራዶ እንዲጀመር ሆኗል፡፡