በፈረንሳይ ሲኒማዎች ላይ የሲጃራ ጭስ ለምን ያለቅጥ ይንቦለቦላል?

ሰፊ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የፈረንሳይ ፊልም ኢንዱስትሪ በሲጃራ ጭስ የታፈነ ይመስላል።

የጸረ ትምባሆ አቀንቃኞች ይህ ሁኔታ ይከነክናቸዋል። አንዳንድ ጊዜም ያስቆጣቸዋል።

እውነት አላቸው።

በምድራችን ላይ ሲጃራ በፈረንሳይ ሲኒማ የሚታየውን ያህል በየትኛውም ዓለም አይታይም። ሆሊውድንም ቦሊውድንም ጨምሮ።

በቁጥር እናስደግፈው?

በአማካይ በማንኛውም የፈረንሳይ ሲኒማ ውስጥ የማጨስ ትዕይንት 2 ደቂቃ ከ6 ሰኮንዶች ይይዛል። ይህ አማካይ አሐዝ ነው።

ይህ ማለት ስድስት ራሳቸውን የቻሉ ማስታወቂያዎች የሚሄድበት ሰዓት ማለት ነው። በሌላ አነጋገር የፈረንሳይ ሲኒማ በጭስ ተደብቆ ያለ ነው የሚመስለው።

የፈረንሳይ ጸረ ካንሰር ማኅበር ነው እዚህ ስሌት ላይ ደምሮና ቀንሶ የደረሰበት።

ብቻ ምን አለፋችሁ ትምባሆ ለፈረንሳይ ሲኒማ ደምና አጥንት ሆኗል ይላሉ አንድ የማኅበሩ ባልደረባ።

ይህ የሲጃራ ትዕይንቶች ድግግሞሽ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ነው። ለምሳሌ በቀጥታ ተዋንያን ሲያጨሱ መታየት፣ ወይም በሲጃራ ዙርያ ሲወያዩ መስማት፣ ወይም በሌላ።

አደጋው ሥነ ልቦናዊ ነው።

በሁሉም ሲኒማዎች ቅንጡና ዘናጭ አጫሽ ተዋንያን በቄንጥ ትምባሆ ሲያንበለብሉ የሚያዩ ሰዎች ቀስ በቀስ ነገሩን የዝመና መገለጫ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ።

የቀድሞ የፈረንሳይ ሲኒማ ሴት ከዋክብት የነበሩት ጂን ሞሪ እና ብሪጊት ባርዶት ሲጃራቸውን በቄንጥ ሲያጨሱ ማየት ለዓመታት የቀጠለ ከትዝታ የማይጠፋ ምሥል ነው።

ከ2015 እስከ 2019 ብቻ በተሠሩ ፊልሞች ላይ በተሠራ አንድ መደበኛ ጥናት 150 ፊልሞች ላይ በቄንጥ የማጤስ ትዕይንት ይታያል።

ይህ ታዲያ ማጨስን ብቻ ሳይሆን ትንባሆን የሚያጅቡ ቁሳቁሶች ለምሳሌ እንደ አሽትሬይና መለኮሻ ላይተርን ሊያካትት ይችላል።

ለምሳሌ ተዋናዮች ስለ ሲጃራ በአንድም ሆነ በሌላ አመጻድቀው ሲያወሩ የሚያሳዩ ትዕይንቶችን የሚጨምር ነው።

ለመሆኑ ተመልካቾች የሲጃራ ትዕይንቶችን ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል?

አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናት እንዳመለከተው በነዚህ ፊልሞች ላይ 60 ከመቶ የሚሆኑ ተመልካቾች በትዕይንቱ እንደተማረኩ አምነዋል።

በፈረንሳይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲጃራ አጫሽ ቀንሷል። ያም ሆኖ ሲጃራና ሲጃራ ማጨስ በሲኒማዎች ውስጥ አሁንም እንደ ትኩስ ፋሽን እየተንሰራፋ ነው።

በፈረንሳይ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን ዜጎች በላይ ማጨስ እንዳቆሙ በቅርብ ጊዜ ተዘግቦ ነበር።

ሲኒማው ግን ይህን አያንጸባርቅም።

አንዳንድ ጊዜ ፊልሞች መሬት ላይ ካለው እውነታም በላይ ሲጃራና ማጨስን በልዩ ሁኔታ ሲያዳንቁት መታየቱ አስገራሚ የሆነውም ለዚሁ ነው።

"ይህ ሁኔታ ማጨስን ጤናማ አድርገው ሰዎች እንዲረዱት የሚያደርግ ነው" ይላሉ የማኅበሩ ባልደረባ።

አሁን የጸረ ትንባሆና የጸረ ካንሰር ማኅበራት እየጠየቁ ያሉት የፈረንሳይ መንግሥት የሲጃራ ትዕይንት ያለቅጥ የሚያሳዩ ሲኒማዎችን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አደብ እንዲያሲዛቸው ነው።

አንዱ አደብ ማስያዣ መንገድ በርካታ የሲጃራ ማጨስና ከዚያ ጋር ተያያዥ የሆኑ ትዕይንቶች ላሉባቸው ፊልሞች ለሲኒማ የሚሰጠውን ድጎማ እየቆረጡ መቅጣት ሊሆን ይችላል።

ማቲው ካዞቪትዝ በፈረንሳይ ሥመ ጥር የፊልም ዳይሬክተር ናቸው። ይህን ሐሳብ ፈጽሞ አይቀበሉትም።

"ፊልሞች የኅብረተሰብ ተምሳሌት ለመሆን አይደለም የሚሠሩት። ፊልሞች የሚሠሩት የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማንጸባረቅ ነው" ይላሉ።

የሲጃራ ትዕይንት በሲኒማ ላይ ይቀነስ የሚለው ሐሳብ ከንቱና ጸረ ኪናዊ እንደሆነ ተሟግተዋል።

በተለያዩ ጊዜ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከየትኛውም አገር በላይ በፈረንሳይ ሲኒማዎች የትምባሆ ትዕይንቶች ይስተዋላሉ።

በአሜሪካ ከ2010 እስከ 2018 ብቻ በወጡ ሲኒማዎች 46 ከመቶ የሚሆኑት አንድ ገጸ ባህሪ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሲያጨስ ወይም ከሲጃራ ጋር የተያያዘ ተግባር ሲከውን ይታያል።

የፈረንሳይ የፊልም ፕሮዲውሰሮች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዣቪየር ሪጎልት የሲጃራ ትዕይንት በሚያሳዩ ፊልሞች ላይ መንግሥት ቁጥጥር ያድርግ የሚለው ዘመቻ መስመር ያለፈ ነው ብለዋል።

"መስመር ያለፈ ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ነጻነትንም የሚጋፋ ነው" ይላሉ።

ዣቪየር ጨምረው ሲኒማ ስለ ኅብረተሰቡ ምናገባው፤ ኅብረተሰብ ለማስተማር አይደለም ፊልም የምንሠራው ብለዋል።

በ60ዎቹ የገነነው የፈንሳይ ሲኒማ በጭስ ተደብቆም ተወዳጅነቱ ቀጥሏል። በሲጃራም ያለ ሲጃራም።