ትዳር፡ እንደሚጋቡ እያወቁ ታገቢኛለሽ ብሎ መጠየቅ ለምን?

ርብቃ ዋቅቶላ ትባላለች። የጋብቻ ስነ-ስርዓቷን የፈፀመችው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

ከሰርጓ በፊት ባለቤቷ ታገቢኛለሽ ሲል መጠየቁን ትናገራለች።

"መጀመሪያ ሽማግሌ ልኮ ነበር። ከዚያ ቤተሰብ እሺ እንዳለው ሲያውቅ የታገቢኛለሽ ጥያቄውን ፕሮግራም አዘጋጅቶ አቀረበልኝ"

ርብቃ ይህ ጥያቄ የቀረበላት ዕለት ደስተኛ እነደነበረች እና ጠብቃው እንዳልነበር ትናገራለች።

"ቅዳሜ ቀን ላይ ከሥራ እንደወጣሁ ብዙ ጊዜ የማገኛቸው ጓደኞቼ፣ አንድ ቦሌ የሚገኝ ሆቴል እንገናኝ ሲሉኝ ላገኛቸው ሄድኩኝ። ሆቴሉ ደርሼ ስገባ፣ ቤቱ ጨለማ ነበር። አንድም ሰው አላየሁም ነበር። ከዚያ ሰርፕራይዝ ሲያደርጉኝ እና ሳያቸው ልቤ በጣም መታ፤ ያልጠበኩት ነገር ነበር የሆነው፤ ከዚያም ተንበርክኮ ጠየቀኝ [ታገቢኛለሽ ብሎ] አዘጋጅቶልኝ የነበረውን ቀለበትም ሰጠኝ።"

በማለት ርብቃ በዕለቱ የነበረውን ታስታውሳለች።

ሙሽሪት የዛን ጊዜ እጮኛዋ እና የአሁን ባለቤቷን እንደምታገባው ወስና እንደነበር ትናገራለች።

በተጨማሪ የዚያኔ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ያቀረበ ቀን ወደ ወላጆቿ ሽማግሌ መላኩንም ታስታውሳለች።

ሽማግሌዎቹ የዚያን ዕለት ወደ ቤተሰቦቿ ሲሄዱ እርሱ ደግሞ የታገቢኛለሽ ጥያቄ አንዳንድ መሰናዶዎችን ማዘጋጀቱን በመጥቀስ "መቼም እምቢ አይሉኝም ብሎ ይመስለኛል" ትላለች ርብቃ።

በፍቅር አንድ ዓመት ካሳለፉት ባለቤቷ ጋር ብዙ የጓደኞቻቸውን የታገቢኛለሽ ጥያቄ ሲታደሙ እንደነበርም ትናገራለች።

ይህ ፕሮግራም ለእርሷም ሊዘጋጅ እንደሚችል አውቅ ነበር ትላለች።

ይህን ሁሉ ካወቅሽ ታዲያ ምኑ ነው ሰርፕራይ ያደረገሽ በማለት ቢቢሲ ጠይቋል።

ርብቃ እኔ ባልጠበቅኩት ቀን መሆኑ፣ ጓደኞቹ እንደወትሮ እንገናኝ ብለው አታለውኝ እዚያ ቦታ መገኘቴ በማለት 'ሰርፕራይዝ' የሆነችባቸውን ምክንያቶች ትዘረዝራለች። አክላም "የዚያን ቀን የደነገጥኩትን ድንጋጤ ልነግርሽ አልችልም" ብላለች።

ሙሽሪት ይህ ፕሮግራም የቃል ኪዳን ማሰሪያ ቀን እንደነበር ትናገራለች።

ቤተ ክርስትያን ከመረቀች በኋላ የተዘጋጀ የታገቢኛለሽ ፕሮግራም?

ዋቅወያ ደሱ፣ ከካናዳ የመጣችው ፍቅረኛውን ከቤተሰቦቹ ርቆ በጎረቤት አገር ኬንያ ነው የቃልኪዳን ቀለበት ያሰረላት። ይኹን እንጂ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ያዘጋጀው፣ ቤተ ክርስትያን ጋብቻውን ከመረቀችው በኋላ ነው።

" እንደ ወጉ ቢሆን ታገቢኛለሽ ጥያቄ የሚቀርበው ከጋብቻ በፊት ነው፤ እኔ ግን ስልተመቻቸልኝ ከጋብቻ በኋላ አቅርቤያለሁ።"

ዋቅወያ ይህንንም ሲያብራራ ከባህር ማዶ ከመጣችው ፍቅረኛው ጋር አብሮ ለማሳለፍ እና አብሮ ለመሆን የቤተ ክርስትያን ፈቃድ ስላስፈለገ፣ በቤተክርስትያን ሽማግሌዎች የምርቃት ስነስርዓት ተካሂዷል።

ከምርቃቱ ከሁለት ሳምንት በኋላም ኑሮውን በመሰረተበት ኬንያ የታገቢኛለሽ ፕሮግራሙን ማዘጋጀቱንም አክሎ ገልጿል።

ባለቤቱ ወደፊት ኢትዮጵያ ስትመለስ እና ቤተሰብ ባለበት ሠርግ ማካሄድ ስለሚፈልጉ፣ ይህንን ፕሮግራም በይፋ ሰዎች እንዲያውቁ በሚል ማዘጋጀታቸውን ተናግሯል።

"ይኼ የታገቢኛለሽ ፕሮግራም፤ መተጫጨታችንን ለማሳወቅ የፈፀምነው ነው፤" የሚለው ዋቅወያ ምክንያቱን ሲያስረዳም፤ "እኛ የቤተክርስትያን ሰዎች ስለሆንን ከቤተክርስትያኒቱ እውቅና ውጪ ከጋብቻ በፊት ምንም ዓይነት ነገር አልፈለግንም ለዚያ ነው መጋቢዎችና የቤተክርስትያን ሽማግሌዎች እንዲመርቁን ያደረግነው እንጅ በቤተክርስትያን ውስጥ ምንም የተዘጋጀ ምግብም ሆነ መጠጥ አልነበም።"

ዋቅወያ አክሎም ቤተ ክርስትያንም በዚህ መልኩ ለተጋቢዎች ጥምረት እውቅና መስጠቷ የተለመደ መሆኑን ያስረዳል።

በተጨማሪም በማያውቁት አገር ውስጥ መገናኘታቸው እና ሁኔታዎች አለመመቻቸታቸው ፕሮግራማቸው ከተለመደው ውጪ እንዲሆን እንዳደረገባቸው ይናገራል።

ዋቅወያ እንደ ርብቃ ሁሉ ባህል የሚጠይቀውን ሽማግሌ መላክ እና የትጭጭት ስጦታን መፈፀሙን ይናገራል።

ጊዜው ይተላለፍበት እንጂ እንደሌሎቹ ሁሉ ወጣቶች ዋቅወያም ፍቅረኛውን "የፎቶ መነሳት ፕሮግራም ካካሄድን በኋላ፣ ልብስ ቀይረን ስንመለስ ያዘጋጀሁት እና እርሷ የማታውቀው ልዩ ፕሮግራም ላይ ታገቢኛለሽ አልኳት እርሷም ፈቃደኝነቷን ገለፀች፤ በዚሁ ለሕዝብ አሳወቅን" ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስረዳል።

ዋቅወያ "ለኔ መጋባት ማለት ምርቃት ነው፤ ይኼ ፕሮግራም ደግሞ ፍቅረኛ ሳታውቅ አዘጋጅቶ የምታስደስታት ሲሆን፣ ለሚቀጥለው የጋብቻ ጉዞም በር የሚከፍት ነው ብዬ አምናለሁ" ይላል።

ለእኔ መኮረጅና ማስመሰል ነው

ዶ/ር አለማየሁ ፈቀደ፣ በጅማ ዩኒቨርስቲ የኦሮሞ ባህል ጥናት ማዕከል የህትመትና ጥናት ጉዳይ ኃላፊ ናቸው።

በኦሮሞ ባህል ላይ የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶችን ማመሳከራቸውን የሚናገሩት ዶ/ር አለማየሁ፣ ስለኦሮሞ ባህል ትጭጭት ቤተሰብ እንደሚሳተፍበት ይናገራል።

" ጎሳ ይጠናል፤ ባህሪ ይጠናል። ሽማግሌ ሲላክም ይህ ሁሉ ከተጠና በኋላ የሴት ቤተሰብ እሺም እምቢም ሊል ይችላል። ገድ ስለሚታይም የቤተሰብ ድርሻ ከፍተኛ ነው። እናም በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው ትጭጭት የሚደረገው።"

እንደ ኖረው ባህል ቢሆን ከትጭጭት በኋላ ነው የጋብቻ ዝግጅት የሚደረገው።

ይኹን እንጂ በአሁኑ ጌዜ እንደ ብርቅና ድንቅ የሚቀርበው የታገቢኛለሽ ጥያቄ ቤተሰብ አያቀውም የባህል መሰረትም የለውም ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህ ጥያቄም በየካፌ በየሆቴሉ አበባ አርከፍክፈው እንደ ዘበት የሚጠይቁት ነው እንጂ ገድ ታይቶ፣ የሚደረግ አይደለም በማለትም ልዩነቱን ያብራራሉ።

ወጣቶቹ በሚዲያ ተጽዕኖ የውጪ አገር ባህልን በመቀበል የሚያደርጉት መሆኑንም ይገልጻሉ።

"ሴቱም ወንዱም ለጋብቻ እንደተዘጋጁ ውስጣቸው እያወቀው ነገር ግን ተንበርክኮ እንደ አዲስ ታገቢኛለሽ ወይ ብሎ ቀለበት መስጠት፤ ለእኔ እንደ ቀልድ ነው የማየው" ካሉ በኋላ "እነዚህ ወጣቶች ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው ትውውቅ ቦታ ከመስጠት ይልቅ ታይታ ላይ ያተኮሩ ይመስላሉ።በተጨማሪም ከእነዚህ በኋላ የሚመጡት ትውልዶች ይህንን እንደራሳቸው ባህል አድርገው ሊቀበሉት ይችላሉ።"

ዶ/ር አለማየሁ ሃሳባቸውን ሲያጠናቅቁም፣ "ስለዚህ እንዲህ እየተደባለቀ ያለ ባህል ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት እና ለራስ ባህል ቅድሚያ መሰጠት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።