ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤተሰብ፡ የአማት እጅ የሚረዝምበት ትዳር የተባረከ ወይስ የተረገመ?
አማት በትዳር ውስጥ በጎ ስም የላትም። በተለይ የባል እናት ስሟ በክፉ ሲብጠለጠል ይሰማል፤ በሚስትና በዘመዶቿ። ለደራሲያንም ቢሆን የሴራ መጎንጎኛ የጡዘቱ ማክረሪያ አጀንዳ ሆኖ አገልግሏል። በአማርኛ ተረትና ምሳሌዎች ውስጥም ፈለግ ፈለግ ቢደረግ አይጠፋም።
አማትና ምራት ሳይስማሙ መሬት፣ ለቅልብልብ አማት ሲሶ በትር አላት... ወዘተርፈ
ሕንዶች ከልብ ወለዶቻቸውም ወጣ አድርገው ከተረትና ምሳሌዎቻቸውም አፈንግጠው 'የአማትን ነገር ማየት በብልሀት' በሚል ጥናትና ምርምር አድርገዋል።
እ.አ.አ. በ2018 ከቦስተንና ከዴልሂ የተውጣጡ ተመራማሪዎች 671 ያገቡ ሴቶችን አነጋግረዋል። እነዚህ ባለትዳር ሴቶች ከ28 መንደሮች የተመረጡ ሲሆኑ መኖሪያቸውን ያደረጉትም በጃንፑር አውራጃ ኡታር ፓርዴሽ ነው።
በዚህ አውራጃ የሚኖሩ ባለትዳር ሴቶች የተመረጡበት ምክንያት ማህበረሰቡ እጅጉን ወግ አጥባቂ በመሆኑ ነው ተብሏል። በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ሴቶች ዕድሜያቸውም ከ18 እስከ 30 እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
እነዚህ ሴቶች የሂንዱ ሀይማኖት ተከታይ ሲሆኑ ከዝቅተኛው ማህበረሰብ የተገኙ መሆናቸውም በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል። አብዛኞቹ ኑሯቸውን በግብርና የሚገፉ ሲሆን ሁሉም ማለት በሚያስደፍር መልኩ የሚኖሩት ከአማቶቻቸው ጋር ነው።
ተመራማሪዎቹ እነዚህን ባለትዳር ሴቶች ከቤት ውጪ ከዘመዶቻችሁና ከጓደኞቻችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል ሲል ጠይቀዋል።
አማቶቻቸው ይህ ግንኙነት ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ምን ያህል ነው ብለው በነፃነታቸው ላይ ያለውን ተጽዕኖ፣ የጤና አገልግሎት መፈለግ ላይ ያለውን አሉታዊና አዎንታዊ ጎን ፈትሸዋል።
በመጨረሻም አማቶች ያሉበት ቤት የምትኖር ሴት የመንቀሳቀስ ነጻነቷ የተገደበ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
በጥናቱ ውስጥ የተካተቱ ሴቶች ከቤቷ ውጪ ያላት ማህበራዊ ግንኙነት በአማት ጠንካራ ገመድ የተቀፈደደ ነው፤ በተለይ ደግሞ የቤት እመቤቶች በተንቀሳቀሱ ቁጥር አዳዲስ መረጃ የማግኘት፣ ከአቻዎቻቸው ጋር በሚፈጥሩት ወዳጅነት፣ በራስ መተማመናቸውን የመጨመር እንዲሁም ለሕይወት ያላቸውን በጎ ገፅታና መሻሻል የማበልፀግ እድል ቢኖራቸውም አማት ግን በአጭር ገመድ ይዛ አላላውስ በማለት ከዚህ ሁሉ እድል ገድባቸዋለች ይላል የጥናቱ ውጤት።
እንዲሁም ይላል ጥናቱ፤ የጤና፣ የወሊድ፥ እና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ የምትወስነው ውሳኔን፣ በሚኖራት ማህበራዊ ግንኙነትና ትስስር ጭምር የሚወሰን ሆኖ ሳለ ከዚህ ሁሉ እድል ተገልላ ትኖራለች ሲል ያስቀምጣል።
በጥናቱ ከተካተቱ ሴቶች መካከል 36 በመቶዎቹ የቅርብ ጓደኛም ሆነ ዘመድ በሚኖሩበት አውራጃ የላቸውም። 22 በመቶዎቹ ደግሞ ጭራሹኑ የልብ ወዳጅም ሆነ የቅርብ ዘመድ የላቸውም።
14 በመቶዎቹ ብቻ ለብቻቸው ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ፣ 12 በመቶዎቹ ደግሞ በመንደራቸው የሚገኙ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸውን ሄደው እንዲጠይቁ ይፈቀድላቸዋል።
በጃንፑር ለጥናቱ ተሳታፊ ከሆኑ ሴቶች መካከል ከባለቤታቸውና ከአማታቸው ውጪ በተለያየ ጉዳይ የተወያዩ ሴቶች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ተመራማሪዎቹ ከአማታቸው ጋር የሚኖሩና ከአማቶቻቸው ጋር የማይኖሩ ሴቶችንም በመለየት አጥንተዋል።
ከዚህም ጥናታቸው ያገኙት ከአማቶቻቸው ጋር የሚኖሩ ሴቶች በጣም ትንሽ የቅርብ ጓደኞች ያላቸው ሲሆን ይህም የሚያሳየው አማቶች ምራቶቻቸው ብቻቸውን እንዳይንቀሳቀሱ፣ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ከሌላ ሰው ጋር እንዳያጠናክሩ በማድረግ የቤተሰብ ምጣኔ ምርጫቸውን እንዲሁም የቤተሰብ ቁጥራቸውን እንደሚወስኑ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉ ነው ተብሏል።
አንዳንዴ አማቶች በርካታ የልጅ ልጆች እንዲኖሯቸው ይፈልጋሉ። በተለይ በርካታ ወንዶች።
በጥናቱ ከተካተቱት ግማሸ ያህሉ እንደተናገሩት አማቶቻቸው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን አይደግፉም። በተለይ ባላቸው ከቤት ውጪ ራቅ ያለ ስፍራ በመሄድ የሚሰራ ከሆነ የአማቶች ቁጥጥር ጠበቅ ያለ ይሆናል።
ይህም በመንቀሳቀስ ነጻነታቸው፣ በውሳኔዎቻቸው ላይ ነጻነት እንዳይኖራቸው በማድረግ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳርፋል።
በጥናቱ የተገኘው ሌላው ነጥብ አማቶች ሁሌም ቢሆኑ መጥፎ አለመሆናቸው ነው።
አማቶች ምራቶቻቸው ባረገዙ ወቅት ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ በማድረግና ክትትላቸው እንዳይስተጓጎል በጎ አስተዋጽኦ በመጫወት ስማቸው በደግ ተነስቷል።