ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሥራ እና ፍቅር፡ ከሥራ አጋርዎ ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመር ሊያስባርር ይገባል?
አውስትራሊያዊው የንግድ ሰው ጌሪ ሊዮን በሥሩ ከምትሠራ ተቀጣሪ ጋር በጀመረው የፍቅር ግንኙነት ምክንያት ከሥራ የተባረረበትን ዕለት አይረሳትም።
ነገር ግን 'ሁሉም ለበጎ ነው' እንዲሉ የፍቅር ግንኙነቱ ፍሬ አፍርቶ ከታምራ ጋር ትዳር ከመሠረቱ 12 ዓመታት አለፉ፤ የ11 ዓመት ሴት ልጅም አለቻቸው።
አሁን አቶ ጌሪ እና መ/ሮ ታምራ የራሳቸው ኩባንያ አላቸው። ሠራተኞችም ቀጥረዋል። ጌሪ፤ እኔ ሠራተኞቼ እርስ በርስ የፍቅር ግንኙነት ቢጀምሩ ምንም ቅር አይለኝም ይላል። ሥራቸውን በአግባቡ እስከከወኑ ድረስ።
የማክዶናልድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑ ስቲቭ ኢስተርብሩክ ከበታች ሠራተኛቸው ጋር የፍቅር ግንኙነት መሥርተዋል ተብለው ከመንበራቸው እንዲነሱ የተደረገው ትላንት ነበር። ኩባንያው ምንም እንኳ ሥራ አስኪያጁ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ቢሆንም የጀመሩት የድርጅታችንን ሕግ ጥሰዋል ሲል አትቷል።
ይህ ዜና ብዙዎች ከሥራ አጋር ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመር ሊያስባብር ይገባል ወይ? ብለው እንዲጠይቁ አድርጓል።
አቶ ጌሪ የተባሩረበት መሥሪያ ቤት መስኮትና እና በር እየሠራ የሚሸጥ ነበር። እሳቸው 'ኦፕሬሽን ማኔጀር' ነበሩ። የአሁኗ ባለቤታቸው ወ/ሮ ታምራ አስተባባሪ ሆነው ነበር የተቀጠሩት። ቀስ እያለ ቅርርባቸው እየበረታ መጣ። ጌሪ የ41 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ፤ ባለቤታቸውን ደግሞ በ14 ዓመት ይበልጧቸዋል።
መጀመሪያ ግንኙነታቸውን በድብቅ ያዙት። እያደር ግን መደበቁ አዋጭ ሆኖ አልታያቸውም። ከሦስት ወራት ገደማ በኋላ አቶ ጌሪ በበላይ አለቆቻቸው ተጠሩ። ያልተገባ ነገር አድርገሃልና ልናባርርህ ተገደናል የሚል አጠር ያለ መግለጫ ተሰጣቸው። ታምራ ግን እንደማይበረሩ ተነገራቸው።
ጌሪ በወቅቱ ምንም የጣሱት ሕግ እንደሌለ ይናገራሉ። ሥራቸውንም በአግባቡ ሲፈፅሙ እንደነበር ነው የሚያወሱት።
«ከሥራ አጋር ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመር ሊያስባብር ይገባል ወይ? በፍፁም። በፈቃደኝት ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ።»
አንድ ጥናት፤ ዘላቂ የፍቅር ግንኙነት ከመሠረቱ ሰዎች በርካታዎቹ የተገናኙት ሥራ ላይ ሳሉ ነው ይላል። ይህ ማለት ሁሉም ሥራ ቦታ የሚመሠረቱ ግንኙነቶች ዘላቂ ናቸው ማለት ግን አይደለም።
ከበታች የሥራ አጋሮቻቸው ጋር ፈቃድ ላይ የተመሠረተ የፍቅር ግንኙነት በመመሥረታቸው መንበራቸውን እንዲለቁ የተደረጉ በርካቶችን መጥቀስ ይቻላል።
አሜሪካ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች የበላይ ሠራተኞች ከበታች ሠራተኞች ጋር ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም እንኳ ግንኙነት እንዲመሠርቱ አይሹም። በተለይ ደግሞ ክብሩ የተገፈፈው የፊልም ሰው ሃርቪ ዋይንስታይን በበርካታ ሴቶች የወሲባዊ ጥቃት ክስ ከቀረበበት በኋላ።
ቢሆንም ብዙዎች ግንኙነት ፈቃድ ላይ እስከተመሠረተ፣ ሠራተኞቹ ሥራቸውን በአግባቡ እስከከወኑና ኃላፊነታቸውን እስከተወጡ ድረስ ተጠያቂነት ሊመጣ አይገባም ባይ ናቸው። መቼስ የሰው ልጅ ፍቅርን እዚህ ቦታ ብቻ ነው የማገኘው ብሎ የሚገድብበት አቅም የለውምና።