ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሳምሰንግ ኩባንያ ቤተሰብ በዓለም ትልቁን የውርስ ግብር ሊከፍል ነው
የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ትልቁ ባለድርሻ የሆኑት ግለሰብ ቤተሰብ ምናልባትም በዓለም ከፍተኛ የተባለውን የውርስ ግብር ለመንግሥት ሊከፍሉ ነው።
ቤተሰቡ ከሟቹ ሊቀመንበር ሊ ኩ ሂ ንብረቶች የውርስ ግብር የሚከፍሉት ጠቅላላ ገንዘብ ወደ 10.78 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል።
ደቡብ ኮሪያ በዓለም ከፍተኛ የውርስ ግብር ከሚጥሉ አገራት አንዷ ናት።
ሚስተር ሊ ሳምሰንግን ከአገር ውስጥ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በማምጣት ኩባንያው ትልቅ ስኬት እንዲቀዳጅ ያደረጉ ሰው ነበሩ።
የሞቱት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ እንደነበር ይታወሳል።
ከሰሞኑ በርካታ ባለሀብቶች ይህንን የውርስ ግብር ጉዳይ በቅርብ ሲከታተሉት ነበር። ምክንያቱም በውሳኔው ላይ ቤተሰቡ በሳምሰመንግ ኩባንያ የሚኖረውን ድርሻ የሚወስን በመኾኑ ነው።
በሳምሰንግ ኩባንያ ድርሻ ያላቸውና የሌላቸው ባለሀብቶች አሁንም ቢኾን ዝርዝር አፈጻጸሙንና ግብሩ ቤተሰቡ ላይ የሚፈጥረውን የድርሻ ክፍፍል በአንክሮ እየተከታተሉ ይገኛሉ።
ይህ የግብር ክፍያ አሁን የሳምሰንግ ሊቀመንበር በሆኑትና በሚስተር ሊ ወንድ ልጅ ጄ ዋይ ሊ የሽርክና ድርሻ ላይ የሚያወጣው ለውጥ ካለ በሚል በብዙ ባለሀብቶች ዘንድ ጉዳዩ ትኩረት አግኝቷል።
የሚስተር ሊ ወንድ ልጅ ጄ ዋይ ሊ ከአውሮፓውያኑ 2014 ወዲህ የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ባለቤት ተደርጎ ይታሰባል።
ይሁን እንጂ ጄ ዋይ ሊ በአሁን ጊዜ ሰዓት በእስር ቤት ነው የሚገኘው። ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞዋ የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ፓርክን ጭምር ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና ባለሀብቶችን ባነካካ የሙስና ቅሌት ሁለት ዓመት ተኩል ዘብጥያ እንዲወርድ ስለተፈረደበት ነው።
ሳምሰንግ ኩባንያ ራሱ ባተመው የኩባንያው የጽሑፍ መግለጫ እንዳለው ከሆነ ይህ የውርስ ግብር በኮሪያም ሆነ በዓለም ምናልባትም ትልቁ ሳይሆን አይቀርም።
የሚስተር ሊ ቤተሰብ ለመንግሥት የሚከፍለው የውርስ ግብር 12 ትሪሊዮን ዎን [የደቡብ ኮሪያ ገንዘብ] ወይም 10 ቢሊዮን ዶላር ሲሰላ ሟቹ ቢሊየነርና የሳምሰን ሊቀመንበር ከነበሩት ሚስተር ሊ በጊዜው ከነበራቸው ሀብት ግማሹን የሚሸፍን ነው።
ሚስተር ሊ ከኤሌክትሮኒክስ ኩባንያው ሌላ በብዙ ዘርፎች በርካታ ሀብቶችን ነበሯቸው።
የሚስተር ሊ ስብስብ ቅርሶችና ሥዕሎችን ለብሔራዊ የኮሪያ ሙዚየም እና ለሌሎች ባሕላዊ ተቋማት በስጦታ ይበረከታል።
የሟቹ ሚስተር ሊ የጥበብ ስብስቦች በስመጥር አርቲስቶች የተሠሩ ብርቅዬ ሥራዎች ናቸው።
የማርክ ቻጋል፣ የባብሎ ፒካሶ፣ የፖል ጋውጊን፣ የክላውድ ሞኔት፣ ጆን ሚሮ እና የሳልቫዶር ዳሊ ሥራዎች በሚስተር ሊ የጥበብ ስብስብ ውስጥ ተካተዋል።
የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት እነዚህን ስጦታዎች ለሙዚየሞች በገጸበረከትነት ማበርከት የቤተሰቡን የውርስ ግብር በትንሹ ሊቀንሰው ይችላል።
የደቡብ ኮሪያ የውርስ ግብር ከጠቅላላው ሀብት 50 ከመቶ እኩሌታ የሚሆን ሲሆን ይህም ከጃፓን ቀጥሎ በዓለም ትልቁ የውርስ ግብር ምጣኔ ነው።
ሟቹ በኩባንያው ውስጥ ቁጥጥሩ ከፍ ያለ ከነበረ በዚህ የ50 ከመቶ ምጣኔ ላይ የፕሪምየም (ቀጥተኛ ያልሆኑ አበሎች) ክፍያዎችም ስለሚጨመሩበት ግብሩ ተቆልሎ የጠቅላላ ሀብቱን ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል።
በዩናይትድ ኪንግደምም ሆነ በአሜሪካ የውርስ ግብር ምጣኔ የሚሰላው 40 በመቶና ከዚያ በታች ሆኖ ነው።