ምርጫን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሶማሊያ ውዝግብ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ያመራ ይሆን?

በሶማሊያ ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ መዘግየቱ አለመግባባትን እና በፖለቲከኞች መካከል አለመተማመንን አባብሷል።

ይህንንም ተከትሎ በመዲናዋ ሞቃዲሾ የሰዎች ሕይወት የጠፋበት አመጽ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።

በመዲናዋ ሞቃዲሾ በፌዴራል ኃይሎች እና በታጠቁ የተቃዋሚ ታማኝ ኃይሎች መካከል ከቀናት በፊት በተነሳ ግጭት ቢያንስ አስር ሰዎች ተገድለዋል። ግጭቱ ይቀጥላል በሚል በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች 'ሠላማዊ' ወደሚሏቸው መንደሮች ተሰደዋል።

ክፍተቱ ለአል-ሻባብ የአፍሪካ ቀንዷን አገር የበለጠ ለማተራመስ መልካም አጋጣሚ ሊሆነው ይችላል።

ታጣቂዎቹ ከቅርብ ወራት ወዲህ ብቻ በምርጫው ዙሪያ ውይይቶች በተካሄዱባቸው ቦታዎች ላይ በርካታ ጥቃቶችን አካሂደዋል።

የአገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት የፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆን የስልጣን ዘመን በሁለት ዓመት ይራዘም ሲል ወሰነ። ከሁለት ሳምንት በፊት ከተላለፈው ውሳኔ በኋላ የአገሪቱ የፖለቲካ ክፍተቶች ተባብሰዋል።

ከወራት ውይይቶች በኋላ ውሳኔው ሲጸድቅ የፌዴራል መንግሥቱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝባዊ ምርጫዎችን እንዲያደራጅ ቢያዝም የአገሪቱን የምርጫ ቀውስ ማስቆም አልቻለም።

የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሥልጣን ማራዘሙን ውድቅ በማድረግ ፋርማጆን ሥልጣንን የሙጥኝ ብለዋል ሲሉ ከሰዋል።

የተነሳባቸው ተቃውሞና ሊከተል የሚችለው ቀውስ ያሰጋቸው ፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመናቸውን የማራዘም ፍላጎታቸውን እንዲተዉ አስገድዷቸዋል።

ነገር ግን ውጥረቱ በጎሳ ፉክክር ይበልጥ እየከረረ ነው። ከአስርት ዓመታት የእርስ በእርስ እና የታጣቂዎች ግጭት በኋላ የተገኘውን አንፃራዊ መረጋጋት ሊቀለበስ የሚችልም ነው።

ቁልፍ ተዋናዮች እና ምላሾች

ተቃዋሚዎች የፋርማጆ ሥልጣን የካቲት 8 ስላበቃ ከእንግዲህ ለፕሬዝዳንትነታቸውን እውቅና አንሰጥም ብለዋል።

ናሽናል ሳልቬሽን ፎረም (ብሔራዊ አገርን የማዳኛ መድረክ እንደማለት ነው) ተቋቁሟል። ፎረሙ ተሰሚ በሆኑ ተቃዋሚዎች የተቋቋመ ነው።

የፋርማጆ ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑት የምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብዲ ሀሺ አብዱላሂ፣ የጁባላንድ እና ፑንትላንድ መሪዎችን ያካተተ ጥምረት ነው።

ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነው የሥልጣን ማራዘሚያ ላይ "አስፈላጊ እርምጃዎችን እንወስዳለን" ሲሉም ዝተዋል።

የሴኔቱ አፈ ጉባኤ አብዱላሂ እንዳሉት፤ ፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ሐሳቡን ለማጽደቅ የላይኛውን ምክር ቤት ሳያቀርቡ ማራዘማቸው ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ነው።

የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት ሰኢድ አብዱላሂ ዴኒ እና የጁባው አቻቸው አህመድ መሐመድ ኢስላም በሞቃዲሾ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ነበር። "ሶማሊያን ከማይቀረው የትርምስ አዘቅት ውስጥ እንዳትገባ እንዲያድኑ" ጠይቀዋል።

የፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ምክር ቤት ፋርማጆን ለመተካት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው የፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ጥምረት ነው።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሼህ አህመድ የሚመራ ሲሆን ፕሬዚዳንቱን "የጦር አበጋዝ" ብለዋቸዋል።

የሃውያ ንዑስ ጎሳ አባላት ተደማጭነት ካላቸው ጎሳዎች መካከል ነው። ለአንድ ቀን በመዲናዋ ሞቃዲሾ ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ ሥልጣን የማራዘሙን ውሳኔ ውድቅ አድርገውታል።

አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና የአውሮፓ ሕብረት ሥልጣን የማራዘሙ ውሳኔ ሶማሊያ ወደ ሰላምና መንግሥት ግንባታ የምታደርገውን ጉዞ የሚያደናቅፍ ነው ብለዋል።

ግንኙነታቸውን በድጋሚ እንደሚያጤኑትም አስጠንቅቀዋል። አሜሪካ "ሰላምና መረጋጋትን በማደናቀፍ" በሥልጣን ማራዘሙ በተሳተፉት ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል ዝታለች።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ሥልጣን ማራዘሙን ውድቅ አድርጎታል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የሶማሊያ መሪዎች በምርጫ ውዝግቡ ዙሪያ ውይይት እንዲቀጥሉ ያቀረበውን ሐሳብ እንደሚደግፍ አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢቀርብባቸውም በታችኛው ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴዎች እና በጋልሙዱግ፣ በሂውማሌ እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ሰፊ ድጋፍ አላቸው፡፡

በቋፍ ላይ ያለ የፌዴራል ሥርዓት

የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ሥር የሰደደውን የጎሳ ግጭት ለማቆም እና የአንድነት መንግሥት ለመመስረት የሚደረገውን ጥረት በመሰናከሉ የተመሠረተ ነው።

ይህን ተከትሎም የተቆራረጠ እና ደካማ ቢሆንም ብሔራዊ ደኅንነት ግንባታው እያዘገመም ቢሆን እንዲጓዝ መንገዱን ጠርጓል።

አገሪቱ ከ30 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ሥርዓት ለመቀላቀል የፋይናንስ ተቋማቷን እንደገና አደራጅታለች።

ምርጫው ያስከተለው አለመረጋጋት በማዕከላዊ መንግሥት እና ቀድሞውንም የፋርማጆን ሥልጣን 'በሚያኮስሱት' አንዳንድ የክልል መንግሥታት መካከል ውዝግቡን አጡዞታል።

እአአ በመስከረም 2018 አምስት የአገሪቱ የክልል ፕሬዚዳንቶች በሥልጣን እና በሀብት ክፍፍል አለመግባባት ምክንያት ከፌዴራል መንግሥት ጋር እንደማይተባበሩ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ለምላሽ አልዘገዩም። ክልሎችን በራሳቸው ቁጥጥር ስር ማድረግ ጀመሩ። ተቀናቃኝ ሊሆኑ የሚችሉትን በመንቀል አጋሮቻቸውን በጋልሙዱግ እና በደቡብ ምዕራብ ግዛቶች አስቀመጡ።

የፌዴራሉ መንግሥት በፑንትላንድ እና በጁባላንድ ባሉ ምርጫዎች ላይ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ማሳደር አልቻለም። የእነዚህ አካባቢ መሪዎች ፋርማጆ እንደገና እንዳይመረጡ እየሠሩ ነው። የፖለቲካ ህልውናቸው የተመሠረተው በዚሁ ላይ ነው።

የመስከረም 17ቱ ስምምነት

ብሔራዊው የምርጫ ኮሚሽን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለው ሕዝባዊ ምርጫ ለማድረግ እንደማይቻል አስታውቋል።

ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማዘጋጀት እስከ 13 ወር ድረስ እንደሚያስፈልገው እአአ ሰኔ 2020 ለሕዝብ እንደራሴዎች ገልጿል።

የጁባላንድ፣ ፑንትንትላንድ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫውን መዘግየት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም።

እአአ ሐምሌ 2020 አስደንጋጭ ነበር የተባለለት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን አሊ ኬይሬ ከሥልጣን መነሳት በምርጫው ሂደት ላይ ያላቸውን እምነት ይባስ ሸረሸረው።

የጁባላንድ እና የፑንትላንድ መሪዎች በማዕከላዊው ዱሳማሬብ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልነበሩም።

በስብሰባው ላይ ከምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያ ስምምነት ተደርሷል። የአማጺያኑ አመራሮች አድሏዊ ነው ሲሉ የምርጫ ኮሚሽኑ እንዲፈርስ ጠይቀዋል።

እአአ መስከረም 17 ቀን 2020 ከሳምንታት የዓለም አቀፍ ግፊት በኋላ በምርጫ ሁኔታዎች ላይ ስምምነት ተፈረመ።

በስምምነቱ መሠረት ሁለት የምርጫ ክልሎች በእያንዳንዱ ክልል ይኖራሉ። ምርጫዎች የሚካሄዱት በየክልል ተሰብሳቢዎች ላይ ተመስርቶ ሲሆን በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ውስጥ 101 የምርጫ ልዑካን ድምጽ ይሰጣሉ።

በአማጽያን ጥያቄ መሠረት ምርጫውን በበላይነት የሚቆጣጠር ብሔራዊ እና ክልላዊ የምርጫ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ተወሰነ።

የጁባላንዱ ማዶቤ እና የፑንትላንዱ ዴኒ በፌዴራል መንግስት የተቋቋመውን የምርጫ ኮሚሽን ባለመቀበላቸው የስምምነቱ ትግበራ እንቅፋት ገጠመው። የጸጥታ አዛዦች እንዲነሱ እና ፓርላማው እንዲበተንም ጠይቀዋል።

የምርጫውን መዘግየት አስቀድሞ የገመተው የፌዴራሉ ፓርላማ እአአ ኅዳር 2020 አዲስ ተመራጮች እስኪተኩ ድረስ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ውሳኔ አስተላልፏል።

የዘር ፖለቲካ እና ግጭት

በምርጫው ላይ በተፈጠረው ክፍፍል ላይ ብሔራዊ ማንነት እና የጎሳ ማንነት ልዩነትም ሚና ተጫውተዋል።

አለመተማመን እየጠነከረ ሲሄድ ፖለቲከኞች እና ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት ወደ ጎሳቸው መመሸግ ጀመሩ።

እነዚህም በጎሳ ሚሊሻዎች፣ በጎበዝ አለቆች እና በቀድሞ የጦር መሪዎች የሚጠበቁ ናቸው። የተወሰኑ የተቃዋሚ የፓርቲ አመራሮች ለትጥቅ ትግል መዘጋጀት ያዙ። የጦር መሣሪያዎችና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የገዙም አሉ።

በመዲናዋ ሞቃዲሾ የዘገየውን ምርጫ የሚቃወሙ ሰልፈኞችን በሚደግፉ ወታደሮች እና በፖሊስ መካከል መጋቢት 15 ቀን ግጭት ተፈጥሯል።

የፖሊስ መኮንኖቹ በቱርክ የሰለጠነው ልዩው የሃርማድ የፖሊስ ኃይል አባላት ነበሩ። ከዚህ በፊት መንግሥት ፍላጎቱን በክልል መንግሥታት ላይ ለመጫን ልዩ ኃይሉን ይጠቀም ነበር።

የቀድሞው የሞቃዲሾ የፖሊስ አዛዥ ሳዲቅ ኦማር ሃሰን (ሳዳቅ ጆን) በምርጫ ውዝግብ ላይ ለመወያየት የተዘጋጀውን የፓርላማ ስብሰባ በማገድ እአአ ሚያዝያ 13 ፊታቸውን መንግሥት ላይ አዞሩ። ከኃላፊነት ተነስተው ማዕረጋቸውም ተገፈፈ።

የቀድሞው የፖሊስ አዛዥ ከቀናት በኋላ በጎበዝ አለቆች እና ከጎሳቸው በተገኙ ሚሊሺያዎች እየተጠበቁ በከተማው በዳይናል አካባቢ ካምፕ መሠረቱ።

መንግሥት የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎችን በአቅራቢያው ወደሚገኙ አካባቢዎች በማሰማራቱ ውጥረቱ ዋና ከተማዋን አዳርሷል።

በኋላ ላይ ሁኔታው ተረጋጋ። በፋርማጆ ላይ የተጀመረው አዲስ አመጽ የጎሳ ጦርነት ቀስቅሶ አገሪቱን በቀላሉ ወደ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳያስገባ ያሰጋል።

የፖለቲካ እና የደኅንነት አንድምታዎች

የአልሻባብ ታጣቂዎች በ2011 ከሞቃዲሾ ከተባረሩ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦርነት ድባብ በከተማዋ ሰፍሯል።

ጂሃዳዊው ቡድን ከአብዛኞቹ ዋና ዋና ከተሞች ተጠራርጎ ተባሯል። ብሔራዊው ጦር፣ በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ልዑክ እና በአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ ጥረት ቢያደረጉም ቡድኑም አሁንም በማዕከላዊ እና በደቡባዊ ክልሎች ኃይሉ እንዳለ ነው።

አል-ሸባብ በሞቃዲሾ በርካታ ጥቃቶችን ፈጽሟል። የተፈጠረውን ሁከት በመጠቀምም እንቅስቃሴዎቹን ለማጠናከር ሊጠቀምበት ይችላል።

እንደመገናኛ ብዙሃን ከሆነ አዲስ ጉዳት የደረሰባቸው ሕንፃዎች፣ ታንኮች እና የጦር ተሽከርካሪዎች ላይ የታጠቁ ወታደሮች እና ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል።

በግል በሚተዳደረው ራዲዮ ኩልሚዬ የሚሠራ አንድ ጋዜጠኛ እንደተናገረው፤ ትራፊክ እና የማዘጋጃ ቤት ፖሊሶች በጎዳናዎች የሉም።

የአል-ሸባብ ጥቃትን ለመከላከል በዋና ዋና መንገዶች ላይ የተተከሉ የደኅንነት ካሜራዎችም ወድመዋል።

በትጥቅ የተደገፈው አመጽ የፕሬዚዳንት ፋርማጆን የእውቅና ጥያቄ የከድጡ ወደ ማጡ የወሰደው ሲሆን፤ በምርጫ ውዝግብ ላይ የተከፈተውን የውይይት መስኮትም የሚዘጋ ነው።