በአማራ ክልል ደባርቅ ከተማ አቅራብያ የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ሊከፈት ነው

ከስድስት ወራት በፊት በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ የነበሩ ሁለት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ከአገልገሎት ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ በአማራ ክልል ደባርቅ ከተማ አቅራብያ የስደተኞች መጠለያ ሊገነባ መሆኑን የተመድ የስደተኞች ተቋም አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከስደተኞች እና የስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ጋር በመሆን በትግራይ ክልል እንዲዘጉ በተደረጉት ሁለት መጠለያ ጣብያዎች ምትክ በአማራ ክልል ደባርቅ ከተማ አቅራብያ ለመገንባት ቦታ የመለየት ስራ መከናወኑን ለቢቢሲ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በስፍራው ላይ ለኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ለመገንባት ሕጋዊ ሰነዶች እስኪሟሉ እየጠበቀ መሆኑን ለቢቢሲ በኢሜል በሰጠው ምላሽ ላይ ጨምሮ ገልጿል።

እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ የክረምቱ ወራት ከመጀመሩ በፊት ግንባታውን ለማካሄድ እና ስደተኞቹን በቦታው ለማስፈር እቅድ ተይዟል፟።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራውያን ስደተኞች ጉዳይ

ጥቅምት 23 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ የነበሩ ሁለት ትልልቅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች፣ ሕጻጽ እና ሽመልባ፣ ከአገልገሎት ውጪ መሆናቸው ተከትሎ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተበታትነዋል።

በወቅቱ በመጠለያ ጣብያዎቹ ተጠልለው የነበሩ ከ 19 ሺህ 200 ኤርትራዊያን ስደተኞች ወደተለያዩ ቦታዎች መሸሻቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ አዲ ሃሩሽ እና ማይ አይኒ መጠለያዎች ገብተዋል ሲል ኮሚሽኑ አክሎ ገልጾ ነበር።

ከእነዚህ ውስጥም እስከ አሁን 2ሺህ 500 የሚሆኑት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም እያካሄደ ባለው የምዝገባ ስራ መረዳቱን የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ዋና ሃላፊ ተስፋሁን ጎበዛይ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ተስፋሁን እንደሚሉት ወደ ሁለቱ ካምፖች ከተመለሱት ውጪ ያሉት ስደተኞች የት እንዳሉ ለማወቅ ተፈልጎ ምዝገባ ተደርጓል።

አክለውም ፖሊስን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት በተሰበሰበ መረጃ መሰረት ከ 6000 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ከመጠለያ ጣብያዎቹ ወጥተው ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።

ምዝገባውንም መጠለያዎቹን ሲያስተዳድር የቆየው የተመድ የስደተኞች ተቋም እና የስደተኞች እና ስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ጋር በጋራ እንዲያካሂድ በተጠየቀው መሰረት እያከናወኑ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ45,000 በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአዲስ አበባ መመዝገቡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ቃል አቀባይ ኤልሳቤጥ አርስንዶርፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኃላፊዋ አክለውም ከእነዚህም መካከል 25,255 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ኃላፊዋ በኢሜል በሰጡት ምላሽ ላይ ገልፀዋል።

እስከ ሚያዚያ ወር አጋማሽ ድረስ ብቻ 2500 ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ኤርትራውያን ስደተኞችን መመዝገባቸውን አክለው ገልፀዋል።

ስደተኞቹ ምን ይላሉ?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ያሉ ሶስት ኤርትራዊያን ስደተኞችም እነርሱን ጨምሮ በርካቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

ነገር ግን አሁን በስራ ላይ ወዳሉት ካምፖች መመለስ እንደማይፈልጉ ግን አልሸሸጉም።

ከእነዚህ መካከልም ተከስተ (ስሙ የተቀየረ) ይገኝበታል። በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ የሚገልፀው ወጣቱ በጋራ መኖሪያ ውስጥ በርከት ካሉ ጓደኞቹ ጋር እንደሚኖር ይናገራል። ውጪ ካሉ ዘመዶቹ በሚላክ አነስተኛ ድጎማ እንደሚኖር የሚናገረው ተከስተ፣ ይህ የአብዛኛው ኤርትራዊ ስደተኛ የገቢ አማራጭ መሆኑን ያስረዳል።

ምንም እንኳን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ቢገቡም እሱ እና ጓደኞቹ በትግራይ ክልል ወዳሉ የስደተኛ መጠለያዎች መግባት እንደማይፈልጉ ገልጿል።

ይህም ጥቃት ይደርስብናል ከሚል ስጋት የመነጨ እንደሆነ "የኤርትራ ወታደር ነው የሚገድለን በሚል ቁጭት እኛን እንዳያጠቁን ስንል ነው የምንፈራው" በማለት ያስረዳል።

የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ኃላፊው አቶ ተስፋሁን፣ ከዚህ በፊት የሰራነው ስህተት መደገም የለበትም ሲሉ ያብራራሉ።

በዚህም የተነሳ መጠለያ ጣብያው፣ ስደተኞቹ ሸሽተው ከመጡበት የስጋት አካባቢ ራቅ ብሎ መቋቋም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም ይገልፃሉ።

አዲስ የስደተኛ መጠለያ ጣብያዎችን ለማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ የቦታ መረጣ እና አለማቀፍ መስፈርቶቹን የሚያሟላ ቦታ ማግኘት ግን ገና ብዙ የሚቀረው ስራ መሆኑን ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይም ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ነበሩበት የመጠለያ ጣብያ ለመመለስ ያሉባቸውን የደህንነት ስጋቶች ተቋሙ እንደሚረዳ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚሉት በጦርነቱ ወቅት በካምፖቹ ውስጥም ጭምር ግጭቶችን ተመለክተዋል፡፡ ከመጠለያ ጣብያዎቻቸው ወጥተው ወደ አቅራቢያ ከተሞች ከዛም ወደ አዲስ አበባ እስከሚደርሱ በነበራቸው ጉዞም እጅግ አሰቃቂ ጥቃቶች እንዳጋጠሟቸውም ይገልፃሉ።

ወደ አዲስ አበባ ከመጡ እንዲሁም የተመድ የስደተኞች ተቋም ምዝገባውን ካካሄደ በኋላም እንደ ህክምና ያሉ አገልግሎቶች ሳያገኙ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ተስፋሁን ይህ ችግር መቃለሉን ቢገልፁም፣ ስደተኞቹ ወደ ኤርትራ እንመለሳለን በሚል ስጋት ለወራት ተደብቀው በመቆየታቸው አገልግሎቶች ለመስጠት እንዳላስቻለ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የሕክምና ወጪዎችን ለመሸፈን ከተመድ የስደተኞች ተቋም ጋር ምክክር እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉት ስደተኞች ቢኖሩም ከካምፕ ውጪ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ስደተኞችን ቢቢሲ አነጋገራል።

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት "እኔ ፕሮሰስ አለኝ። ወደ ሌላ አገር እሄደላሁ። ተከራይቼ ነው የምኖረው። ስራም አለኝ። እና ወደ ካምፕ መመለስ አልፈልግም፤ ግን ደሞ ፕሮሰሴ እንዳይቋረጥ ስጋት አለኝ" ሲል ያስረዳል።

አቶ ተስፋሁን እንደዚህ ያሉ ከመጠለያ ውጪ መኖር የሚችሉ ስደተኞችን ሁኔታ የሚፈቅድ ህግ ኢትዮጵያ እንዳላት ያስረዳሉ። ነገር ግን ለጋሽ አገራት ከካምፕ ውጪ ስደተኞችን ለማቋቋም የገቡትን የድጋፍ ቃል አላከበሩም አሁንም ያንን እንዲያከብሩ ጥሪ እያደረግንላቸው ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ የኤርትራዊያን ስደተኞች ቁጥር በድንገት በመጨመሩ ብዙዎች የቤት ኪራይን ጨምሮ ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች መሰማታቸውንም ለዋና ዳይሬክተሩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ባሉ ሶስት ወራት ብቻ 156 ኤርትውያንን በተለያዩ ምክንያቶች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስተውቆ ነበር፡፡

ነገር ግን ይህን ከካምፕ ውጪ ስደተኞች የሚስተናገዱበት ፖሊሲ የራሱ መርሆች አሉት የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአዲስ አበባ ብቻ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ከካምፕ ውጪ መገኘቱ እንዳለ ሆኖ፣ በድንገት ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱ የሚያመጣውን ጫና እያጠኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም በአዲስ አበባ ተመዝግበው እየኖሩ ለሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አብረውት ከሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እንደሚሰራ ለቢቢሲ ገልጿል።

ይህ ከለላ የመስጠት አገልግሎት የተለያዩ ነገሮችን የሚያቅፍ ነው ያሉት የድርጅቱ ቃል አቀባይ፣ ውስን የሆነ የጤና አገልግሎት እና የትምህርት እንዲሁም መንግሥት ለዜጎቹ የሚያቀርበውን መሠረታዊ ግልጋሎት የማግኘት መብት ስደተኞቹ እንዳላቸው ጨምረው ይገልፃሉ።

ተመድ በአሁኑ ሰዓት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአዲስ አበባ የገጽ ለገጽ አገልግሎት መስጠት ባይችልም በስልክ እና በኦንላየን አገልግሎቱን እያቀረበ መሆኑን ጨምረው አስታውሰዋል።

አዲስ አበባ በግላቸው የመጡ የኤርትራ ተፈናቃዮችን በሚመለከት ሲናገሩ ድርጅቱ ስደተኞቹ ተገቢውን ሰነድ እንዲይዙ እና አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የመለየት ሥራ እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።