ብራዚል በዓለም በቁመቱ ሦስተኛ የሆነ የክርሰቶስ ሐውልት እየገነባች ነው

በብራዚል ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ኤንካታዶ ከተማ የሚገነባው ባለ 43 ሜትር ቁመቱ የክርስቶስ ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በብራዚል ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ኤንካታዶ ከተማ የሚገነባው ባለ 43 ሜትር ቁመቱ የክርስቶስ ሐውልት በአገሪቷ ታዋቂውን የሪዮ ዴ ጄኒሮን ሐውልት ከመብለጡ ባሻገር በዓለም ላይ ሦስተኛው ረዥሙ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የሐውልቱን ጭንቅላት እና የተዘረጉ እጆች የሚሳየው ክፍል ገጠማ ባለፈው ሳምንት ተጠናቋል።

የግንባታው ሃሳብ ያመነጩት የከተማዋ ፖለቲከኛ አድሮአልዶ ኮናዛቲ ባሳለፍነው መጋቢት ወር ነበር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡት።

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ሐውልት 350 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጀት ተይዞላታል።

የክርስቶስ ወዳጆች የተሰኘው ማኅበር ለግንባታው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከግለሰቦች እና ከድርጅቶች እያሰባሰበ እንደሚገኝም ገልጿል።

ሐውልቱ ከአንደኛው እጅ ወደ ሌላኛው የእጅ ጫፍ ድረስ 36 ሜትር ሲረዝም ውስጥ ለውስጥ በሚገጠምለት የመጓጓዣ አሳንሰር ጎብኚዎችን እስከ ሐውልቱ ደረት ድረስ ይወስዳል። ይህም 40 ሜትር ከፍታ ሲኖረው ከተማዋን ለመጎብኘት ያስችላል ተብሏል።

ይህንን ሐውልት የሚበልጡት ሁለት የክርስቶስ ሐውልቶች በኢንዶኔዢያ እና በሆላንድ ይገኛሉ። በኢንዶኔዢያ የሚገኘው 'ቡንቱ ቡራኬ' የተሰኘው የክርቶስ ሐውልት 52.55 ሜትር የሚረዝም ሲሆን የሆላንዱ 'ክራይስት ዘ ኪንግ' የተሰኘው ደግሞ 52.5 ሜትር ይረዝማል።

በመላው ዓለም የድንግል ማሪያምን እና የቡድሃን ጨምሮ ከእነዚህ ሐውልቶች የሚረዝሙ በርካታ ሐይማኖታዊ ሐውልቶች ይገኛሉ።