በምሥራቅ ጎጃም በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ30 ሰዎች ህይወት አለፈ

በአማራ ክልል ውስጥ በምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ውስጥ ዛሬ፣ ሰኞ ጠዋት በደረሰ ከባድ የመኪና አደጋ የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።

አደጋው የደረሰው በዞኑ ውስጥ በሚገኘው በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ በቤዛ ብዙሃን ቀበሌ ልዩ ስሙ ቡሃች ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እንደሆነ የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር አይችሉህም ዳምጤ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የሞጣ ከተማ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የሐኪም ቤት ምንጮችን ጠቅሶ እንዳስታወቀው ቀደም ሲል 27 የነበረው የሟቾች ቁጥር ወደ 30 ከፍ ብሏል።

አደጋ የደረሰው ተጓዦችን አሳፍሮ ከደብረ ታቦር ከተማ በመነሳት ወደ አዲስ አበባ ሲያቀና በነበረ ዋሊያ አውቶብስና ከግንደ ወይን ወደ ሞጣ ይጓዝ በነበረ ቅጥቅጥ አይሱዙ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ መካከል በተፈጠረ ግጭት ነው።

አደጋው ዛሬ ሰኞ መጋቢት 6/2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት አካባቢ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ቡሃች ከተባለው ቦታ ላይ መድረሱን ኃላፊው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አደጋው የተከሰተው ሁለቱ ተሽከርካሪዎች መጓዝ ከነበረባቸው የመንገድ መስመር በተቃራኒ በሚሄዱበት ጊዜ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ከግጭቱ በኋላ አይሱዙው ከ150 ሜትር በላይ ከመንገድ ውጪ ወደ ገደል ተንከባሎ መግባቱ ተነግሯል።

በአደጋው ከሞቱት ሰዎች መካከል 23ቱ በአይሱዙ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ ሲሆኑ፣ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ የአደጋውን መድረስ ተከትሎ ለዕርዳታ በባጃጅ ተሽከርካሪ ተሳፍረው በቶሎ ለመድረስ ሲጓዙ ተሽከርካሪው ተገልብጦ ለህልፈት የተዳረጉ ናቸው።

አንደኛው ሟች ደግሞ በአገር አቋራጭ የዋሊያ አውቶብስ ውስጥ ተሳፋሪ የነበረ ግለሰብ ነው ተብሏል። ኋላ ላይ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች በአደጋው መሞታቸው ተገልጿል።

ከሟቾች በተጨማሪም በአደጋው ስድስት ሰዎች ከባድ አደጋ ደርሶባቸው ለህክምና ወደ ባሕር ዳር የተላኩ መሆኑን የገለፁት ምክትል ኮማንደር አይችሉህም፣ ሌሎች 17 ሰዎች ደግሞ በሞጣ ሆስፒታል ህክምና እያገኙ ነው ብለዋል።

ይህ ከባድ አደጋ የደረሰው ሁለቱም ተሽከርካሪዎች በኩርባ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ሲያሽከረክሩ መሆኑንም ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዜና ባለፈው ቅዳሜ በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ 51 ኩንታል እህልና 25 ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ መኪና ከሌሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ ተገልብጦ የ12 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ገልጾ ነበር።

በዚህም በሦሰት ቀናት ውስጥ ብቻ በሁለቱ የተሽከርካሪ አደጋዎች ምክንያት የ42 ሰዎች ህይወት ለህልፈት ተዳርጓል።

በኢትዮጵያ በሚደርስ የተሽከርካሪ አደጋ ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ህይወት እንደሚያልፍና የአካል ጉዳት እንደሚደርስ በየዓመቱ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በቅርቡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋዎችን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደጠቀሰው ያለፉት ስድስት ወራት በአገሪቱ ውስጥ 20 ሺህ 672 የመንገድ ትራፊክ አደጋዎች አጋጥመዋል።

በዚህም መሠረት ካለፈው ዓመት ከሐምሌ 1 ቀን 2012 እስከ ታኅሣስ 30/2013 ዓ.ም ድረስ በደረሱ አደጋዎች የ1 ሺህ 849 ሰዎች ህይወት አልፏል።

በስድስት ወራት ውስጥ በትራፊክ አደጋ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 2 ሺህ 646 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም 2 ሺህ 565 ዜጎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል እንደደረሰባቸው የፌደራል ፖሊስ ገልጿል።