በኢትዮጵያ በስድስት ወራት 1 ሺህ 849 ሰዎች በትራፊክ አደጋ መሞታቸው ተገለፀ

በኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ 20 ሺህ 672 የመንገድ ትራፊክ አደጋዎች ማጋጠማቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት የወንጀልና ትራፊክ መረጃ ትምበያ በዛሬው ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ እንዳሰፈረው ከሐምሌ 1 ቀን 2012 እስከ ታኅሣስ 30/2013 ዓ.ም ድረስ በደረሰው አደጋ 1 ሺህ 849 ሰዎች ሞተዋል ብሏል።

መረጃው የትምበያውን ተወካይ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር መስፍን አይተነውን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው ከሞቱት ሰዎች ባሻገር 2 ሺህ 646 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት፣ 2 ሺህ 565 ዜጎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ 495 ሚሊዮን 240 ሺህ 473 የሚገመት ንብረት መውደሙንም ኢንስፔክተሩ መግለፃቸው ሰፍሯል።

በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት የትራፊክ አደጋ መረጃ እንዳልደረሳቸው ኢንስፔክተር መስፍን አብራርተው ከዚያ ውጭ ያሉ ክልሎችን መሰረት አድርጎ የተጠናቀረ መሆኑን ተናግረዋል።

በስድስት ወር በአገሪቱ ከተመዘገቡት የትራፊክ አደጋዎች ውስጥ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 15 ሺህ 844 የትራፊክ አደጋ የደረሰ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ 192 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በ846 ሰዎች ላይ ከባድና በ512 ቀላል ጉዳት መድረሱንም ከመረጃው መረዳት ተችሏል።

ለእነዚህ አደጋዎች ምክንያት ብለው ኢንስፔክተር መስፍን በዋነኝነት የጠቀሷቸው የአሽከርካሪዎች ሥነ ምግባር ጉድለት፣ ቸልተኝነትና ብቃት ማነስ፤ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት፣ ወቅቱን የጠበቀ የቦሎ እድሳት አለማድረግ፣ የመንገድ ግንባታ ችግርና የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ችግር ናቸው።

"በሰዎች ህይወት፣በአካል እና በንብረት ላይ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋን መከላከልና መቀነስ እንዲቻል ሁሉም አሽከርካሪዎችና ግረኞች የትራፊክ ህግን አክብሮ በመንቀሳቀስ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው" በማለት ኢንስፔክተሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።