ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሚያንማሯ ፕሬዝዳንት ሳን ሱ ቺ 600 ሺህ ዶላርና ወርቅ በመውሰድ ተወነጀሉ
የሚያንማር ጦር ኃይል አመራሮች ከሥልጣን የተወገዱት ፕሬዝዳንት ሳን ሱ ቺ በሕገወጥ መንገድ 600 ሺህ ዶላር ተቀብለዋል ሲሉ ወነጀሉ።
ፕሬዝዳንቷ በፈረንጆቹ የካቲት 1 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ከቀረቡባቸው ውንጀላዎች በሙሉ ይህኛው ጠንካራ ነው ተብሏል።
ጦር ኃይሉ ለውንጀላው ማስረጃ አላቀረበም።
ብርጋዴር ጄነራል ዛው ሚን ቱን፣ ዊን ሚንት እና ሌሎች ሚኒስተሮችን በሙስና ወንጅለዋል።
የሳን ሱ ቺ ፓርቲ ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ ባለፈው ዓመት የተደረገውን አገራዊ ምርጫ በአብላጫ ድምጽ ማሸነፉ ይታወሳል።
የሚያንማር ወታደራዊ ኃይል አመራሮች ግን ምርጫው የተጭበረበረ ነው ሲሉ አስታውቋል።
ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የጦር ኃይሉን የተጭበረበረ ምርጫ ነው የሚል ክስ የሞገቱ ሲሆን ምንም የታየ ስህተት የለም ብለዋል።
ሳን ሱ ቺ ላለፉት አምስት ሳምንታት በወታደራዊ ኃይሉ ቁጥጥር ስር ቢሆኑም ያሉበት ስፍራ ግን እስካሁን ድረስ አይታወቅም።
ወታደራዊ ባለሥልጣናት በሳን ሱ ቺ ላይ "ፍርሃትና ሥጋት በመቀስቃስ"፣ በሕገወጥ መንገድ የሬዲዮ መሳሪያዎችን በመያዝ እና የኮቪድ-19 እገዳዎችን በመጣስ ክሶች መስርተውባቸዋል።
እስካሁን ድረስ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ሐሙስ ዕለት የተሰማው ሕገወጥ ገንዘብ መቀበል ትልቁ ነው።
ሳን ሱ ቺ ተቀብለውታል የተባለው ወርቅ በገንዘብ ሲሰላ 450 ሺህ ፓውንድ ይሆናል ተብሏል።
ሚያንማር ሳን ሱ ቺ በቁጥጥር ስር ውለው ወታደሩ ሥልጣንን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በጎዳና ላይ ነውጦች እየታመሰች ትገኛለች።
ሐሙስ ዕለት ብቻ ሰባት ተቃዋሚ ሰልፈኞች መገደላቸውን ተከትሎ የሟቾች ቁጥር 60 ደርሷል።
የዓይን ምስክሮች እንደሚሉት የተወሰኑ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የሞቱት ግንባራቸውን በጥይት ተመተው ነው ።
የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና ሌሎች አገራት የተቃዋሚ ሰልፈኞቹን ግድያ ያወገዙ ሲሆን ባለስልጣናቱም ከኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ግን የቀረበበትን ውንጀላ በሙሉ አጣጥሎ ጥፋቱ በሙሉ የሱ ቺ ነው ብሏል።