ለሜጋንና ሃሪ መጠለያና ጥበቃ የሰጠው ጥቁሩ ቢሊየነር ማነው?

የሰሴክስ ዱክና ደችስ በመባል የሚታወቁት ሜጋንና ሃሪ ከሰሞኑ በሰጡት ቃለ ምልልስ አነጋጋሪ ሆነዋል።

ጥንዶቹ ከአሜሪካዊቷ ጉምቱ የቴሌቪዥን ሴት ኦፕራ ዊንፍሬይ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከዩናይትድ ኪንግደም ንጉሣዊ ቤተሰብ ለምን ራሳቸውን ማግለል እንዳስፈለጋቸውና ሌሎችንም ምስጢሮች አውጥተዋል።

ባልና ሚስት በቃለ-ምልልሳቸው ንጉሣዊው ቤተሰብ የገንዘብ ድጎማ ሲያቋርጥባቸው አሜሪካዊው ባለሃብትና የሲኒማ ሰው ታይለር ፔሪ ቤትና ጥበቃ እንደመደበላቸው ተናግረዋል።

ለመሆኑ ታይለር ፔሪ ማነው? እንዴትስ ስኬታማ ሊሆን ቻለ?

የ51 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ፊልም ሠሪ፣ ኮመዲያን፣ ተዋናይ፣ አዘጋጅ እንዲሁም ፀሐፊ ነው።

ፔሪ የሠራቸው ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በተለይ በጥቁር አሜሪካዊያን ዘንድ እውቅናና ክብር አትርፈውለታል።

በተለይ ደግሞ ማደያ የተሰኘውን ፊልም በመፃፍ፣ በማዘጋጀት እንዲሁም በመተወን ይታወቃል።

ታይለር ፔሪ በዚህ ፊልም ላይ አንዲት ጥቁር አያትን ሆኖ ይተውናል።

በፈረንጆቹ 2015 134 ሄክታር ስፋት ያለው የፊልም ስቱዲዮ በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ በመገንባት ከተማዋን የፊልም መናገሻ ለማድረግ ችሏል።

ከዚህ ስቱዲዮ ግንባታ አንድ ዓመት በኋላ ፔሪ ቢሊየነር መሆኑን ፎርብስ መፅሔት አስታወቀ።

ታይለር ፔሪ ከጥቂት ወራት በፊት ከረዥም ጊዜ ፍቅረኛውና ከአንድ ልጁ እናት ገሊላ በቀለ ጋር መለያየቱን አሳውቆ ነበር።

ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊቷ ገሊላ በቀለና ታይለር ፔሪ ልጃቸውን አማን ታይለር ፔሪ ብለው መሰየማቸው አይዘነጋም።

ታይለር ከፍቅረኛው ጋር ከተለያየ በኋላ "አሁን 51 ዓመቴ ነው። የፍቅር ጓደኛም የለኝም። በቀጣይ ምን እንደማደርግ ባለውቅም እግዚአብሔር ከጎኔ እንደሆነ አልጠራጠርም። መልካም አባት መሆኔን እቀጥላለሁ። ቀና ብዬ ማድረግ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ" ብሎ ነበር።

ታይለር በኢንስታግራም ገፁ ባጋራው መልዕክት ላይ አክሎ "በዚህ ሃዘን በሞላው ዓለም እባካችሁ መልካም መሆን ሻቱ" ብሎ ፅፎ ነበር።

ፔሪ፤ ሃሪና ሜጋንን እንዴት ረዳቸው?

ሜጋንና ሃሪ ዩናይትድ ኪንግደምን ለቀው ሲወጡ ወደ ካናዳ ነበር ያመሩት። ነገር ግን በ2020 ወደ አሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ሄዱ።

በዚህ ወቅት ነው ታይለር ፔሪ ሆሊውድ ውስጥ ካሉት 'ፈረስ የሚያስጋልቡ' ቤቶቹ መካከል አንዱን ከነጥበቃው [በነፃ እንደሆነ የተዘገበ] ለጥንዶቹ የሰጠው።

ጥንዶቹ ሁለት ሰዓት በፈጀው ቃለ-ምልልሳቸው ነው ይህን ይፋ ያደረጉት።

ሃሪና ሜጋን ከካናዳዋ ቫንኩቨር አይላንድ ለቀው የወጡት የሚኖሩበት ቤት አድራሻ በመታወቁ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ለቀን ስንወጣ ምንም ዕቅድ አልነበረንም" ብላለች ሜጋን በቃለ-ምልልሱ።

"ቤት ያስፈልገን ነበር እሱ [ታይለር ፔሪ] ቤት ሰጠን፤ ጥበቃም እንዲሁ። ቀጣይ ምን እናድርግ የሚለውን እስክናሰላስል ድረስ እፎይታን ሰጥቶን ነበር።"

"ካናዳ የሰው ቤት እያለን ትልቁ ጭንቀታችን የነበረው ድንገት ሳናስበው ከዚህ በኋላ ጥበቃ የላችሁም መባላችን ነበር" በሏል ሃሪ።

ሃሪና ሜጋን ከቆይታ በኋላ ካሊፎርኒያ ውስጥ ሞንቴሲቶ የሚባል ሥፍራ ቤት ገዝተው ለመኖር መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል።