ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዘጠኝ ዓመቱ የመናዊ ዓይነ ሥውር መምህር
በየመን ታኢዝ፣ በመንግሥት እና በሁቲ አማፂያን መካከል በተደረገ ጦርነት በፈራረሱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በርካታ ህጻናት ይማራሉ።
የዘጠኝ ዓመቱ ዓይነ ሥውር ተማሪ መምህራኖቹ በቀሩ ወቅት የክፍል ጓደኞቹን በማስተማር ይረዳል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ሕጻናት ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከሆነ በየመን ከአምስት ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በጦርነቱ በደረሰበት ጉዳት ከጥቅም ውጪ ሆኗል።
በአውሮፓውያኑ 2015 የሁቲ አማጺያን አብዛኛውን የአገሪቱን ምዕራባዊ ክፍል መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የመን በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ትገኛለች።
የእርስ በርስ ጦርነቱም በዓለም ላይ ከፍተኛው የተባለውን የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። ጦርነቱን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ሕይወታቸው አልፏል።
ይህ ዓይነ ሥውሩ ተማሪ የሚማርበት ትምህርት ቤት ምንም እንኳ በጦርነቱ ምክንያት ቢፈራርስም መምህራኖቹ የአካባቢው ልጆች ከትምህርት ገበታ እነዳይርቁ በማሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል።
በዚህ በጦርነት ክፉኛ በተጎዳ ትምህርት ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ሊማሩ ይመጣሉ።
መምህራኖቹ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ደሞዝ አይከፈላቸውም።
መምህራኖች በማይመጡበት ወቅት የዘጠኝ ዓመቱ አህመድ መምህራኖቹን ተክቶ ያስተምራል።
"አስቀድሜ ያጠናሁትን ነው የማስተምራቸው" የሚለው አህመድ ከማይከብዱት የትምህርት አይነቶች መካከል ቁርዓንና ሳይንስ እንደሚያስተምር ይናገራል።
አህመድ ከተወለደ ጀምሮ ዓይነ ሥውር ነው።
"አዲስ ትምህርት ቤት፣ መቀመጫ ወንበር፣ በሮች፣ መስኮቶች፣ ጥቁር ሰሌዳ እንፈልጋለን።
"የትምህርት ቤቱ ጣርያ ዳግም መገንባት ያስፈልገዋል። እንደዚያ ከሆነ ዝናብ ሲዘንብ አይንጠባጠብብንም። ከቀኑ ፀሀይ የሚከላከል መስኮት ንፋሱን የሚያግድ በርም እንፈልጋለን" ብሏል አህመድ።
ትምህርት ቤቱ እኤአ በ2016 አካባቢው በሁቲ አማፂያን እጅ ሲወድቅ ትምህርት መስጠት አቁሞ ነበር።
የመንግሥት ወታደሮች አማፂያኑን ከስፍራው እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ ዳግም ሥራ ጀምሯል።
አሁንም ትምህርት ቤቱ ጋር ተኩኖ ከርቀት የሚካሄደው ጦርነት ይሰማል።
አህመድ ይህንን የጦርነት ድምጽ ሲሰማ የሚሞት እንደሚመስለው ይናገራል።
ሌላኛዋ የትምህርት ቤቱ ተማሪ የሆነችው ኻሉድ ሁሌም አደጋ ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ፣ "ተባራሪ ጥይት ይመታናል ብለን እንፈራለን፣ የተቀበረ ፈንጂም ይኖራል በሚል እንሰጋለን" ብላለች።
ወደ ትምህርት ቤቱ በስጋት መጥተው፣ በስጋት ተምረው፣ በስጋት ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱ አክላ ታስረዳለች።
"ወደ ትምህርት ቤት የምንመጣው ጓደኞቻችንን ለማግኘትና ለመማር ነው" ስትል የምታስረዳው ኻሉዳ "ፈጣሪ እንደፈቀደ ዶክተር አልያም የሆነ ነገር እንሆናለን" ስትል ተስፋዋን ትገልጻለች።
በመጨረሻም "ጦርነቱ እንዲያበቃ እንፈልጋለን" በማለት "በጦርነት ወቅት ዘና ማለት አይቻልም" ብላለች።