እስራኤል በመርከቧ ላይ ለተፈጸመው የፈንጂ ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አደረገች

ሔሊዮስ ሬይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሔሊዮስ ሬይ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ባለፈው ሳምንት በኦማን ባሕረ ሰላጤ በፈንጂ ጉዳት ለደረሰባት የአገራቸው መርከብ ኢራንን ተጠያቂ አደረጉ።

ሔሊዮስ ሬይ የተባለችው የእስራኤል የጭነት መርከብ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሴንጋፖር በመጓዝ ላይ በነበረበት ጊዜ ነው ባሕር ላይ በተጠመደ ፈንጂ ጉዳት የተደረሰባት።

"ይህ በእርግጥም በኢራን የተፈጸመ ግልጽ ጥቃት ነው" ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ካን በተባለው ሬዲዮ ላይ ተናግረዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን የእስራኤልን ውንጀላ በጽኑ ተቃውሞታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ንግግር የተላለፈው እስራኤል ሶሪያ ውስጥ ያሉ የኢራን ኃይሎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ፈጽማለች ሲል አንድ ተቆጣጣሪ ቡድን ሪፖርት ካደረገ ከሰዓታት በኋላ ነበር።

ባለፈው ሐሙስ ጉዳት ያደረሰው ፍንዳታ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ ያልሆ ሲሆን፤ የመርከቧ ባለቤት ግን ፍንዳታው በመርከቧ አካል ሁለት ቦታዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ቀዳዳ መፍጠሩን ገልጸዋል።

የእስራኤል ካቢኔ ሚኒስትር የሆኑት ዮአን ጋላንት ለአንድ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፤ በመርከቧ ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ፎቶዎች እንደሚያመለክቱት "በባሕር ኃይል ኮማንዶዎች ምሽት ላይ በመርከቧ ውጫዊ ክፍል ላይ ፈንጂ እንደተጠመደ ያመለክታሉ" ብለዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም ጥቃቱ የተፈጸመው ከኢራን የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ ሲሆን መርከቧም የእስራኤል ንብረት መሆኗን በተመለከተ ለሕዝብ ክፍት ከሆኑ መረጃዎች ማግኘት ይቻላል ብለዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ኢራን በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ በበርካታ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ከተፈጸሙ የፈንጂ ጥቃቶች ጀርባ አለች ተብላ ስትከሰስ ቆይታለች። የአሜሪካ ጦር ሠራዊት እንዳለው ፍንዳታዎቹ የተፈጸሙት በመርከቦቹ አካል ላይ በማግኔት አማካይነት በተለጠፉ ፈንጂዎች አማካይነት ነው።

ኢራን ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጋር ምንም የሚያገናኛት ነገር እንደሌለ ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፤ ዛሬ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰነዘሩትን ክስም ውድቅ አድርጋዋለች።