ኮሮናቫይረስ: እስራኤል የፋይዘር ክትባት ውጤታማ ሆኖ ማግኘቷን ገለፀች

ከእስራኤል የክትባት መርሃ ግብር የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የፋይዘር ክትባት የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን 94 በመቶ የመከላከል አቅም አለው።

ይህም ክትባቱ በክሊኒክ ውስጥ በተደረጉለት ሙከራዎች ወቅት የነበረውን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ባለው ህዝብ ውስጥም ውጤታማ መሆኑን ያሳያል፡፡

በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ከፍተኛ ውጤታማነት እያስገኘ መሆኑን የማህበረሰብ ጤና ሐኪሙ ፕሮፌሰር ሀጋይ ሌቪን ተናግረዋል።

"በጣም ተጋላጭ ለሆኑት ቡድኖች ከፍተኛ የክትባት ሽፋን መስጠት ወሳኝ" ነበር ብለዋል፡፡

የእስራኤል ትልቁ የጤና ፈንድ ክላሊት በተመሳሰይ ዕድሜ እና የጤና ሁኔታ በሚገኙ 600,000 ክትባት በወሰዱ ሰዎች ላይ መልካም የሚባል ውጤት መገኘቱን፣ ክትባት ካልወሰዱ ሰዎች አንጻር እንደታየባቸው አመልክቷል፡፡

ክትባቱን በወሰዱት ዘንድ 94% ያነሰ ኢንፌክሽኖችን አግኝቷል፡፡

በተጨማሪም ክትባቱ ሁሉንም ማለት በሚቻል ሁኔታ ከባድ ህመሞችን ተከላክሏል፡፡

ውጤቱ ከ70 ዎቹ በላይ የሆኑትን ጨምሮ በሁሉም የዕድሜ ቡድኖች ውስጥ ተመሳሳይ ነበር፡፡

ይህ "እንደ እንግሊዝ ላሉት ሌሎች ሀገሮች" ስለ ክትባቱ ጠቃሚ መልዕክት ከማስተላለፉም በተጨማሪ፣ በቫይረሱ በጣም ሊታመሙ የሚችሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች "በከፍተኛ" ሁኔታ ክትባቱን እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል ፕሮፌሰር ሌቪን፡፡

ፕሮፌሰሩ አክለውም የእንቅስቃሴ ገደቦችን ከማላላት በፊት ምን ያህል ቁጥር መከተብ እንደሚያስፈልግ መናገር አልችልም ብለዋል፡፡

"በመተላለፍ ላይ ያለው ተጽዕኖ ምን እንደሆነ እስካሁን አናውቅም" ብለዋል፡፡

ሆኖም ቢያንስ "ክትባቱ ግለሰብን ለመጠበቅ ጠቃሚ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡

የእስራኤል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃን በመተንተን ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር ኤራን ሴጋል በበኩላቸው ክትባቱ በኮቪድ -19 ጉዳዮች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመረዳት ሃገሪቱ ዕድሜያቸው ከ60ዎቹ በላይ ከሆኑት መካከል 80 በመቶውን መከተብ እንዳለባት ጠቁመዋል፡፡

እስራኤል የክትባት መርሃግብሩ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመመልከት በዓለም ላይ የመጀመሪያዋ ሀገር ብትሆንም፣ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ የሆነ ህዝብን ማዳረስ እና በርካታ ሳምንታትን ሊፈጅባት ይችላል፡፡

በመጀመሪያ ክትባት በተወሰዱ እና ዕድሜያቸው ከ60ዎቹ በላይ በሆናቸው እና ከዚያ ቀደም ነዋሪዎቻቸውን ባስከተቡ ከተሞች ውስጥ የቫይረሱ ስርጭት ሲቀንስ ታይቷል። ይህም ቀደም ባሉት የእንቅስቃሴ ገደቦች ወቅት ያልታየ ነው ተብሏል፡፡ ይህም ከእገዳው ይልቅ ክትባቱ ለቁጥሩ መቀነስ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠንካራ ማስረጃ ይሰጣል፡፡

ፕሮፌሰር ሴጋል እንደሚያስጠነቀቁት ከሆነ ቁጥሩ ከሚጠበቀው በላይ በዝግታ የቀነሰ ሲሆን ምናልባትም በእስራኤል ውስጥ ዋነኛው የቫይረሱ ዝርያ በሆነው እና በብሪታንያ በተገኘው የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

"በጣም ፈጣን" በሆነው በእስራኤል የክትባት መርሃ ግብር እንኳን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊከላከሉት የማይችሉ ሲሆን በበሽታው ከተያዙም በጠና ሊታመሙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

"አሁንም ቢሆን ከእንቅስቃሴ እገዳው ለመውጣት በጥንቃቄ መውጣት አለብን" ወይም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሆስፒታል መተኛት ሊገደዱ ይችላሉ ይላሉ፡

እስራኤል ከፍተኛ የሆነ የኢንፌክሽን ማዕበል እያጋጠማት እና በጥብቅ እገዳዎች ውስጥ ብትቆይም ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉ የመከተብ መብት ስላላቸው ትምህርት ቤቶች የመከፈት ተስፋ አላቸው ተብሏል፡፡

በፍልስጤም ግዛቶች ክትባቱን ማን መስጠት አለበት በሚለው ጥያቄ ሃገሪቱ ትችት ደርሶባታል፡፡

ለጤና ሠራተኞች እንዲደርስ እስራኤል በዌስት ባንክ እና በጋዛ ላሉት ፍልስጤሞች የተወሰነ መጠን ያለው ክትባት ማሳለፍ የጀመረችው ገና አሁን ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከነዋሪዎቿ ለሩብ ያህሉ ሁለቱንም ዙር ክትባት ሰጥታለች፡፡