ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተባበሩት መንግስታት በትግራይ 'ከፍተኛ ወንጀሎች' ተፈጽመው ሊሆን ይችላል አለ
ትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ወንጀሎች የመፈጸማቸው እድል ከፍተኛ እንደሆነና ኢትዮጵያ በአፋጣኝ እርምጃ የማትወስድ ከሆነ ነገሮች ከዚህም እየባሱ ሊሄዱ እንደሚችሉ አንድ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ኃላፊ አስጠንቀቁ።
በተባሩት መንግስታት ልዩ የዘር ማጥፋት አማካሪ ሆኑት አሊስ ዋይሪሙ ንዴሪቱ እንዳሉት በትግራይ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ሪፖርቶች ደርሷቸዋል።
'' እያወራን ያለነው ስለትግራይ ክልል ብቻም አይደለም። ምንም እንኳን በክልሉ አሁንም ድረስ ጦርነት እየተካሄደ ቢሆንም በሌሎች አካበቢዎችም የመብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ሪፖርቶች ደርሰውናል'' ብለዋል ልዩ አማካሪዋ።
''እንዲህ አይነት ወንጀሎች በአንድ ቀን የሚፈጸሙ አይደሉም። በርካታ ስር የሰደዱ ምክንያቶች አሉ፤ ነገሮች እየተከናወኑ ያሉበት አካሄድም አለ። በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያደርግ የምንፈልገው የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብርና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ተካሂዶ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ነው።''
ልዩ አማካሪዋ ከቢቢሲ ኒውስደይ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ተፈጽመዋል ተብሎ ከቀረቡላቸው ወንጀሎች መካከል አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ፣ የንብረት ውድመት፣ ስም ማጥፋትና ግድያ በዋነኛነት የሚጠቀሱ መሆናቸው ገልጸዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የተባበሩት መንስታት ዋና ጸሀፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆኑ በፊት ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እንዲገገቡ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ማለቱ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፤ በትግራይ ያደረጉትን ጉብኝት ከቀናት በፊት ሲያጠናቅቁ በክልሉ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ መግለጫ ሰጥተው ነበር።
በተያያዘ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በፕሮጄክት ሲንዲኬት ላይ በጻፉት እና ከሁለት ቀናት በፊት በታተመው ጽሑፋቸው፤ በትግራይ እና በመላው አገሪቱ በሰዎች ላይ የሚደርሱ ስቃዮችን መቀነስ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተባበሩት መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በትግራይ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚንሰትሩ በጽሑፋቸው በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እና በክልሉ ሕይወት ወደ ቀደመ ሁኔታ እንዲመለስ አስተዳደራቸው "ቀን እና ለሊት" እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰብዓዊ እርዳታውን በማቅረብ ሥራ ላይ "በሕወሓት ኃይሎች ሆነ ተብሎ እንዲቋረጥ የተደረገው የኮሚኒኬሽን ግንኙነት" ለአስተዳደራቸው ፈተና ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመልሶ ግንባታው ላይ ከፍተኛ ትብብር ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።