ትግራይ ፡ የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ትግራይ ገቡ

የዓለም ምግብ ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው ሰዎች ድጋፍ ለማድረስ ከስምምነት መድረሳቸው ተገለጸ።

በተባባሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና እርሳቸው የሚመሩት ድርጅት በመላው ትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከስምምነት መድረሱን አስታውቀዋል።

ዴቪድ ቢዝሊይ "በትግራይ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ የእኛን አስቸኳይ እርዳታ ይሻል። የምናባክነው ጊዜ የለም" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

በትግራይ የሚገኙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዓለም ምግብ ድርጅት 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ ለመርዳት 20 ሺህ ቶን ምግብ በመላው ትግራይ እያሰራጨ መሆኑን በተንቀሳቃሽ ምስል አስደግፈው አሳይተዋል።

በተያያዘ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በፕሮጄክት ሲንዲኬት ላይ በጻፉት እና ከሁለት ቀናት በፊት በታተመው ጽሑፋቸው፤ በትግራይ እና በመላው አገሪቱ በሰዎች ላይ የሚደርሱ ስቃዮችን መቀነስ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተባበሩት መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በትግራይ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚንሰትሩ በጽሑፋቸው በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እና በክልሉ ሕይወት ወደ ቀደመ ሁኔታ እንዲመለስ አስተዳደራቸው "ቀን እና ለሊት" እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰብዓዊ እርዳታውን በማቅረብ ሥራ ላይ "በሕወሓት ኃይሎች ሆነ ተብሎ እንዲቋረጥ የተደረው የኮሚኒኬሽን ግንኙነት" ለአስተዳደራቸው ፈተና ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመልሶ ግንባታው ላይ ከፍተኛ ትብብር ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።

"በትግራይ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው"

የተባባሩት መንግሥታት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ማለቱ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፤ በትግራይ ያደረጉትን ጉብኝነት ከቀናት በፊት ሲያጠናቅቁ በክልሉ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በተመሳሳይ የኖርዌጂያን ሪፊውጂ ካውንስል (ኤንአርሲ) ዋና ጸሀፊ ጃን ኢግላንድ በትግራይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እያገኙ አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ክልል እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን መሆኑን እና ለእነዚህም ዜጎች አስፈላጊ የሆነ እርዳታ ለማድረስ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ሲያስታውቅ ነበር።

የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራአመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ "በትግራይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውሰዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ሳይሆን 2.5 ሚሊዮን ነው" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ፤ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ለመርዳት መንግሥት በቂ ዝግጅት አድርጓልም ብለዋል።