አስተያየት፡ ከኢትዮጵያ እስከ የመን፡ ረሃብ ተከስቷል ብሎ የማወጅ ፈታኝነት

    • ፀሐፊ, አሌክስ ዲ ዋል
    • የሥራ ድርሻ, የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በክልሉ ረሃብ ተከስቷል የሚሉ በርካታ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።

በባለፈው ሳምንት ረቡዕ በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ እየከፋ እንደሆነና በአሁንም ወቅት በግጭቱ ለተጎዱ ነዋሪዎች እርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልፀዋል።

በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ እንዲሁ ይህንኑ ድርጅት ይመሩ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ዋና ፀሃፊ የሆኑት ጃን ኢግላንድ "በረድዔት ድርጅቶች በሰራሁባቸው አመታት እንዲህ ያለ የተንጓተተ አሰራር አይቼ አላውቅም። በአፋጣኝ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታውን ማድረስ አስቸጋሪ ሆኗል፤ ረዥም ጊዜ እየወሰደ ነው" በማለት አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

ጃን ኢግላንድ አክለውም "አጠቃላይ የረድዔት ድርጅቶች የችግሩን ክብደት አጉልተው አለማሳየቻው ውድቀት ነው" ብለዋል።

በሌላ ቋንቋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን ሁኔታ "ረሃብ ተከስቷል" ይለዋል፤ ከሆነስ ወቅቱ መቼ ይሆን?

በግጭት በተጎዳችው ትግራይ፣ ያለው የግብርና ሁኔታ ከዚህ ቀደምም ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም በባለፈው አመት ደግሞ የተከሰተው የአንበጣ ወረርሽኝ ሁኔታውን አክፍቶታል።

በመስከረም ወር ላይ በነበረው አለም አቀፍ የምግብ ደህንነት ግምገማ መሰረት ከክልሉ 7 ሚሊዮን ነዋሪዎች 1.6 ሚሊዮኑ ያህሉ በረድዔት እርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ ነበሩ ተብሏል።

በፌደራል መንግሥቱና በህወሃት መካከል የነበረው የግንኙነት መሻከር ወደማይታረቅ ደረጃ ላይ ደርሶ በክልሉ የነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅሟል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወታደራዊ ዘመቻ ማወጃቸው የሚታወስ ነው። ግጭቱም የተነሳው ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም ነው።

ለአመታት ገዢ የነበረውን ኢህአዴግን በማፍረስ ውህድ ፓርቲ መፈጠሩን ህወሃት ተቃውሞ ነበር። በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሃት መካከል የነበረውን ቅራኔ አስፍቶታል።

ቅራኔውም ወደ ወታደራዊ ግጭት አምርቶ አሁን ያለውን መልክ ይዟል።

በዚህ ጦርነት ላይ የኤርትራ ሰራዊት ተሳትፈዋል የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል። በቅርቡም አሜሪካን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ለሳምንታት ሲባል የነበረውንና የኤርትራ ጦር በክልሉን መኖሩን አምነዋል።

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) መጠየቁ ይታወሳል። የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት በተደጋጋሚ የኤርትራ ጦር አልተሳተፉም በማለት ይናገራሉ።

በክልሉ አብዛኛው ክፍል አሁንም ቢሆን የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖሩን ተከትሎ ከአለም ጋር ተቆራርጦ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት የረድዔት ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን እየላኩ ሲሆን በክልሉ የሆነውና እየሆነ ያለውን ነገር ይረብሻል እያሉ ነው። ሆሰፒታሎች ተዘርፈዋል፣ መዳን በሚችሉ በሽታዎችና ረሃብ ምክንያት ነዋሪዎች መሞታቸው፣ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ምግብም ሆነ ገንዘብ ለማግኘት አለመቻላቸው በፍራቻ እንዲዋጡ አድርጓቸዋል የሚሉ ዜናዎች እየተሰሙ ነው።

ስልክ ማግኘት የቻሉ የትግራይ ነዋሪዎች መጠነ ሰፊ የሆነ ዘረፋ፣ የእህል መቃጠልና መውደም እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ሊደርሳቸው አለመቻሉን ይናገራሉ።

ከሰሞኑም በክልሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሊሞቱ እንደሚችሉ አንድ የመንግሥት ባለስልጣን ማስጠንቀቃቸውን ከረድዔት ድርጅቶችና ከተባበሩት መንግሥታት ሰራተኞች ጋር ታህሳስ 30፣ 2013 ዓ.ም ከተደረገ ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ፅሁፍ አመላክቷል።

በዚሁ ሪፖርት መሰረት በችግሩ ተጠቂ ከሆኑት መካከል 99 በመቶ መድረስ አልተቻለም ተብሏል። በረድዔት ድርጅቶች መረጃ መስረት በክልሉ 4.5 ሚሊዮን ህዝብ፣ 60 በመቶ የሚሸፍነው ህዝብ በግጭቱ ተጎድቷል፤ እርዳታም ያስፈልገዋል ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ አኃዙ የተጋነነ ነው በማለት ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ በቁጥጥር እንዳዋለው ይናገራል። እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች 2.5 ሚሊዮን እንደሆኑና ሁሉንም በሚባል ሁኔታ መድረስ እንደተቻለም አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ረሃብ የመካድ ታሪክ

በዚህ ረሃብ ሊከሰት ይችላል በሚሉ ሪፖርቶች በተጥለቀለቁበት መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት ዋነኛ ለጋሹን የአውሮፓ ህብረትን ለትግራይ ድንገተኛ እርዳታ ማድረስ ችግር ጊዜያዊ ነው፤ ህብረቱ ለአገሪቷ የሚሰጠውን የልማት እርዳታ ሊቀጥልበት ይገባል ይላል።

ህብረቱ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የ107 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍን የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ያለ አንዳች ገደብ ዕርዳታ ማቅረብ እስኪችሉ ድረስ አግዷል።

ከዚህ ቀደም ህብረቱ ለኢትዮጵያ ከመደበው የበጀት ድጋፍ ውስጥ 90 ሚሊዮን ዩሮ (110 ሚሊዮን ዶላር) እንዲዘገይ ያሳለፈው ውሳኔ በተመለከተ እርምጃው በተሳሳተ ግምገማ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል ቅሬታውን መግለፁ የሚታወስ ነው።

ሆኖም የኢትዮጵያ መሪዎች ረሃብን የመደበቅ ታሪክ አላቸው።

በአውሮፓውያኑ 1973 የጆናታን ዲምቢልቢ ፊልም አገሪቷ ያጋጠማትን መጠነ ሰፊ ረሃብ ከማጋለጥ በተጨማሪ በወቅቱ መሪ በነበሩት አፄ ኃይለ ስላሴ የረሃቡ አስከፊነት ከአለም እንዴት እንደተደበቀ አሳየ። በረሃቡም 200 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል።

ያ ሁሉ ህዝብ በተራበበት ወቅት ንጉሱ ያሳዩት ቸልተኝነት እንዲሁም ቅንጡ ህይወት መቀጠል በርካቶችን ወደ ጎዳና አውጥቷል። መዘዙ ስማቸውን ከማጉደፍ በላይ በቀጣዩ አመት ለውድቀታቸውና የስልጣን ማክተሚያቸው ምክንያት ሆነ።

በ1977 ትግራይና ወሎ የሌላ ረሃብ ማዕከል ነበሩ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በየጊዜው የሚከሰተው ድርቅና በተጨማሪ ጦርነት ነበር። በዚህ ዘግናኝ ረሃብም ከ600 ሺህ- 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል።

በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመራ የነበረው የደርግ መንግሥት ረሃብ አልተከሰተም በማለት ቢፀናም በሚካኤል በርክና መሃመድ አሚን ይመራ የነበረው የቢቢሲ ፊልም ቡድን ያለውን አሰቃቂ ሁኔታ አጋልጦታል።

የረሃቡ ዜና ታዋቂው ሙዚቀኛ ቦብ ጌልዶፍ 'ዱ ዜይ ኖው ኢትስ ክሪስማስ' የሚለውን ዘፈኑን እንዲሰራ መነሻ ነበር። አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለእርዳታ እንዲነሳ በከፍተኛ ሁኔታ ቀስቅሷል።

ረሃቡ የወታደራዊውን መንግሥት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በአገር ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጭ ስማቸው እንዲጎድፍ አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የረሃብና የችጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆና መሳሏ ኢትጵያውን በሌላው አለም ዘንድ ለማኝ ሆነው መታየታቸው አስከፋቸው።

በአውሮፓውያኑ 2001 እንዲሁ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ዘመን በአገሪቱ ደቡባዊ ምስራቅ ክፍል ረሃብ ተከስቷል የሚለው አወዛጋቢ ጉዳይ ነበር። በአካባቢው አማፂ ቡድን ጋር መንግሥት እየተፋለመ የነበረበት ወቅት ሲሆን ከ20 ሺህ-25 ሺህ ሰዎች መንግሥት " አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ" ብሎ በጠራው ችግር ጋር በተያያዘ ህይወታቸው አልፏል።

በባለፉት አስርት አመታት የአለም አቀፉ ረድዔትና የሰብዓዊው ስርዓት መጠነ ሰፊ ሆኗል፤ በበለጠ የተደራጀ መልክ ይዟል።

በአህጉሪቷ ከህፃናት የተመጣጠነ (አልሚ) ምግብ ቁጥጥርና፣ ምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የተራቀቀ ስርዓት የተዘረጋ ሲሆን ይሄም የምግብ እጥረት ሲያጋጥም ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንዲኖረውና ረሃብ እንዳይከሰት ለመከላከል በወጠነ መልኩ ነው እየተሰራበት ያለው።

ከአምስት አመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥትና የውጭ ለጋሾች በአገሪቷ ላጋጠመው ብሄራዊ ድርቅ ምላሽ በመስጠት 10.2 ሚሊዮን ህዝብ አስፈላጊው እርዳታ እንዲደርሳቸው አድርገዋል።

እንደ ቀድሞው ረሃብ ሲከሰት ምግብ ማደል ሳይሆን ነዋሪዎች ያላቸውን ከብት፣ በግና ሌሎች እንስሳቶች ከመሸጣቸው በፊት እርዳታው በየመንደራቸው እንዲደርስ ሆኖ ስርዓቱ ተዋቅሯል።

አርሶ አደሮቹ ችግራቸው ተቀርፎ በቀጣዩ አመት መሬታቸው ላይ እህል እንዲዘሩና እንዳይሰደዱ አስችሏል።

ነገር ግን በ2015-2016 የተከሰተው አፋጣኝ እርዳታና በአሁኑ ወቅት ያለውን የሚለዩዋቸው ሁለት አንኳር ነጥቦች አሉ፤ መረጃና ፖለቲካ።

በአሁኑ ወቅት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረሃብ ተከስቷል ብሎ ለማወጅ በቂ መረጃ የለም።

ከ15 አመታት በፊት የረድዔትና የሰብዓዊ ጉዳይ ሰራተኞች የምግብ ደህንነት መጓደልን ለመለካት በተባበሩት መንግሥታት የተደገፈ ደረጃውን የጠበቀ መለኪያን ሰርተዋል።

የተቀናጀ የምግብ ደህንንትን ለመለካት በደረጃ የሚከፋፍለው 'integrated food security phase classification' (IPC) የተሰኘ ስርዓት ነው ያመጡት።

ይህ ስርዓት አምስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ከዝቅተኛው የምግብ ደህንነት መጓደል ወደ ከፋው ረሃብ መከሰት ያለውን የሚለካ ነው። አይፒሲ መደበኛ የሚባሉ ጠቋሚዎችን ለምሳሌ የምግብ ፍጆታ፣ በምግብ እጦት የተሰቃዩ ህፃናትና የተከሰተውን ሞት በማጥናት ደረጃውን ይለካል።

መረጃ የለም፤ ረሃብ የለም

ረሃብ ተከስቷል ወይ ለሚለው የተሰጠው ይፋዊ ትርጉም በየቀኑ ከምንጠቀምበት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል የምግብ እጦት ተቸግረዋል ከሚለው የበለጠ ግልፅ ነው።

ነገር ግን ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአይፒሲ ስርዓት ሌላ መዋቅር ዘርግቷል። በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ረሃብ ተከስቷል ለማለት የተጠናቀረ ግልፅ መረጃ ያስፈልገዋል።

መንግሥታት ረሃብ ተከስቷል የሚለው ሁኔታ ስማቸውን እንዳያጠለሸው መረጃዎችን በመደበቅ ወይም በማጭበርበር እቅዳቸውን የሚያሳኩ ሲሆን በዚህም የረሃቡን አስከፊነት ዝቅ ያደርጉታል።

ከረሃብ ዝቅ ባለው ደረጃ ያሉት "ቀውስ" ፣ "አፋጣኝ እርዳታ" ተብለው በሚመደቡትም ውስጥ የሰዎች ህይወት ይቀጠፋል፤ ምንም እንኳን ሂደቱ ዝግ ያለ ቢሆንም።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ቀውሶች በተከሰተባቸው ቦታዎች እንዲህ አይነት ፈተናዎች ተጋርጠውበታል። በየመን፤ የሳዑዲ ጥምር ኃይል፣ መንግሥትና የሁቲ ባለስልጣናት ረሃብ ተከስቷል በተባሉ አካባቢዎች እንዳይደርሱ የረድዔት ድርጅቶችን ከልክለዋል። በዚህም ምክንያት ድርጅቶቹ የዳሰሳ ጥናት ማካሄድ አልቻሉም።

የተመጣጠነ (አልሚ) ምግብ እጥረት፣ የህፃናት ሞት፣ የምግብ ፍጆታ ጋር የተያያዘ መረጃ ከሌለ የምግብ ደህንነት መጓደል ስርዓትን የሚለካው የአይፒሲ ኮሚቴ ለጥንቃቄ ሲባል "አፋጣኝ እርዳታ" የሚያስፈልጋቸው በማለት ይመድባል። ረሃብ ተከስቷል ማለት አይችልም ምክንያቱም በአባሪነት መሪጃ ማቅረብ ስለማይቻል።

በደቡብ ሱዳን መንግሥት የመረጃ ስብስብን ማቆም አልቻለም። ነገር ግን ታህሳስ ላይ በነበረው የአይፒሲ የምግግብ ግምገማ "ረሃብ ተከስቷል" የሚለውን ዝቅ ለማድረግ ጣልቃ ገብቷል።

ሆኖም ረሃብ ተከስቷል የሚለው ትርጉም ሊያጨቃጭቀን አይገባም።

በለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲሲን መረጃ መሰረት በደቡብ ሱዳን ከምግብ እጥረትና ግጭት ጋር በተያያዘ 380 ሺህ ሰዎች በባለፉት አምስት አመታት ሞተዋል። ነገር ግን ከዚህ ውስጥ 1 በመቶ የሚሆኑት የሞቱት ረሃብ ተከስቷል በተባለበት በዩኒቲ ስቴት ግዛት በ2017 ነው።

ረድዔት ድርጅቶች የገቡበት አጣብቂኝ

ሌላኛው ዋነኛው ችግር ፖለቲካ ነው። ለተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረትና ረሃብ ወታደራዊ ፖሊሲ ምክንያት ሲሆን የረድኤት ድርጅት ሰራተኞች መውጣት የሚቸገሩበት አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ። እየደረሰ ያለውን ጥሰት ማውገዝና ከአገር ውጭ መባረር ወይስ በረሃቡ ወንጀል ተባባሪ ሆኖ ዝምታን መምረጥ።

የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም አልፎ አልፎ ውጊያ መኖሩን አምኗል። ነገር ግን ግጭቱ ካለባቸው አካባቢዎች የሚወጡ ሪፖርቶች አንደሚያሳዩት ከፍተኛ የሆነው የትግራይ ገጠራማ ክፍል አሁንም ቢሆን የጦር ሜዳ እንደሆነ ወይም በህወሃት ቁጥጥር ስር መሆኑን ነው።

በአለም አቀፉ የሰብዓዊ ህግ መሰረት ይህ ወታደራዊ ግጭት ነው እናም ወደ ሽምቅ ውጊያ የተመለሰው ህወሃት ከማጥቃት ወደ ኋላ አይልም። በግጭቱ የምግብ እጥረት ላጋጠመውና ለተራበው ህዝብ እርዳታ ለማድረስ ከህወሃት ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ያስፈልጋል።

በአንደኛው ወገን ተባባሪነት ብቻ በጭራሽ የሚሳካ አይሆንም።

እስካሁን ድረስ ባለው ህወሃትም ቢሆን ተኩስ ለማቆምም ሆነ የረድዔት ድርጅቶች እንዲገቡ አልጠየቀም። ከዚህ ጋር ተያይዞ አማፂ ቡድኖች እርዳታውን አላግባብ በመጠቀም የራሳቸውን ሰራዊት ሊመግቡ ይችላሉ የሚለው ፍራቻ አለ። ለዚያም ነው አለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች አስፈላጊ የሚሆኑት።

በትግራይ ያለው የምግብ እጥረትና ረሃብ ለረድዔት ድርጅቶቹ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ከቷቸዋል። ስለ ቀውሱ ከባለስልጣናቱ የሚሰጠውን ይፋዊ መረጃ በመገዳደር በክልሉ ያላቸውን ውስንና መሰረታዊ ስራዎች አደጋ ውስጥ አለመክተት ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ሆኖባቸዋል።

በረድዔት ሰራተኞች መካከል የተለመደ አባባል አለ፤ ለሰብዓዊ ቀውሶች ሰብዓዊ እርዳታ መፍትሄ አይደለም። በዋናነት የሚያስፈልገው የከፍተኛ አመራር ፖለቲከኞች ተግባርና ቁርጠኝነት ነው።

በሁሉ ነገር በሚለያዩ ሶሪያና ኮንጎ በመሳሰሉ አገራት በተከሰቱ ቀውሶችና እንዲሁም በተለያዩ አገራት በተደጋጋሚ የሚከሰት ችግር በመሆኑ የተባበበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ወታደራዊ ግጭትና ረሃብን በተመለከተ ሪዞሉሽን 2417 የተባለ ሰነድን ከሶስት አመታት በፊት አፅድቋል።

ሪዞሉሽን እስካሁን ድረስ በተግባር ላይ ባይውልም፣ ድርጅቱ በተደጋጋሚ እንደሚለው ረሃብን እንደ መሳሪያ መጠቀም እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል። ከዚህም በተጨማሪ በሪዞሉሽኑ መሰረት ወታደራዊ ግጭቶች መጠነ ሰፊ የምግብ ደህንነት መጓደል ወይም ረሃብ የሚያስከስት ከሆነ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የፀጥታው ምክር ቤትን ማሳወቅና ማስጠንቀቅ አለበት። ይሄንን ሪዞሉሽን አስተውሎ ላየው እንደ ትግራይ ክልል ባሉ የተከሰቱ ቀውሶችን እሳቤ ውስጥ በመክተት የፀደቀ ነው።

ነገር ግን ለረድዔት ድርጅቶች ይህንን ሪዞሉሽን እንዳይጠቅሱም መደናገጥ አለ፤ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የኢትዮጵያን መንግሥት ማስቀየም አይፈልጉም።

በትግራይ ክልል ባለው የረሃብተኞች፣ ህመምተኞችና ሞት ቁጥር አስተማማኝ ቁጥር ባይኖርም ነገር ግን እስካሁን በተረዳነው መሰረት ክፉኛ የሆነ ቀውስ እየተፈጠረ ለመሆኑ ማሳያ ነው።

ፀሃፊው አሌክስ ዋል በአሜሪካ በሚገኘው በተፍትስ የፍሌቸር ስኩል ኦፍ ሎው ኤንድ ዲፕሎማሲ ዩኒቨርስቲ ፣ የዓለም አቀፉ የሰላም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው