ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጃክ ፓላዲኖ፡ የቢል ክሊንተን የትዳር መማገጥ ዜናን ያድበሰበሰው ሰው አስገራሚ አሟሟት
ዕውቁ የዝነኞች የግል መርማሪ በካሜራው ምክንያት ገዳዮቹን አጋለጠ።
ጃክ ፓላዲኖ ይባላል፡፡ ትናንትና 76 ዓመቱ ነበር፡፡ ዛሬ እንኳ የለም፡፡
በአሜሪካ ዕውቅ የግል ወንጀል መርማሪና ጉዳይ አስፈጻሚ ነበር፡፡
ባለፈው ሐሙስ ለታ ወንበዴዎች ድንገት ያዙት፡፡
ሳንፍራንሲስኮ በሚገኘው ቤቱ ደጅ ላይ ነው ማጅራቱን የቆለፉት፡፡ ታገላቸው፡፡ ጣሉት፡፡ ድንገት ግን አንዲት የድሮ ካሜራውን ይዟት ነበር፡፡ እነሱ ሊቀሙት ይታገሉት ነበር፡፡ ካሜራዋን።
እንደምንም ብሎ ተጫናት፡፡ ፎቶ አነሳች፡፡
ወንደበዴዎቹ ጭንቅላቱ ላይ ባደረሱበት ጉዳት ኋላ ላይ ነፍሱ ከሥጋው ብትለይም ፖሊስ ጥፋተኞቹን ደርሶባቸዋል፡፡
ገዳዮቹ ሊደረስባቸው የቻለው ደግሞ ፓላዲኖ ከመሞቱ በፊት ፎቶ ስላነሳቸው ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ከ2 ሳምንታት በፊት ነው፡፡
ፓላዲኖ ሥመ ጥር የግል ወንጀል መርማሪ ሲሆን ከዋና ዋና ደንበኞቹ መሀል የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች እና ዕውቅ የሆሊውድ ተዋናዮች፣ ሙዚቀኞችና ጸሐፊ ተውኔቶች እና ሌሎች ገናናዎች ይገኙበታል፡፡
የፓላዲኖ ካሜራ የወንበዴዎቹን ምሥል በማስቀረቱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን አድኖ ቢይዝም በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሆስፒታል የነበረው ፓላዲኖ ግን ትናንትና ሰኞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
ዝነኛው ፓላዲኖ ዘመናትን ባስቆጠረው የግል መርማሪነት ሥራው አነጋጋሪ የነበሩ ጉዳዮችን በመያዝ ገናና ነበር፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን፣ ሞዛቂና ተዋናይት ከርትኒ ላቭ፣ በቅሌት ማጥ ውስጥ የሚገኘው ዝነኛው ፕሮዲዩሰር ሐርቬይ ዊኒስተን የፓላዲኖ ደንበኞች ነበሩ፡፡
ባለፈው ሐሙስ ፓላዲኖ ጥቃት ሲደርስበት ሳንፍራንሲስኮ ከሚገኘው ቤቱ ደጅ ላይ የነበረ ሲሆን 2 አደገና ቦዘኔዎች ናቸው የተባሉ ወጣቶች ናቸው በእጁ ይዞት የነበረውን ካሜራ ሊቀሙት የታገሉት፡፡
ይህን ተከትሎ ፓላዲኖ ወደኋላ ወድቆ ጭንቅላቱ ስለመታው ራሱን ወዲያውኑ ሳተ፡፡
በሚደንቅ ሁኔታ ታዲያ አጥቂዎቹ ከመሸሻቸውና እሱ ራሱን ከመሳቱ በፊት በነበረች ቅጽበት ፓላዲኖ የካሜራውን ጉጠት ተጭኖት ነበር፡፡
ፓላዲኖ ቢሞትም ፖሊስ ግን ያን ምሥል ተጠቅሞ ነው ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው፡፡
የፓላዲኖ ባለቤት ሳንድራ ሱተርላንድ የወንጀለኞቹን መያዝ ስትሰማ፣ ‹‹ምነው የሰራው ሥራ ወንበዴዎቹ እንዲያዙ ማድረጉን መርማሪ ሆኖ የኖረው ባለቤቴ ባወቀ›› ብላ ተናግራለች፣ ለአሶሲየትድ ፕሬስ፡፡
ሕይወቱን ሙሉ የወንጀል መርማሪ ሆኖ የኖረ ሰው ገዳዮቹ በዚህ መልክ መያዛቸው የሕይወት ግጥምጥሞሽ በሚል ብዙዎቹን አስደንቋል፡፡
ፓላዲኖ ሕግ የተማረ ሲሆን የግል መርማሪ ሆኖ መሥራት የጀመረው በ1970ዎቹ ነበር፡፡ ያን ዘመን የግል መርማሪ በፊልሞች ውስጥ ገዝፎ ይሳል ስለነበር ሥራውም ገናና ያደርግ ነበር፡፡
በ1977 ፓላዲኖ በአንድ የግል የወንጀል ምርመራ ቡድን ውስጥ ከባለቤቱ ጋር ተቀጠረ፡፡ እሱና ባለቤቱ ለዓመታት ወንጀል ምርመራ ውስጥ አብረው ሰርተዋል፡፡
እነ ፓላዲኖ በተለይም ለሆሊውድ ዝነኞች ስማቸው እንዳይጎድፍ የሚዲያ ዘመቻ በመክፈት፣ ወይም የሚዲያ አፍ በማዘጋት ሥራ ይሰማሩ ነበር፡፡
ለምሳሌ ሙዛቂዋ ከርተኔይ ባሏ ከሞተ በኋለ በሱ ዙርያ ይወሩ የነበሩ የሚዲያ ሐሜቶችን እንዲያከስምላት ፓላዲኖን ቀጥራው ነበር፡፡
ፓላዲኖ በተለይ ቢል ክሊንተን ከትዳራቸው ውጭ ወጣ ይሉ ነበር የሚለውን ሐሜት እንዲቀብርላቸው ክሊንተን ቀጥረውት ውጤታማ ሥራ ሰርቶላቸዋል፡፡
በ1999 ዓ/ም ሳንፍራንሲስኮ ኤክዛሚነር ጋዜጣ ፓላዲኖን ሲገልጸው፣ ‹አስጨናቂ መርማሪ፣ የጎደፈ ስም ወልዋይ፣ ለሙያው ሟች› ብሎት ነበር፡፡