ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢስዋቲኒ (ስዋዚላንድ) በኮቪድ ምክንያት የአስክሬን መጠቅለያ እጥረት ተከሰተ
በኢስዋቲኒ (ስዋዚላንድ) በኮቪድ ምክንያት የአስክሬን መጠቅለያ እጥረት ተከሰተ
ስሟን ከስዋዚላንድ ወደ ኢስዋቲኒ የቀየረችው የደቡባዊ አፍሪካ አገር በኮቪድ ታማሚዎች ምክንያት የአስክሬን መጠቅለያ እጥረት ገጥሟታል፡፡
በሉቦምቦ የሪፈራል ሆስፒታል የጤና ሠራተኞች እንዲሁም በጉድሼፐርድ ሚሽን ሆስፒታል የጤና መኮንኖች ለታይምስ ኦፍ ስዋዚላንድ እንደተናገሩት የአስክሬን ላስቲክ እጥረት በማጋጠሙ የተነሳ ሬሳ በአንሶላ ለመጠቅለል ተገደዋል፡፡
እጥረቱ የተከሰተው ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ነው፡፡
ችግሩን ተከትሎ የአስክሬን ፌስታል አቅራቢዎች እንዲወዳደሩ ጨረታ ወጥቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊዚ ንኮሲ ስለችግር መጀመርያ መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ትንሽዋ ደቡብ አፍሪካዊት አገር ኢስዋቲኒ የጤና መኮንኖች በበቂ ባለመኖራቸው የዓለም ጤና ድርጅት ትብብር እንዲያደርግ ጠይቃለች፡፡ ይህን ተከትሎም 28 የጤና መኮንኖች ወደዚያች አምርተዋል፡፡ ከነዚህ መሀል 11 ሐኪሞች የተላኩት በታላቋ ብሪታኒያ አማካኝነት ነው፡፡
በተህዋሲው ክፉኛ የተሽመደመደችውን ደቡብ አፍሪካን የምትዋሰነው ኢስዋቲኒ 15ሺ ዜጎቿ ታመውባታል፡፡ 574 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል፡፡
ኢስዋቲኒ በአፍሪካ በቆዳ ስፋት ትንሽ ከሚባሉና የባሕር በር ከሌላቸው አገራት ተርታ ስትሆን የሕዝብ ብዛቷም 1.1 ሚሊዮን አካባቢ ብቻ ነው፡