የዓለም ሂጃብ ቀን፡ የመገለል ስሜትን ለመታገል በማሰብ የሚከበረው ዓለማቀፉ የሂጃብ ቀን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሂጃብ ቀን እየተከበረ ነው። በዚህ ዕለት ሒጃብን ሙስሊም ያልሆኑ ሴቶች ለአንድ ቀን ለብሰውት ይውላሉ፡፡ ይህ በተለይ በአሜሪካና በእንግሊዝ የተለመደ ነው፡፡
ለምሳሌ በታላቋ ብሪታኒያ ሊንክሻየር በርካታ ሙስሊም ያልሆኑ ሴቶች ሂጃብን ለአንድ ቀን አድርጎ ለመዋል ተመዝግበው ይህንኑ አድርገዋል፡፡
በተለይ የ2ኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች ቀኑን በዚህ መንገድ እንዲያሳልፉ ይበረታታሉ፡፡ ዋናው ምክንያት ሒጃብ የሚለብሱ ተማሪዎች የመገለል ስሜት እንዳይሰማቸው ለማድረግ ነው፡፡
የሒጃብ ቀን የሚከበርበት ዋንኛ ምክንያት ሙስሊም ሴቶች በሒጃብ ምክንያት የሚደርስባቸውን ሥነ ልቡናዊና ማኅበረሰባዊ መገለል ለመቃወም ነው፡፡
በሊንከንሻየር የሊንከን ሙስሊም ሲስተርስ ባልደረባና የመብት አቀንቃኝ የሆነችው ኻዳ መሐመድ እንዲህ ትላለች፡-
‹‹አንዳንድ ሴቶች ሒጃብ በማድረጋቸው ብቻ የዚህ ኅብረተሰብ ሙሉ አባል እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል፤ የነሱን ስሜት ሌሎች እንዲጋሩትና ባለሒጃብ ሴትን እንዳያገሉ ለማድረግ ነው የሒጃብ ቀንን የምናከብረው፡፡"
ይህ ተግባር ከዚህ ቀደምም በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ተሞክሮ መጠነኛ ማኅበረሳዊ የግንዛቤ ለውጥ እንዳመጣ ሲዘገብ ነበር፡፡ በተለይም ሙስሊም ያልሆኑ ሴቶች ከአሜሪካ ባንዲራ ቀለማት ያጌጠ ሒጃብ በመልበስ ሒጃብን መልበስ ግማሽ አሜሪካዊ እንደማያሰኝና ብሔራዊ አገራዊ ስሜትን እንደማይቀንስ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
ነፍረቲቲ ብራውን ጥቁር አሜሪካዊት ናት፡፡ አጋርነቷን ለመግለጽ ሒጃብ ለብሳ ለቢቢሲ ሐሳቧን ባጋራችበት ቪዲዮ ላይ እንዲህ ስትል ትሰማለች፡
‹‹የምወዳቸው ሙስሊም ጓደኞች አሉኝ፡፡ እኔ የማመልከውን አምላክ አይደለም የሚያመልኩት፡፡ ያ የእነርሱ ምርጫ ነው፡፡ ይህንን ሒጃብ (በእጇ እያመላከተች) ስለለበሱ ግን ከኔ ያነሱ አሜሪካዊ ተደርገው መወሰዳቸው ቅር ይለኛል›› ትላለች፡፡
የሒጃብ ቀን በኢትዮጵያ
ሂጃብን ለሃይማኖታዊ ተግባሩ ብቻ ሳይሆን እንደባህልም ወስደው የሚለብሱ ማህበረሰቦች ባሉባት ኢትዮጵያም ‹የሒጃብ ቀን› ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።
በኢትዮጵያ ይህንን ቀን የሚያዘጋጀው የሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠራው ድርጅት 'ውሜንስ አሊያንስ ፎር ፒስ ኤንድ ጀስቲስ' ይሰኛል።። የዚህ ድርጅት ኃላፊ የሆነችው ጀሚላ ሰዒድ፣
"በተለይ በምዕራባውያን አገራት ሂጃብ የለበሰች ሴት ስትታይ መጀመሪያ የሚመጣባቸው ምሥል ከአሸባሪነት ጋር የተያያዘ›› መሆኑን ትናገራለች።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሂጃብ የሚለብሱ ማኅበረሰቦችን የማግለል ስሜት ስለነበር ይህንን ለማስቀረት ተብሎ ነው ቀኑ መከበር የጀመረው ብላለች።
" እኛ ሂጃብ ስለለበስን ብቻ የተለየ ሰዎች ተደርገን መታየት የለብንም። እስቲ እናንተም ልበሱትና የሚሰማችሁን ስሜት ንገሩን ብለን ሙስሊም ያልሆኑ ጓደኞቻችንን ሂጃብ እንዲለብሱ በማድረግ ነው ይህንን ቀን የምናከብረው" ትላለች ጀሚላ።
የእስልምና እምነት እሴትና መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ሂጃብ ነው። ኢስላማዊ እሴት ከመሆኑም ባሻገር የሴቷ መብትና ክብር መገለጫ ነው ይላሉ በሂጃብ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ሴቶች።
ሒጃብ የለበሰችን ሴት ሲያዩ አሉታዊ ስሜት የሚፈጠርባቸው ሰዎች ቀላል አይደለም፡፡
ይህን አስተሳሰብ ለማስቀረት በሚል እኤአ በ2013 የዓለም አቀፍ ሂጃብ ቀን በሚል መከበር ተጀመረ።
ይህን ቀን ማክበር ያስጀመረችው ሴት በዜግነት አሜሪካዊት በትውልድ ደግሞ ባንግላዲሻዊት የሆነችው ናዝማ ካኻን ነች።
ይህ ቀን ታስቦ በሚውልበት ወቅት የእስልምና እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የሌላ እምነት ተከታይ ጓደኞቻቸውም ሂጃብ መልበስ የሚፈጥረው ስሜት ምን ዓይነት እንደሆነ እንዲሰማቸው በማድረግ ነው የሚከበረው።
ይህ የዓለም አቀፍ ሂጃብ ቀን እኤአ ፌበሪዋሪ 1 የሚከበር ሲሆን በኢትዮጵያም ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።
በሂጃብ ምክንያት የሚደርሰው ችግር ሲታይ የምዕራባውያን እና የእኛ ተመሳሳይ አይደለም የምትለው ጀሚላ በምዕራባውያኑ አገራት ሂጃብ የሚለብሱ ሙስሊሞች የተለያዩ ችግሮች ሲደረሰባቸው እንደሚታይ ታስረዳለች።
" በምዕራባውያኑ አገራት ያሉ ሴቶች ከማህበረሰብም ሆነ በሥራ ዓለም የተለያየ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በእኛ አገር ግን ሕዝቡ በብዛት ሃይማኖተኛ ስለሆነ፣ ሂጃብ እና ቀሚስ ለብሶ መሄድ ይህን ያህል ችግር አይፈጥርም። ችግሩ ያለው በመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና በንግዱ ዓለም ውስጥ ነው። የእኛ ዋና ዓላማ ይህንን ሐሳብ ማስቀየር ነው።"
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ አንዲት ሴት ሂጃብ ስለለበሰች በማህበረሰብ ውስጥ የሚደርስባት ችግር ላይኖር ይችላል የምትለው ጀሚላ፣ በሥራ ዓለም ውስጥ ግን ይህ ችግር በብዛት እንደሚስተዋል ትናገራለች።
አብዛኛው የሥራ ዘርፎች የመሥሪያ ቤታቸውን የልብስ ደንብ ሲያወጡ ሂጃብን ያማከለ የአለባባስ ደንብ ከነጭራሹ የለም ስትልም ታብራራለች።
"በኢትዮጵያ እንደማኅበረሰብ ሂጃብ የሚለብሱ ማህበረሰቦች አሉ። ቁጥራቸውም ብዙ ነው። ስለዚህ የመሥሪያ ቤቶች ደንብ ልብስ ይህንን የሚያቅፍ መሆን እንዳለበት ለማሳየት ጭምር ነው የዚህ ቀን መከበር ያስፈለገው።"
አክላም ሂጃብ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የዚያ ማኅበረሰብ መገለጫ ባሕል ሆኖ ሊለበስ ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ባህል ወስደው የሚለብሱም አሉ። ለምሳሌ ሶማሌ፣ አፋር፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ አካባቢዎች ሂጃብን የሚለብሱት ለሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ባህላቸውም ስለሆነ ነው ትላለች ጀሚላ።
ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ትርጉም ያለውን ልብስ ማግለል ትክክል እንዳልሆነ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ቀኑን ማክበር ያስፈለገው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንዲት ሴት በአለባበሷ ምክንያት ከሥራ የምትገለል ከሆነ እንደ ማኅበረሰብም አንደ አገርም የሚደርሰው ኪሳራ ቀላል አይደለም የምትለው ጀሚላ፣ የመገለል ስሜቱ ለአገር ያለኝን ፍቅር ሊቀንስ እንደሚችልም በመግለጽ "ማንነቴን የማታስተናግድ አገር ከሆነች ሞራሌ ይነካል፤ ለአገሬም የማስበውን የበኩሌን ለማበርከት ሊቸግረኝ ይችላል።" ብላለች።
ሂጃብ-መብትና የሴቶች መብትና ክብር
የሂጃብ አለባበስ የአንዲት ሙስሊም ሴት የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከሴቶች መብት ጋር የሚያያዝ ጽንሰ ሃሳብ ነው የምትለው ጀሚላ፣ "ይህ አለባበስ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት በተወሰነ ሊቀንስ ይችላል ብላ ታምናለች፡፡ እንደ እስልምና ሃይማኖትም የሴቷን ለሥነ ሥርዓት ተገዢ መሆኗን ማሳያ ነው" ትላለች፡፡
በተጨማሪም የቁርዓን መርህም ሂጃብ አንዲት ሴት በምግባረ ብልሹ ሰዎች እንዳትጠቃ የሚከለክል ነው ስትል ትናገራለች። ለሴቶች መብት እንደ ከለላ ይታያል ስትልም ታክላለች።
የሂጃቡ ዋና ጽንሰ ሃሳብ የሴቷ ክብር ነው። ሴቶች ሂጃብ ሲለብሱ በቀላሉ ለአካላዊ ጥቃት አይጋበዙም። የሂጃብ ትርጉም ከሃይማኖታዊም አልፎ የሴቷን መብት ለማስከበር የሚሆን ትርጉም አለው።
የሂጃብ ቀን መከብር ከጀመረ ጀምሮ በርካታ ለውጦች ታይተዋል የምትለው ጀሚላ፣ ይህንኑም ስታስረዳ በአንዳንድ አገራት ለሂጃብ ያላቸው አመለካከት ተቀይሯል ትላለች።
ለዚህም ማሳያ በዩኬ፣ ኒውዚላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ ሙስሊም የፖሊስ አባላት ሂጃብ ለብሰው እንዲሠሩ መፍቀዳቸውን ትጠቅሳለች።
እንደ ካናዳ ባሉ አገራት ደግሞ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሂጃብ ማድረግ ይፈቀዳል።
















