“የፈረንሳይ ምርቶችን አንገዛም”

"የፈረንሳይ ምርቶችን አንገዛም"

የፎቶው ባለመብት, Arshad Tareen/Merve Ozdemir/Hiba Mohamed

ከቱርክ እስከ ባንግላዲሽ፤ ከጆርዳን እስከ ማሌዥያ የፈረንሳይ ምርቶች እንዲታገዱ ንቅነቄ እየተካሄነ ነው።

አንዳንድ መደብሮች የፈረንሳይ ምርቶችን ከመደርደሪያቸው አውርደዋል። የፈረንሳይ ምርቶች እንዲታገዱ የሚያበረታታው ሀሽታግ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከ100,000 ጊዜ በላይ ታይቷል።

ንቅናቄው የተጀመረው የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ነው።

ስለ ንግግር ነጻነት ሲያስተምር የነብዩ መሐመድን ካርቱን ለተማሪዎቹ ያሳየ የታሪክ መምህር መገደሉን ተከትሎ፤ ፕሬዘዳንቱ "የተገደለው የነጋችንን መውሰድ በሚፈልጉ ኢስላሚስቶች ነው። ካርቱን ከመሥራት አንቆጠብም" ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2006 ላይ ቻርሊ ሄብዶ የተባለው የስላቅ መጽሔት የነብዩ መሐመድን ምሥል ማተሙ ይታወሳል። ይህም በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞችን አስቆጥቷል።

ማክሮን ከሃይማኖት ነጻ የሆነ ምልከታ እና የንግግር ነጻነትን መደገፋቸው ተገቢ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።

ባለፈው ሳምንት ኒስ ከተማ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ፤ ማክሮን "እስላማዊ የሽብር ጥቃት ነው" ብለዋል።

ንግግራቸውን በርካታ የሙስሊም አገራትን ኮንነዋል።

ባንግላዲሽ ውስጥ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የፈረንሳይ ምርቶች እንዲታገዱ የሚጠይቅ ሰልፍ አካሂደዋል።

ቢቢሲ ሦስት አገሮች የሚኖሩ፣ የፈረንሳይ ምርቶችን መግዛት ለማቆም የወሰኑ ሰዎችን አነጋግሯል።

የፓኪስታኗ ተዋናይት- ሚሺ ካሀን

የፈረንሳይ መዋዋቢያ እጠቀም ነበር። በተለይ ሎሬል ፓኪስታን ውስጥ በቀላሉ ይገኛል።

አሁን ግን ምግብ እና ቁሳቁስ ስገዛ ፈረንሳይ አለመሠራቱን አረጋግጬ ነው። የፈረንሳይ ምርቶችን በፓኪስታን ምርቶች እየተካሁ ነው።

ምክንያቱም የአገሪቱ ፕሬዘዳንት መላው የሙስሊም ማኅበረሰብን አዋርዷል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የፈረንሳይ ምርቶችን ማንም እንዳይገዛ እየቀሰቀስኩ ነው። ሃይማኖቴን እየተከላከልኩ ስለሆነ ህሊናዬ ንጹህ ነው።

ከእንግዲህ ሰዎች ሃይማኖታችን እና ነብያችን ላይ እንዲቀልዱ መፍቀድ የለብንም። በቃን። እስካሁን ሃይማኖቱ ላይ የተሳለቁ ሰዎችን ይቅር ብለናል። ከእንግዲህ ግን እርምጃ እንወስዳለን።

ማክሮን ሆነ ብለው ሊጎዱን እንደፈለጉ ይሰማኛል። ሰውን ከቆነጠጡ በኋላ "አመመህ?" ብሎ የመጠየቅ ያህል ነው።

ጥላቻን እየዘሩ ነው። ሰዎችን እየተነኮሱ፣ እየከፋፈሉ ነው። ንግግራቸው ሙስሊም ጠል ድርጊት ያነሳሳል።

የአገራቸውን ዜጎች አንድ ማድረግ እና እኩል ማየት ነው የሚጠበቅባቸው።

መጀመሪያ ላይ የቻርሊ ሄድቦ መጽሔትን ስመለከት የምናገረው ጠፋኝ። ለረዥም ጊዜ ላለማየት ሞክሬያለሁ። ሳየው ግን ደነገጥኩ። አለቀስኩ። ፈጣሪዬ ሆይ ለምን ይሄን ተመለከትኩ? አልኩ።

ቱርካዊቷ ተማሪ- ላቲፍ ኦዝደሚር

እንደ ላንኮም ያሉ ምርቶችን በየቀኑ እጠቀም ነበር። ከዚ በኋላ ግን አልገዛም።

የፈረንሳይ ምርቶችን የማልገዛው ከዚህ በኋላ ትዕግስት እንደሌለን ለማሳየት ነው። የፈረንሳይን ሙስሊም ጠል አካሄድ መታገል እፈልጋለሁ።

እኛ ሙስሊሞች ድምጻችንን ማሰማት አለብን። ለዘመናት ታፍነናል። አሁን ማድረግ የምንችለው ምርቶቹን አለመግዛት ብቻ ነው።

ቻርሊ ሄብዶ አስጸያፊ ነገር አትሟል። በፊት ገጹ ፕሬዘዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ካናቴራ ያለ ሱሪ ለብሰው፣ ቢራ ሲጠጡና ሂጃብ የለበሰች ሙስሊም ሴት ቀሚስ ሲገልቡ ያሳያል።

ሂጃብ እንደሚለብስ ሰው ሳስበው ይህ ሙስሊም ሴቶችን የሚያስከፋ ነው።

እንደኔ ያሉ ሙስሊም ሴቶች ሃይማኖቱ በበጎ እንዲታይ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ እኩል እንድንታይ እንታገላለን።

ይህ ካርቱን ግን ትግላችንን ዋጋ ያሳጣዋል። አውሮፓ ሙስሊም ሴቶችን ሙስሊም ካልሆኑ ሴቶች እኩል መቼም እንደማታይ ያሳያል።

ካርቱንም ይሁን ስላቅ መፍጠር ያለበት የበሰለ አስተሳሰብ እና ክርክር ነው። አውሮፓ ግን ከዚህ በተቃራኒው ሙስሊሞችን ለማግለል ትጠቀምበታለች።

በተደጋጋሚ እነዚህን ካርቱኖች መሳል እሳቱ ላይ ቤንዚን መጨመር ማለት ነው። ይሄን ነው የምንፈልገው? በንግግር ነጻነት ስም እርስ በራሳችን የምንዘላለፍበት እና የምንጠላላበት ዓለም ነው የምንሻው?

ሀይማ መሐመድ ሞሳ- የሞሪታኒያ ተማሪ

የፈረንሳይን ድርጊት ለመኮነን በተጠራው ሰልፍ ላይ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር ተሳትፌያለሁ።

የፈረንሳይ ምጣኔ ሀብት ተንኮታኩቶ ማክሮን በጥላቻ ንግግራቸው ያስቀየሟቸውን ሁለት ቢሊዮን ሙስሊሞች ይቅርታ እስካልጠየቁ ድረስ የፈረንሳይ ምርቶችን ባጠቃላይ አንገዛም።

በፈረንሳይ አይብ ፋንታ የቱርክ ምርቶችን እየተጠቀምን ነው። እንደ ላኮስቴ ያሉ የፈረንሳይ ሽቶዎች አሉኝ። ከጨረስኳቸው በኋላ ከእንግዲህ በድጋሚ አልገዛም።

ማክሮን ይቅርታ እንዲጠይቁ ደብዳቤ ጽፌያለሁ። እሳቸው የታሪክ መምህሩ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል። የኛ ነቢይስ ክብር አይገባቸውም?

በሙስሊም ጠል ንግግራቸው ሃይማኖቱን ከኋላ ቀርነት ጋር ማገናኘታቸው በጣም አስቆጥቶናል። ይህንን ኢ ፍትሐዊ ንግግር መታገስ የለብንም።

የፈረንሳዩ መሪ አንድ ማኅበረሰብን የሚያስቀይም ምስልን የንግግር ነጻነት መገለጫ ማለታቸው ሃይማኖቱን ማጥቃት ነው።

በፖለቲካ ውድድር ነጥብ ለማስቆጠር ነው የሞከሩት።

የነብዩ መሐመድ ካርቱን ቻርሊ ሄብዶ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታተም ልጅ ነበርኩ። በመጽሔቱ ቢሮ የደረሰው ጥቃት ትዝ ይለኛል።

እስከዛሬ ካርቱኑን ላለማየት ስሞክር ነበር። ባለፈው ግን ትዊተር ላይ ተመለከትኩት። እንደተዋረድኩ ተሰማኝ። እስልምና ልክ እንደ ክርስትና እና የአይሁድ ሃይማኖት ለምን አይከበርም?