የፈረንሳዩ ኩባንያ በደረሰበት ጫና ሂጃብ መሸጥ አቆመ

የፎቶው ባለመብት, DECATHLON MAROC/FACEBOOK
የፈረንሳዩ የስፖርት ትጥቅ አከፋፋይ ኩባንያ ለስፖርተኞች ሂጃብ ማቅረቤን አቁሜያለሁ አለ።
ዲካትሎን የተባለዉ ትጥቅ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ ዛቻዎችና የገበያ ማስፈራሪያዎች ስለደረሱብኝ የስፖርተኞች ሂጃብ ማቅረቡን ለጊዜው ትቼዋለሁ ብሏል።
ኩባንያዉ የሚያመርተው ሒጃብ ሴት ስፖርተኞች በጨዋታዎች ጊዜ የሚለብሱት ነው። ነገር ግን ይህን አንቀበልም ያሉ ወገኖች በኩባንያዉ ላይ ጫና አሳድረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ሂጃብ ማድረግ የሃገሪቱ መንግሥት ከሃይማኖት ጋር የተለያየ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው የሚል አስተያየት ሲሰጥ፣ የሕግ ባለሞያዎች ደግሞ ምርቱ እንዳይሸጥ ቅስቀሳ እናደርጋለን የሚል ተቃውሞ መሰንዘራቸው ዲካትሎን ምርቱን እንዲያቆም ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ናቸው።
የኩባንያዉ ቃል አቀባይ ዣቬየር ሪቮየር "ዉሳኔ አሳልፈናል. . . በዚህ ሰዓት ፈረንሳይ ውሰጥ መሸጥ የለበትም" ብለዋል።
ነገር ግን ካሁን በፊት ቃል አቀባዩ ለኤኤፍፒ በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ሂጃብ ገበያ ላይ የምናቀርበው ሁሉንም የዓለም ሴቶች በስፖርት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ነዉ" ብለው ነበር።
ጸጉርን ብቻ የሚሸፍነዉ ሂጃቡ ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በ49 ሃገራት በስፋት ይሸጥ ነበር። ነገር ግን ይህ በመሆኑ ተቋሙ ባለፉት ወራት የተቃውሞ ይዘት ያላቸው ከ500 በላይ የማስጠንቀቂያ የስልክ ጥሪዎችና የኢሜይል መልዕክቶች ደርሰውኛል ብሏል።
የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር አግነሰ በዚን "ይህ ልጋራው የማልፈልግ የሴቶች ምርጫ ነው። የፈረንሳይ ኩባንያም ይህን ምርት ባያስተዋውቀው እመርጣለሁ" የሚል ሃሳብ መስጠታቸዉም ሌላኛው ጫና ተደርጎ ተወስዷል።
በተመሳሳይ የፈረንሳይ መንግሥት ቃል አቀባይ አውሮር በርጌ "እንደሴትነቴና እንደ ፈረንሳያዊ ዜጋ እሴቶቻችንን የማያከብር ምርት ላይ እምነት አለመጣልን እመርጣለሁ" የሚል መልዕክት በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸው ኩባንያዉን ምርቱ ወደ አለመሸጥ ውሳኔ መርቶታል።
ፈረንሳይ መንግሥትን እና ሃይማኖትን የሚለያይ ጠንካራ ሕግ ያላት በመሆኗ ምንም አይነት ሃይማኖታዊ መገለጫ ያላቸዉ አልባሳት በትምህርት ቤቶችና በመንግሥት ተቋማት እንዳይለበሱ ከልክላለች።
ፈረንሳይ በ2010 ሙሉ ፊትን መሸፈንን የከለከለች ሲሆን የመብት ተሟጋች ነን የሚሉ ቡድኖች "ፈረንሳይ ሙስሊም ሴቶችን ታገልላለች፣ እስልምናንም ትጠላለች" በማለት እየከሰሱ ነው።












