የደቡብ አፍሪካ ጦር በሴት ሙስሊም የሰራዊቱ አባላት ላይ የጣለውን የሂጃብ ገደብ አነሳ

የጦር መኮንን

የፎቶው ባለመብት, Legal Resources Centre twitter page

የደቡብ አፍሪካ ጦር ከሃይማኖት ጋር የተያያዘውን የአለባበስ ፖሊሲውን በመቀየር ሴት ሙስሊም የሰራዊቱ አባላት ላይ የጣለውን የሂጃብ ገደብ አንስቷል።

በተሻሻለው ፖሊሲ መሰረት ሴት ሙስሊም የሰራዊቱ አባላት ከወታደራዊ ደንብ ልብሳቸውም ጋር ሂጃብ መጠምጠም ይችላሉ ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ይህ ፖሊሲ ሙስሊም ሴቶችን የሚያገል ነው ብሎ በመቃወም አንድ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶት ነበር።

ሌጋል ሪሶርስ ሴንተር የተባለው ድርጅት እንዳሳወቀው ይኸ ፖሊሲ የተቀየረው ከደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሰራዊት ጋር ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ ነው።

ድርጅቱ ከሃይማኖት ከእኩልነት ጋር በተያያዘ ያቀረበውን ክስም እንደተወው አሳውቋል።

"ይኼንን ጉዳይ በፍርድ ቤት እንዲቋጭ የማድረጉን ሁኔታ ትተነዋል። ምክንያቱም የመከላከያ ሰራዊቱ ሙስሊም ሴቶች ላይ ያደርገው የነበረውን ማግለል በማስቀረት ሂጃብ እንዲለብሱ ፈቅዷል" በማለት ድርጅቱ በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ቃለ አቀባይ ብርጋዲየር ጄኔራል ማፊ ምጎብሆዚ በበኩላቸው " የሰራዊቱ የሃይማኖት አለባበስ ፖሊሲ ተሻሽሎ ሙስሊም ሴቶች በእምነታቸው መሰረት እንዲጠመጥሙ ፍቃድ ሰጥቷል" በማለት መናገራቸውን አይኦኤል የተባለ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከዚህ ቀደም ሜጀር ፋጢማ አይዛክ የተባለችና ሙስሊም ሴት የሆነች የሰራዊቱ አባል ከአለባበስ ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ከላይ የመጣ ትዕዛዝና ስርአት አላከበርሽም በሚል ክስ ቀርቦባት ነበር። ለሁለት አመት ያህል ስትታገል ነበር ተብሏል።