ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ከቀረቡ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ተወሰነ
በእነ አቶ ጃዋር መሃመድ ከቀረቡ ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት፣ ጥር 14/2013 ዓ.ም ውሳኔ አስተላልፏል።
የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፤ በዛሬው ውሳኔ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 የተያያዙ መሆናቸውም ተገልጿል።
በእነ አቶ ጃዋር መዝገብ ስር 24 ተከሳሾች ቢኖሩም የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ተጠቅሶ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባንና ጠባቂዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 12 ሰዎች ላይ ነበር።
ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገመንግሥታዊ አንደኛ ችሎት ዛሬ ማለዳ በዋለው ችሎት ነው።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ጥር 4፣ 2013 ዓ.ም በነበረው ችሎት አቃቤ ሕግ ክሶቹን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ማዘዙ ይታወሳል።
ነገር ግን አቃቤ ሕግ ሌሎቹን ክሶች እንዳሻሻለ ከተራ ቁጥር አምስት እስከ አስር ያሉና የተጠቀሰውን፣ከጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ መሰረት በማድረግ የተከፈቱትን ክሶች ማሻሻል እንደማይፈልግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱ በምላሹ ክሶቹ በተጠቀሰው አዋጅ ስር መታየት እንደማይችሉ በመጥቀስ እንዲቋረጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም መሰረት በጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 የተከፈቱ ስድስቱም ክሶች እንዲቋረጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የቀሩት አራት ክሶች "በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ"፣ የፀረ ሽብር አዋጅ 1176/2012 እና የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅን 7061/2004 የሚመለከቱ ናቸው።
ጥር 4 2013 ዓ.ም በነበረው ችሎት ላይ ቃቤ ሕግ ክሶቹ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ በታዘዘው መሰረት፣ በተቀሩት ክሶች ጋር በተያያዘ አቃቤ ሕግ ሸኔ ምን እንደሆነ እንዲያብራራ ፍርድ ቤቱ ጠይቆ ነበር።
ሸኔ ግለሰብ ነው ወይስ ቡድን በሚል የተጠየቀው አቃቤሕግ፣ ሸኔ ግለሰብ ሳይሆን ቡድን ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ሶስተኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ሀምዛ አዳነን በተመለከተ ሚዲያዎችን በመጠቀም ቅስቀሳ አድርጓል የሚል ክስ የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የትኛዎቹን ሚዲያዎች መጠቀማቸውን ጠይቆ ነበር።
አቃቤ ሕግ በበኩሉ ኦኤም ኤን እና የግል ማህበራዊ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ እነዚህን ማሻሻያዎች ጨምሮ ክሱን ለተከሳሾች ካነበበ በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሊቀበል ጠይቆ፣ ጠበቆች የእምነት ክህደት ከመስጠት በፊት ክሱ በተገቢው መንገድ መሻሻሉን ለማየት ቀነ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለጥር 19 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አማራር አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ ለፍርድ ቤቱ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈፀሙ እና የቀረበባቸው ክስ በመጪው አገራዊ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል።
"ምንም ወንጀል እንዳልፈፀምን አቃቤ ሕግ ራሱ ያውቃል፤ እኛ ብንወጣ እና ምርጫው ላይ ብንሳተፍ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጥቅም ይኖረዋል" ሲሉ አቶ ጃዋር ተናግረዋል።
የችሎቱ ዳኛ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ፍትህ ይጓደላል የሚል እምነት እንደሌለው እና ክሱንም ከጊዜ ወደጊዜ እየተጣራ እንደሚሄድ ተናግረዋል።
ኦፌኮ ሰሞኑን ከፍተኛ የአመራሮቹና አባላቱ እንደታሰሩ፣ በተለያዩ ቦታዎች ቢሮዎች እንደተዘጉባቸው በመግለጽ በመጪው ምርጫ መሳተፍ እንደሚቸገር መግለፁ ይታወሳል።
እነ አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለ ገርባም በተደጋጋሚ ለችሎቱ የታሰሩት በፖሊቲካ አመለካካታቸው እና ምርጫ ላይ እንዳይታሰተፉ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ይገልፃሉ።
መንግሥት ግን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆነ እና በፖለቲካ አመላከከቱ የታሰረ እንደሌለ ይገልጻል።
በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ከሙዚቀኛው ሃጫሉ ግድያ በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ጃዋር መሐመድና በክስ መዝገባቸው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች 24 ሰዎች ተደራራቢ አስር ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበና ፀጋዬ ረጋሳ አገር ውስጥ የሌሎና በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ውስጥ ከተከሰሱት መካከል ናቸው።
የድምጻዊ ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረ ሁከት ጋር ተያይዞ ነበር እነአቶ ጃዋር መሐመድ በቁጥጥር ሥር የዋሉት።