ዐቃቤ ሕግ በእነአቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የክስ ማሻሻያ እንዲያቀርብ ታዘዘ

የአቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 21 ተከሳሾች ጉዳይ ዛሬ [ማክሰኞ] የተመለከተው ፍርድ ቤት ያቀረቡትን የክስ መከላከያ ውድቅ አድርጎ ዐቃቤ ሕግ የክስ ማሻሻያ እንዲያቀርብ አዘዘ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አንደኛ ችሎት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 21 ሰዎች ያቀረቡትን የክስ መከላከያ ውድቅ አድርጓል።

ተከሳሾቹ ከዚህ በፊት ፍርድ ቤቱ ክሳቸውን ለማየት ሥልጣን እንደሌለውና ወንጀሉ ተፈፀመ የተባለው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሆኑ እንዲሁም ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር ያላትን ልዩ ጥቅም በመጥቀስ ክሳቸው ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሄዶ መታየት አንዳለበት መከላከያ አቅርበው ነበር።

ከዚህም በተጨማሪም የአስተዳዳር አዋጅና የጦር መሳሪያ ቁጥጥር እንዲሁም የቴሌኮም ማጭበርበርን አስመልክቶ ተከሳሾች መከላከያ አቅርበው ነበር።

ክሳቸው ሕገ መንግሥቱ የሚሰጠውን እኩልነት በጣሰ መልኩ ነው የቀረበው በሚል በመከላከያ ላይ ያካተቱ ሲሆን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለዚህም ክስ መልስ ሰጥቶ ነበር።

በፍርድ ቤቱ ውሎ እነአቶ ጃዋር መሐመድም ያቀረቡት እነዚህ የክስ መከላከያዎች በችሎቱ በሙሉ ድምጽ ውድቅ ያደረገ ሲሆን በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክሶቹ ላይ ማሻሻያ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግም ክሶቹን አስተካክሎ እንዲያቀርብ የአንድ ወር ጊዜ እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው ግን ተቃውመውታል።

የሕግ የበላይነት ማስከበር፣ ለተከሳሾች ፍትሕ መስጠት፣ ተጎጂዎች ካሳ እንዲያገኙ ከታሰበም ጉዳዩ በፍጥነት እንዲታይ የተናገሩት ጠበቆች የተሰጠው ቀጠሮ እንዲያጥር ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ከተከሳሾች ውስጥ "መንግሥት ያሰረን ወንጀል ሰርተን ሳይሆን ምርጫ ላይ እንዳንሳተፍ ነው" ያሉት አቶ ሐምዛ አዳነ የቀጠሮው ጊዜ እንዲያጥር ጠይቀዋል።

ፍርድቤቱም የሁለቱን ወገን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ለጥር 14/2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።

ችሎት ላይ ምን ተባለ?

አለብን ካሉት የደኅንነት ስጋት በመነሳት ባሉበት ቦታ ጊዜያዊ ችሎት እንዲቋቋምላቸው የጠየቁና ባለፉት ሦስት ቀጠሮዎች ያልተገኙት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ በዛሬው ችሎት ላይ ተገኝተዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ቀጠሮ ላይ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ እንዳሳዘናቸው አቶ በቀለ ገርባና አቶ ጃዋር መሐመድ ተናግረዋል።

"እኛ አንቀርብም ያልን በማስመሰል 'በግድ ፍርድ ቤት ይቅረቡ' ተብሎ ትዕዛዝ መውጣቱ በጣም አሳዝኖናል፤ በዚህም መሰረት ለደኅንነታችን እየሰጋን ነው የምንመጣው" በማለት ወደ ፍርድ ቤት የመጡበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

አቶ በቀለ ገርባ ከደኅንነታቸው በተጨማሪ የሚደርስባቸው ጥቃት አገሪቷን ችግር ውስጥ እንደሚከታት በመናገር፣ ለሚያጋጥመው ችግር መንግሥትና ችሎቱ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

አቶ ጃዋር መሐመድም፣ አገሪቷ ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑ በመግለጽ "አንዳች ነገር ቢደርስብን፣ በዚህ ምክንያት አገሪቷ ላይ ችግር ቢመጣ፣ ሸኔ ሻዕብያ እያሉ ምክንያት መስጠት አያዋጣም። የምትጠየቁት እናንተ የሕግ ባለመያዎችና መንግሥት ነው" ብለዋል።

ዳኞቹ በበኩላቸው ትዕዛዝ በሚሰጡበት ወቅት ወደ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ የሚል እምነት ኖሯቸው መሆኑን በመጥቀስ "የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አታከብሩም የሚል እምነት የለንም። በግድ መቅረብ አለባቸው የሚለውን ትዕዛዝ የሰጠነው እንደ አማራጭ ነው" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እነአቶ ጃዋር መሐመድ ያቀረቡትን ክስ በስፋት ማየታቸውን በመናገር፣ የደኅንነታችሁን ሁኔታ እንከታተላለን። ወደዚህ የምትመጡበትንም ሁኔታ እንከታተላለን ብለዋል።

በሌላ በኩል የመንግሥት ሚዲያዎችና አንዳንድ የግል ሚዲያዎች ዘገባቸው ወገንተኝነት እንዳለበት ቅሬታ ያቀረቡት ደግሞ አቶ ደጀኔ ጣፋ ሲሆኑ፣ የመገናኛ ብዙሃኑ የፍርድ ቤት ውሎን በአግባቡ አንዲያቀርቡ "ይህንን ፍርድ ቤቱ እንዲያሳስብልን" በማለት ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ሚዲያዎቹ ችሎቱ ላይ የተባለውንና የችሎቱን ውሎ ብቻ እንዲዘግቡ አሳስቧል።

የአቶ ጃዋርና የ24 ሰዎች የክስ መዝገብ

በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ጃዋር መሐመድና በክስ መዝገባቸው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሰዎች የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በወጣው አዋጅ፣ የቴሌኮም ወንጀልን ለመከላከል በወጣው አዋጅ፣ የአስተዳደርና የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅንና የአገሪቱን ወንጀል ሕግ የተለያዩ አንቀጾችን በመተላለፍ ነው የተከሰሱት።

አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበና ፀጋዬ ረጋሳ አገር ውስጥ የሌሎና በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ውስጥ ከተከሰሱት መካከል ናቸው።

የድምጻዊ ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረ ሁከት ጋር ተያይዞ ነበር እነአቶ ጃዋር መሐመድ በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ከዚያም በኋላ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 24 ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ክስ መክፈቱ ይታወሳል።

ይኹን እንጂ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ለደኅንነታችን እንሰጋለን ብለው ሲናገሩ ነበር።

ስለዚህም ይህን ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ውስጥ ጊዜያዊ ችሎት እንዲቋቋምላቸው መጠየቃቸው ይታወሳል።