ኳታር ጎረቤቶቿ ለዓመታት የጣሉባትን ከባድ ማዕቀብ ሊያነሱላት ነው

የሀብታሟ አገር ኳታር ዋና ከተማ ዶሃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሀብታሟ አገር ኳታር ዋና ከተማ ዶሃ

ላለፉት ዓመታት በጎረቤቶቿ ማዕቀብ የተነሳ አበሳዋን ስታይ የነበረችው ባለጸጋዋ አገር ኳታር ማዕቀቡ ሊነሳላት እንደሆነ ተሰምቷል።

የኩዌይት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ተናገሩ እንደተባለው ሳዑዲ አረቢያ የየብስና የባሕር ድንበሯን በቅርቡ ለኳታር ክፍት ታደርግላታለች።

ይህ የብስራት ዜና የተሰማው የባሕረ ሰላጤው አገራት የትብብር መድረክ ጉባኤ ሊካሄድ አንድ ቀን ሲቀረው ነው።

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት ዜናው እውነት መሆኑንና የስምምነት ሰነድም እንደሚፈረም አረጋግጠዋል።

ኳታር ላለፉት 3 ዓመታት ተኩል ጎረቤቶቿ በጣሉባት ማዕቀብ የተነሳ ፈታኝ ጊዜያትን አሳልፋለች።

ኳታር የተጣለባትን ማዕቀብ አሜሪካ ጎረቤቶቿ ጋር በመነጋገር እንድታስነሳለት ደጅ ስትጠና ቆይታለች።

ዶናልድ ትራምፕ የሳዑዲ ወዳጅ በመሆናቸውና ኳታርም ለአሜሪካ ቁልፍ አጋር በመሆኗ ማዕቀቡን ታስነሳለች ተብሎ ሲጠበቅ 3 ዓመት ተኩል ቆይቷል።

ኳታር ላይ ማዕቀቡን የጣሉት አገራት ሳዐዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ኢምሬትስ፣ ኩዌይትና ግብጽ ሲሆኑ ማዕቀቡን በትንሽዋ ሐብታም አገር ኳታር ላይ የጣሉባት ሽብተኞችን ትደግፋለች፣ በአገራችን የተረጋጋ መንግሥት እንዳይኖር ተቃዋሚዎችን እየረዳት ታሴርብናለች በሚል ነው።

ብዙዎቹ አገሮች ከጸደይ የአረብ አብዮት ጀርባ የኳታር እጅ አለበት ብለው ማሰባቸውም አልቀረም።

ማዕቀቡን የጣሉባት አገራት ኳታር 13 ጥብቅ መመርያዎችን ተግባራዊ ካላደረገች ማዕቀቡን እንደማያነሱ ዝተው ነበር፤ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ኳታር ከጠላታቸው ኢራን ጋር የንግድ ግንኙነቷን እንድታቋርጥ የሚጠይቅ ነበር።

ሌላው ጥያቄያቸው አልጀዚራ ሚዲያን እንድትዘጋ የሚል ነው።

ማዕቀቡ ኳታር የአራቱን አገራት የአየር ክልል እንዳትጠቀም የሚያስገደድ ስለነበረ ለኳታር ቀላል አልሆነም።

ትንሽዋ አገር ኳታር ይህንን የትኛውም አገር ይቋቋመዋል የማይባለውን ማዕቀብ ተቋቁማ የቆየችው እጅግ ሀብታም አገር በመሆኗ ነው ይላሉ ተንታኞች።

ኩዌይት እና አሜሪካ ይህ ማዕቀብ እንዲነሳ ዘለግ ያለ ጊዜ ወስደው አገራቱን ለማግባባት ሞክረዋል ተብሏል።

አሁን ማዕቀቡን ለማንሳት አስገዳጅ የሆነው ምናልባት ሳዑዲ አረቢያ ጠላቶቼ ከምትላቸው ኢራንን ከመሰሉ አገራት ኳታር ይበልጥ ተቀራርባ መሥራት መጀመሯ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

እነሳዑዲ ኳታር ከኢራንና ከቱርክ ጋር ሽርክ ሆና ማየትን አይሹም።

የትራምፕ ሴት ልጅ ባል ጃሬድ ኩሽነር አገራቱ በኳታር ላይ ማዕቀብ በሚያነሱበት የስምምነት መድረክ ላይ ይገኛል ተብሏል።

ኩሽነር በገልፍ አረብ አገራት ጉዳይ ላይ ትራምፕን ወክሎ የዲፕሎማሲ ሥራ ሲሰራ የቆየ ነው። አረብ አገራት ከእስራኤል ጋር አዲስ ስምምነቶችን እንዲፈርሙ ጫና ከሚያሳድሩ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም አንዱ ነው።

የኳታሩ ኢሚር ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ ሳዑዲ ውስጥ በሚደረገው የገልፍ አገሮች ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ከንጉሥ ሰልማን ግብዣ ቀርቦላቸዋል።

ኳታር ከዚህ ጉባኤ በኋላ አገራቱ በየብስ፣ በአየርና በባሕር ቆላልፈው ያስቀመጧትን ኳታር ሁሉም ዓይነት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ያደርጋሉ ተብሏል።