ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕዳሴ ግድብ ፡ ሱዳን በሦስትዮሽ ውይይቱ ላይ ሳትገኝ በመቅረት ቅሬታዋን አሰማች
ለአንድ ወር ያህል ተቋርጦ ቆይቶ ትናንት ዕሁድ በተጀመረው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በበይነ መረብ በሚካሄደው ስብሰባ ሁለተኛ ቀን ላይ ሱዳን ሳትገኝ መቅረቷን ኢትዮጵያ ስታስታውቅ ሱዳን ደግሞ ቅሬታ አሰማች።
የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰኞ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በሦስቱ አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ውይይት ላይ ሱዳን ባለመገኘቷ ሳይሳካ እንደቀረ አመልክቷል።
የአፍሪካ ሕብረት የሰየማቸው ባለሙያዎች እንዲሁም ታዛቢዎች የተገኙበትን የሰኞው ውይይትን ኢትዮጵያ ሰብሳቢ የነበረች ሲሆን ሱዳን ሳትገኝ ቀርታለች ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ሙሌትና ቀጣይ ሥራ ላይ ዛሬ [ሰኞ] በተካሄደው የሦስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ቅሬታ እንዳላት የሱዳን ዜና አገልግሎት ሱና የአገሪቱን መስኖና ውሃ ሀብት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።
እሁድ የተካሄደውን ውይይት መሰረት አድርጎ ከሚኒስቴሩ የወጣው መግለጫ እንዳለው ሱዳን በዚያው ዕለት ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ ለማድረግ ብትጠይቅም ምላሽ ሳታገኝ የቀጥታ የሦስትዮሽ ድርድር ላይ እንድትሳተፍ ጥሪ ቀርቦላታል ብሏል።
ይህም ሱዳን በተሳትፎዋ ላይ ያላትን ቅሬታ ይፋ እንድታደርግ እንዳደረጋት ያመለከተው መግለጫ "ሱዳን የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ድርድሩን በማስተባበር በኩል ሰፋ ያለ ሚና እንዲሰጣቸው ያላትን ጽኑ አቋም ታረጋግጣለች" ሲል አጽንኦት መስጠቱን ሱና ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ ሱዳን በውይይቱ ላይ አለመገኘቷን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ "ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሰየማቸው ባለሙያዎች ባዘጋጁት ሰነድ ላይ ያሏትን የልዩነት ሃሳቦች ለሕብረቱ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር አሳውቃለች" በማለት ሰነዱን ለሦስትዮሽ ድርድር እንደግብዓት ለመጠቀም መስማማቷን አስታውሷል።
ጨምሮም የሰኞው ስብሰባ በአገራቱ መካከል ያለውን የልዩነት እና አንድነት ሃሳቦችን ለማጠናቀር የታሰበ እንደነበር በመጥቀስ ይህም በሱዳን አለመሳተፍ ሳቢያ ሳይካሄድ ቀርቷል ብሏል።
ሱዳን ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ለአንድ ወር ያህል ተቋርጦ የነበረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር እሁድ ዕለት ተጀምሮ በተካሄደበት ጊዜ የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ያቀረቡትን ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያና ሱዳን ሲቀበሉት ግብጽ ሳትቀበለው እንደቀረችና ውይይቱ እንደሚቀጥል ተገልጾ ነበር።
የግንባታው 78 በመቶ መጠናቀቁ የተነገረለትና በቅርቡ በከፊል ኃይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት መደረስ አለበት በሚል ሱዳንና ግብጽ ግፊት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ ባለፈው የክረምት ወር የግድቡን የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት ማከናወኗ ይታወሳል።
ግብጽ ከአባይ ወንዝ ላይ በማገኘው የውሃ መጠን ላይ መቀነስን ያስከትላል በሚል ጥያቄ በምታነሳበት በዚህ ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ፣ በካርቱም፣ በካይሮና በዋሽንግተን ውስጥ አገራቱ ተከታታይ ድርድሮች ቢካሄዱም አስካሁን መደምደሚያ ላይ አልተደረሰም።
በተለይ በአሜሪካ አሸማጋይነት ዋሽንግተን ላይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር መቋጫ ላይ ይደርሳል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ጥቅሜን የሚያስጠብቅ አይደለም በማለት ራሷን ከስምምነቱ ውጪ ማድረጓ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተጀመረው ውይይት እየተካሄደ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች እየተቋረጠ መልሶ ሲጀመር እዚህ ላይ ደርሷል።