ተቋርጦ የነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ተጀመረ

በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረውና የተቋረጠው ድርድር ትናንት አርብ መጀመሩ ተነገረ።

በደቡብ አፍሪካ ሊቀመንበርነት በአፍሪካ ሕብረት ተሳታፊነት በቪዲዮ የሚካሄደው የሦስቱ አገራት ድርድር መጀመሩን የሱዳን ዜና አገልግሎት ገልጿል።

የኢትዯጵያው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው ላይ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እንዳሰፈሩት የሦስትዮሽ ድርድሩ አርብ ከሰዓት በኋላ እንደጀመረና ቅዳሜም መቀጠሉን አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም ከአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ታዛቢዎች ባሉበት እተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ድርድሩ እስከ ሁለት ሳምንተ ለሚደርስ ጊዜ በየዕለቱ እተካሄደ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በሦስቱ አገራት መካከል ከሳምንት በፊት ለቀናት ሲካሄድ ቆይቶ በተቋረጠው ድርድር ላይ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ከስምምነት ላይ መደረሱ የተገለጸ ሲሆን ቁልፍ የሆኑ ሕጋዊና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ነው ውይይቱ መቋረጡን አገራቱ አሳውቀው ነበር።

በተለይ ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራ በሐምሌ ወር እንደምትጀመር ዕቅድ በያዘችበት ሁኔታ በቀሪ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ የውሃ ሙሌት እንዳይጀምር በሚል ከግብጽና ከሱዳን የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ድርድሩ ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።

ትናንት አርብ መልሶ ተጀምሮ ዛሬም እንደሚቀጥል በተነገረው በዚህ የሦስቱ አገራት ድርድር ላይ በግድቡ ዙሪያ ያሉ መሰረታዊ የቴክኒክና የሕግ ልዩነቶች የመወያያ ጉዳዮች እንደሚሆኑ የግብጽ የመስኖ ሚኒስቴር መግለጹን አል አህራም ዘግቧል።

ሚኒስቴሩ በአዲሱ ዙር የድርድሩ የመጀመሪያ ቀን ውይይት ዙሪያ ባወጣው አጭር መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የጀመሩት በቪዲዮ አማካይነት የሚያደርጉት ውይይት ዛሬ ቅዳሜም ይቀጥላል።

ሦስቱ አገራት ባካሄዱት የመጀመሪያ ቀን ድርድር ላይ ደቡብ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ሕብረት ጽህፈት ቤት ተወካዮችና የህግ ባለሙያዎች፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በታዛቢነት መሳተፋቸውን የግብጽ የመስኖ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ቀደም ያለው ከሰኔ 2 አስከ 10/2012 በሦስቱ አገራት መካከል በቪዲዮ አማካይነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቀርቦ ባለፈው ሰኞ ምሽት ውይይት እንደተካሄደበት ይታወሳል።

ቀደም ብሎ የተደረገው ውይይት ከተቋረጠ በኋላ በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና ግብጽ መሪዎች በተደረገው ውይይት አገራቱ ድርድራቸውን ጀምረው በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።

ግብጽና ሱዳን ድርድሩ ተካሂዶ ከስምምነት ላይ ሳይደረስ በፊት ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራ እንዳትጀምር ቢወተውቱም ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ ግን ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለመጀመር ዕቅድ የያዘች መሆኑን አመልክቶ በዚህ ጊዜም ቀሪ የግንባታ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ ገልጿል።

ጉዳዩ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት መሄዱን ያልተቀበለችው ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት በሱዳንና በግብጽ ላይ እንደማያስከትል ለምክር ቤቱ ገልጻ የግድቡ ዋነኛ ግብ ልማት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥታ ነበር።

ባለፈው ሳምንት የአገራቱ መሪዎች በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ባደረጉት ውይይት ጉዳዩ በአህጉሪቱ የበላይ አካል በአፍሪካ ሕብረት የተያዘ በመሆኑ ይህንኑ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ለማሳወቅ መስማማታቸው ይታወሳል።

አስር ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምሰት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።