ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአንድ ጊዜ በሁለት ዲግሪ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ሙከረም
ሙከረም አሊ ኑር ይባላል። በኮምፒውተር ሳይንስ እና ኢንጂነሪንግ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ እና ኮሙኒኬሽን ኢንጂነሪንግ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል።
3.93 በማምጣት የግቢውን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቦ ዋንጫ ተሸልሟል።
ሙከሪም በአንድ ጊዜ በሁለት ዲግሪ ነው የተመረቀው። በዩኒቨርስቲው አንድ ተማሪ የተሻለ ውጤት ካለው ሁለት ዲግሪዎችን በተመሳሳይ ጊዜ መማር ይችላል።
3.5 እና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ሁለተኛ የትምህርት ክፍል በመምረጥ መማር ይችላሉ። ሁለት ዲግሪ ሲወሰድ ትምህርቶቹ ተመሳሳይ እንዲሆኑ ይጠበቃል። ይህ ማለት ደግሞ የሚወሰደው ትምህርት ብዛት ስለሚቀንስ በአምስት ዓመት ውስጥ መጨረስ ይቻላል ማለት ነው።
ከሙከሪም ጋር በሁለት ዲግሪ የተመረቁት 33 ተማሪዎች ናቸው።
የመጀመሪያው ቢ...
በኮምፒውተር ሳይንስ እና ኢንጂነሪንግ 170 የትምህርት ሰዓት (ክሬዲት አወር)፣ በኤሌክትሮኒክስ እና ኮሙኒኬሽን ኢንጂነሪንግ 23 የትምህርት ሰዓት (ክሬዲት አወር) ወስዶ ትምህርቶቹን በአምስት ዓመት ውስጥ እንዳጠናቀቀ ይናገራል።
ሙከሪም አብዛኛውን ትምህር 'ኤ' አግኝቶ ነው የተመረቀው።
"አንድ ሁለት ቢ ይኖራል። ሌላው ኤ እና ኤ ማይነስ ናቸው" ይላል።
ኤ ማግኘት የለመደው ተመራቂው ቢ ሲያገኝ እንደሚያዝን ይናገራል። ለመጀመሪያ ጊዜ ቢ ያገኘበትን ጊዜም እንዲህ ያስታውሳል. . .
"የመጀመሪያውን ቢ ያገኘሁት የመጀመሪያ ዓመት፣ ሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ላይ ነበር። ከዚያ ትምህርት ውጭ የሁሉንም ውጤት አይቼ ነበር። ሁሉም ኤ እና ኤ ቻርጅ ነበሩ። እና የቀረችዋ አንድ ኮርስ ኤ ብትመጣ ኖሮ 4 ነበር የማመጣው። እሷን በጣም ጠብቄ ነበር። በእርግጥ ጫናዎች ስለበዙብኝ እንዳልሰራሁ ገብቶኝ ከኤ በታችም ጠብቄ ነበር።
ቢ ሳመጣ በጣም ነው ውስጤ የተነካው። ያዘንኩበት ጊዜ ነው። ወደፊት እንደዚያ አይነት ነገሮች እንዳይደገሙ የተሻለ ለመሥራት ነበር ያቀድኩት።"
ሁሌም ወደ ፈተና ከመግባቱ በፊት በጎ ነገር እንደሚያስብ ይናገራል። "ብዙ ጊዜ ነገሮችን የማቅለል ባህሉና ልምዱ አለኝ" የሚለው ሙከረም፤ ቀለል አድጎ የማንበብና ፈተናውን እንደሚሠራ እርግጠኛ የመሆን ልማድ እንዳዳበረ ያስረዳል።
የሚያነበውና የሚያውቀው ሐሳብ ላይ ያተኩራል። ፈተና ከመጀመሩ በፊት ውጤቱ ጥሩ እንደሚሆን እርግጠኛ ሆኖ ይገባል።
"ሳልገባም፣ ስገባም፣ ከወጣሁም በኋላ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ እጠብቃለሁ" የሚለው ተመራቂው ፈተና ላይ ሳለ ደግሞ ደስተኛ ሆኖ የተሻለ ውጤትን ይጠብቃል።
ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ የዋንጫ፣ ሜዳሊያ እና ላፕቶፕ ሽልማቶች አግኝቷል። ከሁሉም በላይ ግን ከሰዎች ያገኘው ከበሬታ ያስደስተዋል።
"የሰውን ምላሽ ሳይ ትልቅ ውጤት እንዳስመዘገብኩ ነው እየተሰማኝ"ያለው ሙከሪም፣ "ከሰዎች የምታገኘው ሞራል በጣም ደስ የሚል ነገር ነው" ሲል ያክላል። "ዩኒቨርሲቲው የማስተርስ ሙሉ ስኮላርስፕም ሰጥቶናል።"
ከተመረቀ በኋላ ዋንጫውን ይዞ ኮምፒውተሩን ለመውሰድ ወደ ቤተ ሙከራ አምርቶ እንደነበር ያስታውሳል።
ታዲያ ቤተሰቦቹ ሲደውሉት "ላብ ነኝ" ብሎ ሲመልስላቸው ለጥናት የሄደ መስሏቸው "በምርቃቱ ቀን ያጠናል" ብለው አስበው እንደነበርም አውግቶናል።
"ላይብረሪ ብዙም አልጠቀምም"
ሙከሪም ብዙም ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ማጥናት አያዘወትርም። እንዲያውም ትኩረቱ የቡድን የቤት ሥራዎች ላይ ነው።
"ዶርም ከጓደኞቼ ጋር እየተረዳዳሁ። ሁላችንም የየራሳችን አቅም አለን። እኔ ያለኝን አቅም ለሌሎች አሳያለሁ፤ አስረዳለሁ። እነሱም ደግሞ ከእኔ የተሻለ አቅም ስላላቸው ባላቸው አቅም እኔን ያስረዱኛል። ይህ የግሩፕ ጥናት ከአንደኛ ዓመት ጀምሮ እስከምንመረቅበት ድረስ ስናደርግ የነበረው ነው።"
ከክፍል ከወጡ በኋላ ከማጥናት ይልቅ ክፍል ውስጥ የማተኮር ልማድ ያለው ሙከሪም፤ "ክፍል ውስጥ ያልተረዳሁትን ነገሮች እዚያው ነው ጨርሼ የምሄደው" ይላል።
እሱና ጓደኞቹ ከእነርሱ በታች ያሉ ተማሪዎችን ያስተምራሉ። ይህም የበለጠ እንዲያነብ አግዞታል።
ከዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ እንቅጠርህ ያሉት ድርጅቶች እንደነበሩና እሱ ግን በትምህርቱ የመግፋት ሐሳብ እንዳለው ይናገራል።
በዩኒቨርሲቲው የፌስቡክ ገጽ ላይ ውጤቱን አይተው ያደነቁት፣ ያበረታቱት እንዳሉም ያስታውሳል።
ቀጣይ እቅዱ በአገር ውስጥና በውጪም ትምህርቱን ገፍቶበት በሙያው ማኅበረሰቡን ማገልገል ነው።
"ኢትዮጵያውያኖች እንደ ማኅበረሰብ ብዙ ችግር አሉብን። እነዚያን ነገሮች ባለኝ እውቀት መፍታት እና ማኅበረሰቡን የመጥቀም ትልቅ ፍላጎት አለኝ። ግን እሱን ለማድረግ እራሴ ጠንካራ እውቀት ሊኖረኝ ይገባል በሚል አሁን ትምህርቱ ላይ ነው ያተኮርኩት። ከዚያ በኋላ ግን እነዛን ተጠቅሜ የመሥራት ሃሳቡ አለኝ።"
ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ሶፍትዌሮች መሥራት ህልሙ ነው።
በኮምፒውተር ሳይንስ እና ኢንጂነሪንግ፣ በሰው ሠራሽ ክህሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ)፣ በማሽን ለርኒንግ እና ዳታ ሴንስ ዘርፎች ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያምናል።
በአይሲቲ ዘርፍ ላለፉት አምስት ዓመታት በውድድር ሲሳተፍ እንደነበረና ይህንን በአዳማ ዩኒቨርስቲ እንደጀመረው ይናገራል።
ወደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የማስፋፋት እቅድም አለው።
"አባቴ ነጋዴ እንድሆን ይፈልግ ነበር"
የሙከሪም አባት ባለ ሱቅ ናቸው። እስከ 12ኛ ክፍል ሲማር ከትምህርት ሰዓት ውጪ ሱቅ ውስጥ ይሠራ ነበር። አባቱ ንግድ ላይ እንዲያተኩር ይፈልጉ እንደነበርም ይናገራል።
"ያደግኩት ንግድ ላይ ነው። አባቴ ሱቅ ውስጥ እንድሠራ ይፈልግ ነበር። እስከ ስምንተኛና ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ያሉትን ውጤቶች ሲያይ ግን ወደ ትምህርት ብታደላ የሚል ነገር አመጣ" ሲል ያስታውሳል።
ቤተሰቡ የዩኒቨርስቲ ውጤቱን ሲያዩ ያሉትንም እንዲህ ያስታውሳል. . .
"ደስታቸውን መግለጽ ነው ያቃታቸው። ያኔ ያሰብነው ነገር [ንግዱ] ትክክል እንዳልነበረ ነው ያሰቡት። አሁን ደስተኛ ናቸው። ቤተሰቦቼ የነበረውን ብዙ ጫና ተቋቁሜ በማለፌ ደስተኛ ናቸው።"
"ቤተሰብን የመርዳት እና የእነርሱን ሃቅ የመጠበቅ ግዴታ ይኖርብኛል። ከሥራዬና ከትምህርቴ ጋር የማይጋጭብኝ ከሆነ ለማገዝ ፍቃደኛ ነኝ" የሚለው ተመራቂው፤ ከዚህ በኋላ ምናልባትም ከትምህርት ለእረፍት ወደቤት ሲሄድ እንደ ድሮው ቤተሰቦቹን በሱቅ ሥራው ያግዝ ይሆናል።
በእርግጥ ከቤተሰቡ በተጨማሪ ሌሎችንም የሚያግዝ ሰው ነው።
ዩኒቨርስቲ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ለአምስት ዓመታት ተማሪዎችን አስተምሯል።
"ያለኝን እውቀትና ልምድ ለሌሎች የማስተላለፍ ግዴታ አለብኝ ብዬ ስለማስብ ሁሌም አስተምር ነበር። በዚያ የተነሳ ከብዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት ፈጥሬያለሁ። በተማሪዎች ዘንድ ትልቅ ተወዳጅነት ነው ያለኝ። ሁሉም ሰው እውቀቱን ለሌሎች ማካፈል አለበት ብዬ ነው የማስበው" ሲልም ምክሩን ያካፍላል።
አብዛኛው ተመራቂ በቀላሉ ሥራ እንደማያገኝ ከግምት በማስገባትም፤ ተመራቂዎች መቀጠርን ብቻ ግብ ከማድረግ የራሳቸውን ሥራ መፍጠር አለባቸው ይላል።
"ግዴታ ቅጥር መጠበቅ የለብንም። ባለኝ እውቀት ምን መሥራት እችላለሁ? ማኅበረሰቡ ላይ ምን ችግር አለ? ምን እድልስ አለ? የሚለውን በደንብ ካየን ያንን መፍታትና ወደ ሥራ መቀየር እንችላለን።"