ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ከ32 ዓመታት በኋላ የጋዳፊ 'ቦምብ ቀማሚ' ነበር ያለችውን ሊቢያዊ ከሰሰች
አሜሪካ ለሦስት ዐሥርታት እንቆቅልሽ ሆኖ የቆየውን ክስ በአንድ ሊቢያዊ ላይ መስርታለች።
ጉዳዩ በታሪክ 'የሎከርቢው ፍንዳታ' ተብሎ ከሚታወቀው የሽብር ጥቃት ጋር የተያያዘ ነው።
ስኮትላንድ ሰማይ ላይ የዛሬ 32 ዓመት በፈነዳውና 190 አሜሪካዊያንን ሕይወት በቀጠፈው የሽብር ጥቃት አውሮፕላኑን ወደ ፍርስራሽነት የቀየረውን ቦምብ በመቀመም እጁ አለበት ያለችውን ሊቢያዊ በሽብር ከሳዋለች።
ሊቢያዊው አቡ አጊላ መሐመድ አልመሱድ ለቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ የግል 'ቦምብ ቀማሚ' ነበር ተብሏል።
በተጨማሪም ግለሰቡ በሊቢያ የደኅንነት መኮንን እንደነበረም ደርሼበታለሁ ብላለች አሜሪካ።
'ፓን አም 103' የበረራ ቁጥር የነበረው ቦይንግ 747 የመንገደኞች አውሮፕላን የዛሬ 32 ዓመት በስኮትላንድ ሎከርቢ ሰማይ ላይ ሲጋይ በድምሩ 270 ተሳፋሪዎች ነበር ያለቁት።
ይህ አደጋ ከደረሰ በኋላ በሊቢያው ጋዳፊና በምዕራባዊያን ዘንድ ለረዥም ጊዜ የቆየ የዲፕሎማሲ መኳረፍ አስከትሎ ነበር።
ጋዳፊ በመጨረሻም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ በመስጠት ጉዳዩ እንዲቋጭ መሞከራቸው አይዘነጋም።
ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ የአሜሪካ አቃቢ ሕግ ዊሊያም ባር ተጠርጣሪው አል መስኡዲ ከሊቢያ ተላልፎ እንዲሰጣቸው እንደሚጠይቁ ይፋ አድርገዋል።
ይህ የዛሬ 32 ዓመት የተደረገው በረራ ከሎንዶን ወደ ኒውዮርክ ይበር በነበረ አውሮፕላን ላይ በሳምሶናይት የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ነው በታሪክ ውስጥ እንቆቅልሽ የሆነ ውስብስብ ምርመራን የጋበዘው።
በብሪታኒያ ታሪክ እንዲህ ዓይነት የከፋ ጉዳት ያደረሰ የሽብር አደጋ የለም። በአሜሪካ ታሪክም የሎከርቢው ፍንዳታ 2ኛው የከፋ የሽብር ተግባር ተደርጎ ነው የሚታየው።
አውሮፕላኑ ከሎከርቢ ሰማይ ሲከሰከስ ምድር ላይ አገር ሰላም ብለው ሕይወታቸውን ይመሩ የነበሩ 11 ስኮትላንዳዊያንም ተገድለዋል።
አውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት 270 ሰዎች ውስጥ 35 የሚሆኑት ትምህርታቸውን ተከታትለው ለገና ወደ አገራቸው ይመለሱ የነበሩ አሜሪካዊያን ተማሪዎች ነበሩ።
የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የአሁኑ የአሜሪካ አቃቢ ሕግ ዊሊያም ባር ያን ጊዜ አደጋው በደረሰበት ወቅት በጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ስር ባለሥልጣን ነበሩ፤ የፍንዳታውን ጉዳይ ይከታተሉ የነበሩት እርሳቸው ነበሩ።
ያን ጊዜም አቃቢ ሕግ መሥሪያ ቤት ውስጥ ይህንን ወንጀል እንዲመረምሩ ሮበርት ሙለርን መድበዋቸው ነበር።
አሁን ሮበርት ሙለር የሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብነት የሚመረምረው ቡድን መሪ በመሆን ነው የሚታወቁት።
ይህ አሳዛኝ አደጋ 32ኛው ዓመት በሚዘከርበት ወቅት ዊሊያም ባርና ሚስተር ሙለት ተገኝተዋል።
ከዚህ ቀደም ከሎከርቢው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ሁለት ሊቢያዊያን ተከሰው አንዱ በነጻ ሲለቀቅ ሌላኛው ተጠርጣሪ እድሜ ይፍታህ ተፈርዶበት እንደነበር አይዘነጋም።
ሆኖም ወንጀለኛው በካንሰር በመታመሙ በእዝነት ፍትሕ ወደ ሊቢያ አገሩ ሄዶ የቀሩትን ወራት በነጻነት እንዲያሳልፍ ተደርጎ ነበር።
ሆኖም ጥቂት ጊዜ በትሪፖሊ ከኖረ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አሜሪካ አሁን ደረስኩበት ያለችው አል መስኡዲ እስከዛሬ ተከሶ አያውቅም ነበር።
ይህን ቦምብ ቀማሚ ተጠርጣሪ ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ልትደርስበት የቻለችው የጋዳፊን ሞት ተከትሎ ሊቢያን የተቆጣጠረው ቡድን አንድ የቀድሞ ደኀንነት ባልደረባን ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ጊዜ ያልተጠበቀ ነገር በመናዘዙ ነው።
ዊሊያም ባር ግለሰቡ የተናዘዘውን ጉዳይ የሊቢያ ደኀንነት መሥሪያ ቤት ቅጂውን እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ይህ ተናዘዘ የተባለው ግለሰብ ደግሞ አሁን ክስ የተመሰረተበት አልመስኡድ ነው።
ዊሊያም ባር እንዳሉት አል መስኡድ ቦምቡን ከቀመመ በኋላ ጋዳፊ ለሰራው ጀብዱ በግል ለሰራው ምሥጋናን ችረውታል።
"ጊዜው ይርዘም እንጂ ከአሜሪካ ፍትሕ ሊያመልጥ የሚችል ማንም የለም" ብለዋል ዊሊያም ባር።
የሊቢያ መንግሥት አል መስኡድን አሳልፎ ስለመስጠት ያለው ነገር የለም።