ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሚበሩ መኪኖች እየመጡ ነው - ዓለምን ሊቀይሩ ተዘጋጅተዋል
በፈረንጆቹ 1982 የተሠራው ብሌድ ራነር የተሰኘው ፊልም ሎስ አንጀለስ የተሰኘችውን የአሜሪካ ብርቅርቅ ከተማ መቼቱ አደርጎ ነው የተሠራው።
ፊልሙ 82 ላይ ሆኖ 2019 ተሻግሮ ይመለከታል። ፊልሙ ላይ መኪናዎች ሲበሩ፤ ሰዎች እርስ በርስ ሲባረሩ ይታያል።
ከዚህ ሲኒማ በኋላ ዓለም በሳይንሱ ዘርፍ አድጋለች፤ ተመንድጋለች።
ሆሊውድ 2019 የማይደርስ መስሎታል፤ እነሆ ደረሰ። ደርሶም አለፈ።
እርግጥ ነው በራሪ መኪናዎች ጣራችንን ታከው ሲያልፉ አላየን ይሆናል። ነገር ግን መምጫቸው ቅርብ እንጂ ሩቅ አይደለም።
በራሪ መኪናዎች የምንኖርባትን ዓለም እስከወዲያኛው ሊቀይሩ ይችላሉ።
የመኪና አንቀሳቃሽ ባትሪ፤ ቁሳቁስ እና ኮምፒውተር ሳይንስ ዕለተ'ለት በፍጥነት እየተለወጡ ነው።
በቅርቡ ሰማይ ላይ የምናያቸው መኪናዎች ልክ 'ብሌድ ራነር' እንደተሰኘው ፊልም ላይሆኑ ይችላሉ። ቅርፃቸውን ቀይረው መምጣታቸው ግን አይቀሬ ነው።
ከትናንሽ አውሮፕላኖችም ያነሱት በራሪ መኪናዎች ክንፍ የላቸውም፤ ቸርኬ እንጂ። ይህ ደግሞ ሲነሱና ሲያርፉ እንዲያመቻቸው ታስቦ የተደረገ ነው።
ቸርኬዎቹ አስፋልት መንገድ ላይ እንደምናያቸው መኪናዎች ቀጥ ያሉ አይደሉም። ጋደል ያሉ ናቸው።
በራሪ መኪናዎች ያስፈለጉበት ምክንያት ግለፅ ነው። ሕይወትን ለማፍጠን።
ከቤት ወደ ሥራ፤ ከሥራ ወደቤት የምንሄድበትን ጊዜ ለማሳጠር ያለሙ ናቸው። ቀጠሮ ቦታችን ከች በኮሮኮንች ቀርቶ ከላይ እንደ ድንገቴ ዝናብ ዱብ እንድንል ያደርጉናል።
በተለይ ደግሞ ትራፊክ ለሚጨናነቅባቸው ከተማዎች በራሪ መኪና ወደር የለሽ መድኃኒት ነው።
በአሁኑ ወቅት በራሪ መኪና ለማምረት ወዲያ ወዲህ የሚሉ በርካታ ፋብሪካዎች አሉ።
1.5 ትሪሊየን ዶላር መድቦ በራሪ በፈረንጆቹ 2040 መኪና ለማምረት እየጣረ ያለውን ኡበር የተሰኘውን የታክሲ ኪራይ ድርጅት ጨምሮ በርካቶች ከቀን ቀን እመርታ እያሳዩ ነው።
የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ድርጅቶች ደግሞ ይህን ከግምት ውስጥ ያስገባ አዲስ ፖሊስ ለማርቀቅ ምክክር ላይ ናቸው።
ጀርመን ውስጥ የሚገኘው ቮሎኮፕተር የተሰኘው ፋብሪካ ቮሎሲቲ የተባለ ያለ አብራሪ የሚበር የሰማይ ታክሲ ሰርቷል።
የድርጅቱ ምክትል ሊቀ መንበር ፋቢዬን ኔስትማን 'እኛ የመጀመሪያዎቹ ነን' ይላሉ።
ለጊዜው ቮሎሲቲ ለአንድ ሰው ብቻ የሚሆን ጋቢና ተበጅቶለታል። ይህ ማለት ደፍሮ የሚሳፈር ኪሶ ወፈር ያለ መሆን አለበት ማለት ነው።
ነገር ግን ድርጅቱ ለተጠቃሚዎች በዋጋም በደህንነትም ምቹ የሆነ በዘጠኝ ባትሪዎች የሚሠራ በራሪ መኪና ለመፈብረክ አልሟል።
ይህ በራሪ መኪና ልክ እንደ አውሮፕላን ተቆጣጣሪ ያለው መንደርደሪያ ይዘጋጅለታል። በሰዓቱ ይነሳል፤ በሰዓቱ ያርፋል።
ቮሎሲቲ በራሪ መኪናዎች በመጪው የፈረንጆቹ 2022 የሙከራ በረራ ለማድረግ ተልመዋል።
የመጀመሪያዎቹ በረራዎች ቲኬት 300 ፓውንድ [140 ሺህ ብር] ናቸው ተብሏል። ነገር ግን ቀስ በቀስ ዋጋቸውን ተመጣጣኝ እናደርጋለን ይላሉ ኔስትማን።
ሌሎች ኩባንያዎችም ከመኪና [መሬት ላይ ከሚበረው] አምራች ፋብሪካዎች ጋር ተጣምረው በሰማይ በራሪ መኪና ለመሥራት እየተንደፋደፉ ነው።
ስካይድራይቭ የጃፓን ኩባንያ ነው። ይህ ኩባንያ ከቶዮታ ጋር ተጣምሮ በኤሌክትሪክ የሚሠራ የሰማይ ታክሲ ሠርቶ ለመሞከር አቅዷል
መኪናዋ በዓለም ትንሿ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ትሆናለች ይላሉ።
ድርጅቱ ከወራት በፊት ኤስዲ-03 ሲል የሰየመውን አብራሪ ያለው መኪና በተሳካ ሁኔታ ሞክሯል።
የበራሪ መኪናዎችን ዕድገት ተከትሎ ተያያዥ ቴክኖሎጂዎችም እያደጉ ነው። የሞተር ድምፅ መቀነሻ፤ ረዥም ዕድሜ ያለው ባትሪና የመሳሰሉት ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋል።
ነገር ግን በራሪ መኪናዎችን እንዲሁ ሠርቶ ሰማይ መስቀል ቀላል አይደለም።
የመጀመሪያው ነገር የመኪናዎቹ ደህንነት ምን ያክል ነው የሚለው ነው። ቀጥሎ ሰዎች እንዲሳፈሯቸው ማሳመን ይጠይቃል።
ደህንነታቸው ስለተረጋገጠ ብቻ ሰዎች ይሳፈራሉ ማለት አይደለም። በራሪ መኪናዎች የወደፊቱ ዓለም ዜማ መቃኛ ናቸው ብሎ ሰዎችን ማሳመን ቀላል አይሆንም።
አሁን ከአድማስ አድማስ የምንፈላሰስባቸው አውሮፕላኖች ቁጥጥር የሚደርግላቸው መሬት ላይ ካለ ማማ የተሰቀሉ ተቆጣጣሪዎች ናቸው።
በራሪ መኪናዎች ግን ሰው አልባ በሆነ ቴክኖሎጂ ነው ወጥተው የሚገቡት።
ይህ ቴክኖሎጂ ሰማይ ላይ ያለውን ሁሉ ያውቃል። ስንት ሰዓት መነሳት፤ መቼ ማረፍ እንዳለበት ይረዳል። ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅዳሚያ ይሰጣል። ሰማይ ላይ 'ዜብራ' የእግረኞች ማቋረጫ ቢኖር እንኳ ቆሞ ለማሳለፍ የሚሰንፍ አይደለም ይሉለታል።
በራሪ መኪናዎች መሬት ላይ የሚተራመሱ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ሊቀንሱ ይችላሉ። ሰዓት ይቆጥባሉ።
ችግሩ ግርግሩ ከመሬት ወደ ሰማይ እንዳይሸጋገር ነው። ይህን የሰማይ ትራፊክ የሚቆጣጠር ቴክኖሎጂ ማዳበር የግድ ነው።
አልፎም መሬት ላይ ያሉ ሰዎች በበራሪ መኪናዎች አደጋ እንዳይቀጠፉ ማረጋገጫ መኖር አለበት።
በራሪ መኪናዎች ወደ ሰማይ ምን ያክል ጫማ ከፍ ብለው ነው መብረር ያለባቸው የሚለው ሌላው አከራካሪ ጉዳይ ነው።
ይህን የተመለከቱ ሕጎች ከወዲሁ አሜሪካና አውሮፓውያን ሃገራት ማርቀቅ ጀምረዋል።
በጠቅላላው በራሪ መኪናዎችን ቀና ብለን እንድናይ ወይም እንድንሳፈር በርካታ ኢንዱስትሪዎች ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው መረዳት አያዳግትም።
በራሪ መኪናዎች ከወፎች ጋር እየተጋፉ መብረር ጀመሩ ማለት ከተሞች ቅርፃቸውን መቀየር አለባቸው ማለት ነው።
ሕንፃዎች አደግ አደግ ብለው ለበራሪ መኪናዎች ማረፊያ የሚሆን ደረቱ ሰፋ ያለ ጣራ ሊኖራቸው ይገባል።
መሬት ያሉ መኪናዎች ቁጥራቸው ቀነሰ ማለት ደግሞ ለአረንጓዴ መስክ የሚሆን ትርፍ ቦታ ተገኘ ማለት ነው።
ብሌድ ራነር እንደተነበየው በ2019 መኪናዎች መብረር አልጀመሩ ይሆናል። ከአስርና ሃያ ዓመታት በኋላ ግን የመኪናዎችን ብልት ቀና ብለን ማየታችን አይቀሬ ይሆናል።