ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እያወዛገበ ያለውን የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር በጨረፍታ
ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሁለት አገሮችን ያወዛገበ ድንበር፤ ከፍ ያለ የእርሻ ልማትና ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች የሚደምቁበት አካባቢ ነው።
በሁለቱም አገሮች የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪ ድንበርተኞች የይገባናል ጥያቄን ያነሱበታል፡፡ ይህ ለረዥም ዘመን የዘለቀ ጉዳይ ነው።
ለመሆኑ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር መልክ ምን ይመስላል?
ባለፈው ሳምንት በርካታ የሱዳን ወታደሮች ከኢትዮጵያ በኩል በተሰነዘረ የሚሊሻ ጥቃት መገደላቸው ተዘግቧል።
ካርቱም ክስተቱን "የደፈጣ ጥቃት" ስትል ጠርታዋለች፤ ድርጊቱ የተፈጸመው በሚሊሻዎች እንደሆነ ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኩል ክስተቱ ያልተስተባበለ ሲሆን "ድንበር ጥሰው በገቡ ኃይሎች ላይ የተወሰደ ራስን የመከላከል አስፈላጊ እርምጃ ነው" ብለውታል።
እንዲህ ዓይነት የድንበርተኞች ግጭት በተደጋጋሚ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ ይከሰታል። ግጭቱ ቦታው የእኛ ነው በሚሉ ኢትዮጵያዊያን አራሽ ገበሬዎች እና "የለም አካባቢው የእኛ ነው" በሚሉ የሱዳን ጎረቤቶቻቸው መካከል የሚከሰት ነው።
ይህ ክስተት የተሰማው ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል የተካሄደው ሕግን የማስከበር ወታደራዊ እርምጃ መጠናቀቁን በገለጹ ማግስት መሆኑ ነገሩን ላልተረጋገጡ ፖለቲካዊ ትርጓሜና መላምቶች አጋልጦታል።
የፌዴራል መንግሥት ወታደሮች መቀለን መቆጣጠራቸው እንዲሁም ጦርነቱን ተከትሎ 50ሺህ ዜጎች ወደ ሱዳን መሰደዳቸው የቅርብ ሳምንት ትኩስ ክስተት ነው።
የድንበር ግጭቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትዊተር ሰሌዳቸው፤ "እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በሁለቱ አገሮች ያለውን ጥብቅ ቁርኝት አይበጥሰውም፤ እኛ ሁልጊዜም ችግሮቻችንን በውይይት ነው የምንፈታው" ብለዋል።
ሁለቱ አገሮች ዛሬ ማክሰኞ ይህን ለዘመናት ያልተፈታውን የድንበር ችግር በተመለከተ ንግግር ይጀምራሉ ተብሏል። ይህንንም የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጽሕፈት ቤት እሑድ ዕለት ነው ቀደም ብሎ ያስታወቀው።
ለመሆኑ ከዚህ ድንበር ጋር በተያያዘ ያለው ታሪክ ምንድነው?
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚጋሩት ድንበር ርዝመት 750 ኪሎ ሜትር ያካልላል። ነገር ግን ይህ ድንበር አብዛኛው ርቀት ግልጽ በሆነ መንገድ መሬት ላይ አልተመላከተም።
ይህን ለማሳካት ተደጋጋሚ ንግግሮች ተጀምረው በተደጋጋሚ ተቋርጠዋል።
አሁን ኢትዮጵያና ሱዳን ያሉበት አካባቢ ታሪካዊ ሁኔታዎች ከብሉ ናይል እና አትባራ ወንዞች ጋር በአንድም በሌላም መልኩ የተጋመዱ ናቸው።
እነዚህ ወንዞች ሁለቱ ሕዝቦች በንግድና በሌሎች መልኮች እንዲገናኙ ለዘመናት ምክንያት ሆነው የቆዩ ናቸው። ነገር ግን ንግድ ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ግጭቶችም መነሻ ናቸው፡፡ በተለይም ድንበር ላይ ለሚነሱ ግጭቶች።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የቅኝ ገዢዎች ያበጇቸው ድንበሮች ሱዳንን፣ ግብጽንና ሌሎች የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ አገራትን የአሁን ቅርጽና መልክ ፈጥረውላቸዋል።
ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ የተባሉ ተመራማሪ፤ "የአፍሪካ ቅኝ ግዛት ዘመን ድንበሮች በተለይም የሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ" በተሰኘና በእንግሊዝኛ በተጻፈ ጥናታቸው እንደገለጹት የሁለቱ አገሮች ድንበር የአሁን ጊዜ ወሰን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1902 እና በ1907 የተደረጉ የአንግሎ-ኢትዮጵያ የካርታ ላይ ምልከታ ስምምነቶችን መሠረት ያደረጉ ናቸው።
በቅኝ ግዛት ወቅት በሱዳንና በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለተመላከቱ ድንበሮች ኃላፊነቱ ተሰጥቶት የነበረው ሁነኛ ሰው የአይሪሽ ተጓዥና አሳሽ የነበረው ቻርለስ ግዊይን ነበር።
የሱዳን ገዳሪፍና ብሉ ናይል ግዛቶች ከአማራ ክልል ጋር ይዋሰናሉ። በ1908 ነበር በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ድንበር የተሰመረው።
መልካሙ ዜና በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መካከል ይበል የሚያሰኝ ግንኙነት ነው ያለው፡፡ ይህም ማለት ሁኔታዎች ከመካረራቸው በፊት በንግግር የመፍታት ሰፊ ዕድል ይሰጣል።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በ2001 ዓ.ም አዲስ አበባን ሁለት ጊዜ ጎብኝተዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በቀጣዩ ዓመት፤ ማለትም በ2002 (እ.አ.አ) ካርቱምን ጎብኝተዋል።
ይህም በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት መልካም እንደነበረ አንድ ማሳያ ነበር፡፡ ይህ ግንኙነት አሁንም መልኩን አልቀየረም።
ቀረብ ባለው ዘመንም ቢሆን በሚያዚያ 2012 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ በሱዳን ጉብኝት አድርገው ነበር።
ባለፈው ግንቦት ወር ደግሞ የሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ ወደ አዲስ አበባ ልኡክ ይዘው ሄደው ነበር። በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ቡድን ለንግግር ተቀምጦ ነበር።
ይህ ውይይት በግንቦት 10/2012 ሲጠናቀቅ የድንበር ንግግሩ የወሰን ማካለሉን ጉዳይ ወደተሻለ ደረጃ ሊያደርስ፣ የአካባቢው ሕዝቦችን ዘላቂ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ደረጃ መድረሱን አቶ ደመቀ ጠቅሰው ነበር።
አርሶ አደሮች ያለስጋት ወደ ግብርናቸው እንዲመለሱ፣ ተገቢነት የሌላቸው እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ሁለቱ አገሮች መስማማታቸውም ያን ጊዜ ተገልጾ ነበር።
የአልፋሽቃ ማዕዘን
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በይገባኛል የምትወዛገብብት አካባቢ ረዥም የግዛት ድንበር ነው ያላት። ሁለቱም አገሮች ለም ነው የሚባለውን ፋሽቃ አካባቢን እጅጉኑ ይፈልጉታል።
ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ማዕዘን ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል።
በዚህ ድንበር ሁለቱም አቅጣጫ የሚገኙ ገበሬዎች ባሻገራቸው ያሉ ለም መሬቶች ላይ ያማትራሉ። አልፋሽቃ ማዕዘን በደቡብ ምሥራቅ ሱዳን ምሥራቃዊ ገዳሪፍ የሚገኝ ለም መሬት ነው።
አልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞችም በቅርብ ይገኛሉ።
የሱዳን ባለሥልጣናት አልፋሽቃ የሱዳን ግዛት ነው ይላሉ። አሁን በኢትዮጵያን እጅ ለምን ሆነ ሲባሉ፣ "የሱዳን መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ባለው የትብብርና የመግባባት ስምምነት መንፈስ ነው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ቦታውን አሁን እያለሙት ያሉት" ይላሉ።
ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር በድጋሚ ለማስመር፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።
ቀደም ካለው አስተዳደር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሬው ሕዝብ ሉአላዊ መሬቱን ቆርሶ እየሰጠ ነው በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ነው የቆየው።
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ቀን እንዲያሳውቁ መመርያ አስተላልፈውላቸው ነበር።
ሆኖም አወዛጋቢውን ድንበር መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ እስከዛሬም አልተሳካም፡፡
ይህ ዛሬ የሚጀመረው ንግግርስ ለውዝግቡ የመጨረሻ እልባት ይሰጣል ወይ? የሚለው በጊዜ ሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው።