ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳያቸውን በሰላም አንዲፈቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ

ከሰሞኑ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ግጭት ተነስቷል መባሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ሰጥቷል።

ሐሙስ ግንቦት 20/ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያና ሱዳንን በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ በተፈጠረው ክስተት ማዘኑንም የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በተፈጠረው ግጭት በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን በኩል ጉዳት ለደረሰባቸው ጥልቅ ሐዘኑን ገልጾ፤ ይህ ክስተት በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ያለው ጥብቅ ትስስር የማይወክል መሆኑን አመልክቷል።

ሚኒስቴሩ ጨምሮም በድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለመቆጣጠርና ተጨማሪ ውጥረትን ለማስወገድ ሁለቱ አገራት በክስተቱ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን በጋራ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

በአሁኑ ጊዜ ሁለቱ አገራትን ወደ ግጭት የሚያስገባ ተቀባይነት ያለው ምክንያት ስለሌለ በድንበር አካባቢ ያሉ ክልላዊ አስተዳደሮች በመተባበር የሠላምና የደኅንነት ሁኔታውን እንዲያረጋግጡ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

እንዲህ ያሉ ክስተቶችም በሁለቱ አገራት መካከል ባለው ወዳጃዊ ግንኙነት መሰረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሄ ማግኘት እንደሚገባቸው አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በካርቱም የሚገኘውን የኢትዮጵያ የኤምባሲ ተወካይን ጠርቶ ስለጉዳዩ ማብራሪያ በመጠየቅ ማነጋገሩም ተዘግቧል።

ባለፈው ሐሙስ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች አጋጠመ በተባለው በዚህ ክስተት ተገድለዋል ከተባሉት የሱዳን የጦር ኃላፊ ባሻገር ምንያህ ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የተገለጸ ነገር የለም።

ከዚህ ቀደም ሲል በድንበር አካባቢ ከሚከናወን የእርሻ ሥራ ጋር በተያያዘ በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች መካከል አለመግባባትና ግጭቶ ያጋጥሙ እንደነበር ይታወሳል።