ጁፒተር እና ሳተርን መንገድ ላይ ሊገናኙ ነው

ጁፒተር እና ሳተርን አንድ ላይ ገጥመው አንድ ፕላኔት መስለው እንደሚታዩ ሳይንቲስቶች ጠቁመዋል።

ይህ የጁፒተር እና ሳተርን ጥምረት የሚፈጥረው ብርሃን ዛሬ ምሽት ሊታይ እንደሚችልም ተነግሯል።

ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት ሰማይ ላይ እጅግ ደማቅ ብርሃን ታይቶ እንደነበር የሚናገሩት ሳይንቲስቶች ይህ ክስተት አሁን ሊፈጠር ይችላል ከተባለው ጋር ተመሳሳይነት ሳይኖረው አይቀርም ይላሉ።

ይህ ክስተት 'ዘ ስታር ኦፍ ቤቴልሄም' ወይም የቤቴልሄም ኮከብ ተብሎ ይጠራል።

ፕላኔቶቹ ከቀን ቀን እየተቀራረቡ መጥተው ዛሬ ምሽት ታኅሣሥ12/2013 ደማቅ ብርሃን ሊፈነጥቁ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

አውሮፓውያን አሁን ያሉበት የክረምት ወቅትና ደመና ተባብረው ይህን የብርሃን ትርዒት እንዳይከለክሏቸው ሰግተዋል።

"እውነት ለመናገር የአየር ሁኔታው አስተማማኝ አይደለም" ይላሉ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የአስትሮኖሚ ተቋም ምሁሯ ዶክተር ካሮሊን ክራውፎርድ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

ነገር ግን በደመና መካከል በተገኘ ቀዳዳ ሁለቱ ፕላኔቶች ገጥመው የሚፈጥሩት ብርሃን ሊታይ እንደሚችል ተነግሯል።

ይህ ዳግማይ የቤቴልሄም ኮከብ መመለስ ይሆን?

አንዳንድ የህዋ ጥናት ተመራማሪዎች 'አዎ' ሊሆን ይችላል ይላሉ።

የቨርጀኒያ ኮሌጅ የኃይማኖት አጥኚው ፕሮፌሰሩ ኤሪክ ቫንዴን ሁለቱ ፕላኔቶች የሚገጥሙበት ሰዓት ሰዎችን ለሴራ ትንታኔ አጋልጧል ይላሉ።

"ምናልባት ይህ ጊዜ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ካለው ክስተት ጋር ተመሳሳይነት አለው ወይ የሚለው አነጋጋሪ ሆኗል። ዮሴፍ፣ ማርያምና የክርስቶስ መወለድን የሚተርከው የመፅሐፍ ቅዱስ ክስተት የብርሃን መፈንጠቅን ያካተተ ነውና" ይላሉ ምሁሩ።

በ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀርመናዊው አስትሮኖመር 'ዘ ስታር ኦፍ ዎንደር' በማለት ጁፒተርና ሳተርን በጣም ተቀራርበው ያመነጩትን ብርሃን ገልፆት ነበር።

"ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት ሰዎች ሰማይ ላይ ምን እንየተከናወነ እንዳለው በደንብ ያውቁ ነበር" የሚሉት ደግሞ ዶ/ር ክራውፎርድ ናቸው። ስለዚህ የቤቴልሄም ኮከብ የመሆኑ ነገር አጠራጣሪ ነው ባይ ናቸው።

ይህ ክስተት በስንት ጊዜ ይከሰታል?

ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ አንድ መስመር ላይ ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም የአሁኑ ግን ለየት ይላል።

እኒህ ክስተቶች ለእይታ መልካም ናቸው፤ አልፎ አልፎ ይከሰታሉ። ነገር ግን ሁለት ፕላኔቶች ይህን ያክል ሲቀራረቡ ማየት እጅግ አስደናቂ ነው የሚሉት የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ቲም ኦብራያን ናቸው።

ሕዋ ላይ ሁለቱ ግዙፍ የሆኑት ፕላኔቶች ላለፉት 800 ዓመታት ሰማይ ላይ ይህን ያክል ተቀራርበው አያውቁም።

ሁለቱ ፕላኔቶች በጥምረት የሚፈነጥቁት ብርሃን መሸትሸት ሲል ሊታይ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።