ቱሪስቶችን ወደ ሕዋ ለሽርሽር የሚወስደው መንኮራኩር ሊሞከር ነው

ወደ ሕዋ የሚመጥቁ መንኮራኩሮች የሚያመርተው ቨርጅን ጋላክቲክ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቱሪስት ይዞ የሚጓዝ በሮኬት የሚወነጨፍ አውሮፕላን ሊሞክር ነው።

በእንግሊዛዊው የንግድ ሰው ሰር ሪቻርድ ብራንሰን የተቋቋመው ቨርጅን ጋላክቲክ በቀጣዩ ዓመት (እአአ 2021) ላይ ወደ ሕዋ ቱሪስቶችን መውሰድ እንደሚጀምርም ተገልጿል።

እስካሁን ከተመዘገቡት 600 ተጓዦች መካከል ጀስቲን ቢበር እና ሊዎናርዶ ዲካፕሪዮ ይጠቀሳሉ።

ለዚህም ወደ ሕዋ ቱሪስቶችን ማመላለስ ከመጀመሩ በፊት የሙከራ በረራው ይካሄዳል። ሁለት ተጨማሪ የሙከራ በረራዎች የሚደረጉም ሲሆን፤ በሦስተኛውና የመጨረሻው የሙከራ ደረጃ ሰር ሪቻርድ ብራንሰንም ይሳፈራሉ።

ላለፉት 16 ዓመታት ብዙ ሲባልለት የነበረው የሕዋ የቱሪስቶች ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ቨርጅን ጋላክቲክ ዝግጅቱን ለማጠናቀቅ እየሞከረ ነው።

የመጀመሪያው ሙከራ የሚካሄደው በሁለት አብራሪዎች ብቻ ነው። አብራሪዎቹ የቀድሞው የናሳ ጠፈርተኛ ሲጄ ስታርኮው እና የቨርጅን ጋላክቲክ ዋነኛ የሙከራ ፓይለት ዴቭ ማኬይ ናቸው።

በረራው የሚነሳው ከአሜሪካዋ ኒው ሜክሲኮ ነው። የአውሮፕላኑን ዝግጁነት አብራሪዎቹ የሚፈትሹም ይሆናል።

የድርጅቱ መሀንዲሶች ቴክኖሎጂውን አሁን ከሚገኝበት ለማድረስ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ሂደቱ በኮቪድ-19 ምክንያት ቢስተጓጎልም፤ ሠራተኞች ኒው ሜክሲኮ እና ካሊፎርንያ ውስጥ ሲሠሩ ነበር።

የዩናይትድ ኪንግደም የሕዋ ቡድን ፕሬዘዳንት ዊል ዋይትሆርን በረራው "ትልቅ እርምጃ ነው። አስተማማኝና ርካሽ ይሆናል። ሂደቱ ቀላል አልነበረም" ብለዋል።

እአአ በ2014 ላይ ከባድ አደጋ ተከስቶ የሕዋ ጉዞ ሂደቱ እንዲመረመር ተወስኖ ነበር።

ፕሬዘዳንቱ "የሕዋ ጉዞ እሽቅድድም አይደለም። ቅድሚያ የሚሰጠው ለደኅንት ነው" ብለዋል።

አውሮፕላኑ ጠፈርተኞችን ለማሰልጠንም ይውላል። ዋናን ጨምሮ በተለየ ከባቢ አየር ውስጥ መንቀሰቀስና ሌላም ስልጠና ይሰጣል።

"የሕዋ ቱሪዝም እና የሕዋ ሳይንስት ውስጥ ስልጠናው ጉልህ ቦታ አለው" ሲሉ ተናግረዋል።

ቨርጅን ጋላክቲክ በቅርቡ ቱሪስቶችን ወደ ሕዋ የሚወስድበትን ዲዛይን ይፋ አድርጓል። ይህም ከምድር ወደ ሕዋ ተወንጭፈው ወደ ምድር የሚመለሱበትን መቀመጫ ያካትታል።

ከእያንዳንዱ ተጓዥ ፊት ለፊት በሚገኝ ስክሪን ላይ በረራው በቀጥታ ይታያል።

ዲዛይኑ ላይ 12 መስኮቶች አሉ። ይህም እስካሁን ከተሠሩ የሕዋ መንኮራኩሮች የበለጠ ነው።

መስኮቶቹ ተጓዦች ሕዋን በደንብ እንዲመለከቱ ለማስቻል ነው የተሠሩት። በጉዞ ወቅት የመቀመጫቸውን ቀበቶ ፈትተው መንሳፈፍም ይችላሉ።

ስበት ስለማይኖር ተጓዦች ሲንሳፈፉ ራሳቸውን እንዲያዩ በሚል ትልቅ መስታወትም ተገጥሟል።