ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን ፡ ለዓመታት ከመንደራቸው ርቀው የቆዩት የዳርፉር ነዋሪዎች ተስፋና ስጋት
ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በጦርነት ከምትታመሰው የደቡብ ሱዳኗ ዳርፉር ግዛት መውጣት መጀመራቸውን ተከትሎ የንጹሃን ዜጎች ደኅንነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል እየገተገለጸ ነው።
የ14 ዓመቱ ታዳጊ አብዱላህ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች የሚኖሩበት መጠያ ካምፕ ውስጥ ነው ኑሮውን እየመራ የሚገኘው።
የተወለደው ከዳርፉር በስተሰሜን በኩል በሚገኘው አቡ ሾክ በተባለው መጠለያ ካምፕ ውስጥ ሲሆን ሙሉ ሕይወቱን ያሳለፈው እዚያው ነው። ቤተሰቦቹ ቤታችን እያሉ የሚጠሩትን መንደር በስም እንጂ አይቶት አያውቅም።
"ቤተሰቦቼ እና በርካታ ዘመድ አዝማዶቼ ተሰባስበው በደን በተከበበች አንዲት በጣም በምታምር መንደር ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ሰምቻለሁ" ይላል።
"ቤተሰቦቼ እንደነገሩኝ ከሆነ መንደሯ በጣም ሰላማዊና ለሕይወት ምቹ ነበረች። ሁሉም ነገር በመንደሪቱ ቀላል ነበር።"
አብዱላህ በሕይወቱ ቴሌቪዥን አይቶ የሚያውቀው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እነሱ በሚኖሩበት ካምፕ ደግሞ ትልቅ ስጋት አለ። ታጣቂ ቡድኖች ሌሊት ሌሊት ወደ አካባቢው በመምጣት ጥቃት ይፈጽማሉ።
"ሁሌም መደበቅ አለብን፤ ምንም ለማድረግ አንችልም። መልሰን ለማጥቃት ወይም ለመከላከል ከሞከርን ልንገደል እንችላለን" ይላል አብዱላህ።
በደቡብ ሱዳን ይደረስበታል ተባለው የሰላም ስምምነት ለ17 ዓመታት የዜጎችን ሕይወት ሲያመሳቅል የቆው ጦርነት እንዲያበቃና የአብዱላህ ቤተሰቦቹን የመሳሰሉ በርካቶች ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ ሊያደርግ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።
እስካሁን ድረስ ባለፉት 17 ዓመታት 300 ሺህ ሰዎች በዚሁ ጦርነት ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 2.5 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።
ይሄ ሁሉ ቀውስ የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2003 ላይ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች መንግሥት ዘንግቶናል በማለት አመጽ በማስነሳት የትጥቅ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
የተነሳውን ተቃውሞ ለመቆጣጠርም ካርቱም አርብቶ አደር አረቦችን በማስታጠቅ እርምጃ ወሰደች። እንዚህ የታጠቁ አርብቶ አደሮችም 'ጃንጃዊድ' በመባል የሚታወቁ ሲሆን የሱዳን መንግሥት ጠቀም ያለ ገንዘብ ይከፍላቸውም ነበር።
በርካታ አማጺያን ከመንግሥት ጋር የስምምነት ፊርማቸውን ቢያኖሩም እንደ አብዱላህ እና ቤተሰቦቹ ያሉ ቢያንስ 1.5 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች እስከ 60 በሚደርሱ መጠለያ ጣቢያዎች ተበታትነው ይገኛሉ።
የሱዳን ዳርፉር ግጭት
- ሚያዝያ 2003 ላይ የዳርፉር ግጭት ተጀመረ
- ሐምሌ 2007 የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ሰላም አስከባሪ በቦታው እንዲሰማራ ወሰነ
- መጋቢት 2009 ላይ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በዳርፉር የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በማለት የእስር ትዕዛዝ አወጣ
- ሚያዝያ 2019 የሱዳን ወታደሮች ፕሬዝዳንት አልበሽርን ከስልጣን አባረሩ
- የካቲት 2020 ላይ መንግሥት ፕሬዝዳንት አልበሽር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተስማማ
- ነሐሴ 2020 የሱዳን መንግሥት ከአምስት አማጺ ቡድኖች ጋር የሰላም ስምምነት ደረሰ
ላለፉት 17 ዓመታት መኖሪያቸውን በአቡ ሾክ መጠለያ ውስጥ ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዷ የሆነችው ዛራ ምንም ያህል ወደ ቀድሞ ቤቷ መመለስ ብትፈልግም ሁኔታዎች እስካሁን አልፈቀዱላትም።
"ወደ መሬታችን ሄደን እንኳን እርሻ መስራት አንችልም፤ ምክንያቱም በሌሎች ሰዎች ተይዟል። እነሱ ናቸው የሚደግሉን፣ እነሱ ናቸው ከመኖሪያችን የሚያፈናቅሉን። እኛ ግን አሁንም እዚህ መጠለያ ውስጥ እስካሁን አለን" ትላለች።
ከአቤ ሾክ መጠለያ ካምፕ በስድስት ሰዓት የመኪና ጉዞ ርቀት ላይ በምትገኘው ጂተሪ መንደር ያለው ሁኔታ ሰዎች አሁንም ድረስ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለምን እንደማይመለሱ ጥሩ ማሳያ መሆን ይችላል።
አብዛኛዎቹ በዚህ መንደር የሚገኙ ገበሬዎች ወደ ቀድሞ መሬታቸው ሄደው እርሻ ለመጀመር በጣም ነው የሚፈሩት፤ ምክንያቱም ይህን አስበው ወደቦታው የሄዱ ሰዎች ይገደላሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ።
ሌላው ቀርቶ በዚህች መንደር ውስጥ የፍርሀት ኑሮ እየመሩ እንኳን ደኅንነታቸው የተረጋገጠ አይደለም።
ጃንጃዊድ በመባል ሚታወቁት የታጠቁ ቡድኖች በዚች መንደር በቅርቡ መጥተው የካዲጃን ባለቤት እንዲሁም አንደኛውን ወንድ ልጃቸውን ተኩሰው ሲገድሉ እሷንም አቁስለዋታል።
"ሁሌም ቀውስ ነው፤ ሁሌም ግድያ ነው" ትላለች።
"መንግሥታችንን፣ ወታደሮችንም ሆነ ፖሊሶችን አናምናቸውም። ምንም አይነት እምነት የምንጥላባቸው አይደሉም። በፍጥነት መፍትሄ የማይፈለግ ከሆነ እዚህ ቦታ ላይ የዘር ማጥፋት ይፈጸማል።"
እነ ካድጃ የመንግሥት ወታደሮችን ለማመን ከሚቸገሩባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው በሠራዊቱ ውስጥ እነዚሁ የሚያውቃቸው የጃንጃዊድ አባላት መኖራቸው ነው።
በሰላም ስምምነቱ መሰረትም የሁሉም አማጺያን ወታደሮች ወደ መንግሥት ኃይሎች ተጠቃለው እንዲገቡ ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሌላ ነዋሪዎቹን ስጋት ላይ የጣለ አንድ ጉዳይ አለ። የሰላም ስምንቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከ13 ዓመታት በኋላ ለቀው መውጣት ጀምረዋል።
ምንም እንኳን ውጤታማነቱ እስከዚህም ነው ቢባልም ላለፉት ዓመታት በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሕብረት የሚመራው ሰላም አስከባሪ ኃይል ንጹሃን ዜጎችን ከመጠበቅና ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻር ቀላል የማይባል ሥራ አከናውኗል።
በሱዳን በቅርቡ የተቋቋመው ከፊል ወታደራዊ ጊዜያዊ መንግሥት ላይ ደግሞ በርካቶች ተስፋቸውን እንዲጥሉ አድርጓቸዋል።
ጊዜያዊ መንግሥቱ ወደ ስልጣን የመጣው በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣናቸው ከተባረሩ በኋላ ነው።
ከዚህ በኋላ ከዳርፉር ጋር በተያያዘ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ የሚቀርብባቸው በሙሉ ለፍርድ ይቀርባሉ። ማንም የሚቀር ሰው እንደማይኖርም እየተገለጸ ነው።
ፋይሳል ሞሀመድ ሳሊህ የሱዳን የባህልና መረጃ ሚኒስትር ናቸው። የቀድሞው የሰብአዊ መብት ተሟጋች በቀድሞው ሥርዓት ለእስር ተዳርገው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የሽግግር መንግሥቱ አካል ናቸው።
''በዳርፉር ማንኛውም አይነት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ለፍርድ ይቀርባሉ። ማንም ሰው አያመልጥም'' ብለዋል።
ነገር ግን በአቡ ሾክ መጠለያ ውስጥ የሚኙት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሰል እርምጃዎች ከዚህ በፊት ተጀምረው ሲጠናቀቁ ባለመመልከታቸው አብምዛም ተስፋ የሚጥሉበት እንዳልሆነ እየገለጹ ነው።
ምናልባት ከጦርነት፣ ረሃብና መፈናቀል ውጪ ምንም አይነት ነገር አይቶ ለማያውቀው የ14 ዓመቱ አብዱላህ ተስፋ ሰጪ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም አሁንም ቢሆን ግን ሕይወት በጣም ከባድነቱ አያጠራጥርም።
"ሁሌም በህልሜ ምንም ስጋት የሌለበት ቦታ ላይ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ማሳቸውን ሲንከባከቡ አያለሁ። ሰዎች በሰላም መኖር የሚችሉበትን ቦታ ሁሌም አስባለው፤ ነገር ግን ይህ ነገር ለማሰብ እንኳን የሚከብድ ነገር ነው'' ይላል አብዱላህ።