አል-በሽር ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው ሊሰጡ ነው

አል-በሽር ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው ሊሰጡ ነው።

ሱዳን የቀድሞውን ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፋ ልትሰጥ እንደሆነ ተነገረ።

ሱዳን አል-በሽርን አሳልፋ የምትሰጠው በቀረበባቸው የጦር ወንጀል ክሶች ነው።

የቀድሞ ፕሬዝደንት እአአ 2003 ላይ በዳርፉር ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጆሎችና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክሶች ቀርቦባቸዋል።

በሄግ የሚገኘው ዓለም የአቀፉ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት አቃቢ ሕጎች የቀድሞ ፕሬዝደንት የቀረበባቸውን ክሶች በሄግ ተገኝተው እንዲከላከሉ ሲጠይቁ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ በዳርፉር በነበረው ጦርነት በትንሹ የሞቱት ሰዎች 300,000 እንደሚኑ እና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም መፈናቀላቸውን አስታውቋል።

ከሁለት ወራት በፊት አል-በሽር በቀረቡባቸው የሙስና ወንጀሎ የሁለት ዓመት እስር ተበይኖባቸው ነበር።

የአል-በሽር አገዛዝ አልፋ እና ኦሜጋ በተመሳሳይ ወታደራዊ ድራማ መጠናቀቁ ይታወሳል። ዘመናቸው በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ተጀምሮ፤ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ፍፃሜውን በማግኘቱ።

ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ከስልጣን የተወገዱት አል-በሽር፤ በመፈንቅለ መንግሥት እአአ 1989 ላይ ነበር ወደ ስልጣን የወጡት።

የአል-ባሽር የፖለቲካ ሕይወት በጦርነት ዜማ የተቃኘ ነው።

አል-በሽር ሥልጣን ሲቆናጠጡ በደቡባዊ እና ሰሜናዊ ሱዳናውያን መካከል በተከሰተ የእርስ በርስ ጦርነት ሃገሪቱ ስትታመስ የነበረበት ወቅት ነበር።

ሱዳን በአል-በሽር አገዛዝ መባቻ ግድም የተረጋጋች ብትመስልም ግጭቱ እንደ አዲስ አገረሸ፤ አል-በሽርም ዳርፉር አካባቢ ከባድ የጦር ኃይል ተጠቅመዋል ተብለዋል ተወቀሱ።

ጫና የበረታባቸው አል-በሽር ግን በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2015 የተደረጉ ምርጫዎችን በማሸነፍ መንበራቸው ላይ ተደላደሉ።

በአይሲሲ የእሥር ማዘዣ የወጣባቸው አል-በሽር ከሃገራቸው ውጭ በተገኙበት የካቴና ሲሳይ እንዲሆኑ ቢወሰንባቸውም ወደ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አራቢያ እና ደቡብ አፍሪቃ ከመሄድ ግን ያገዳቸው አልተገኘም።

ወርሃ ሰኔ 2015 ላይ ግን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሳሉ ሊያዙ መሆናቸውን የሰሙት አል-ባሽር ሹልክ ብለው የወጡበት መንገድ ዓለምን ጉድ አሰኘ።