የጄፈሪ ኤፕስተን ተባባሪ በ28.5 ሚሊዮን ዶላር ዋስ እንድትወጣ ጠየቀች

ህፃናትን በወሲብ ንግድ በማሰማራት ክስ ተመስርቶበት የነበረው ጄፈሪ ኤፕስተን ጋር በወንጀል ተባብራለች የተባለችው ጊዝላኔ ማክስዌል በ28.5 ሚሊዮን ዶላር ዋስ እንድትወጣ ፍርድ ቤቱን ጠይቃለች።

በእስር ቤት ራሱን ላጠፋው ቱጃሩ አሜሪካዊ ታዳጊ ሴቶችን በማማለል ታመጣለት ነበር በሚልም ተወንጅላለች።

እንግሊዛዊቷ ጊዝላኔ ማክስዌል ከወንጀሉ ነፃ ነኝ በማለት እየተከራከረች ሲሆን የፍርድ ሂደቷም እስኪደርስ ድረስ በዋስ እንድትለቀቅ ጠይቃለች።

በቤት እስር እንድትቆይና ጠባቂዎችም የመውጣት የመግባት ሁኔታን በተጨማሪነት እንዲቆጣጠሩ ፍርድ ቤት ውሳኔ ይስጥ ብላለች።

የኒውዮርኩ ዳኛ አሊሰን ናታን የዋሱን ጥያቄ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውሳኔ ይሰጡበታል ተብሏል።

ለእስር በተዳረገችበት ሐምሌ ወር ወቅትም የዋስ መብቷ እንዲከበር ብትጠይቅም ፍርድ ቤቱ በወቅቱ ውድቅ አድርጎባታል።

ህፃናትን በወሲብ ንግድ በማሰማራት ክስ ፍርድ እየጠበቀ የነበረው ጀፈሪ ኤፕስተን ጋር የፍቅር ግንኙነትም ነበራት ጊዝላኔ ማክስዌል።

ጄፈሪ ኤፕስተን ለአስርት አመታት ያህል ህፃናትን በወሲብ ንግድ አሰማርቷልለ በሚል ክስ ቀርቦበት የፍርድ ውሳኔም ሳያገኝ ራሱን አወዛጋቢ በሆነ መልኩ አጥፍቷል ተብሏል።

በጊዝላኔም ከቀረቡባት ክሶች መካከል አራቱ ከ1994-1997 ድረስ እስከ አስራ አመት እድሜ ያላቸውን ሴት ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ እንዲሰማሩ ትመለምል ነበር የሚል ነው።

ሃምሌ ወር ላይ ሊታይ በታቀደው የክስ ሂደትም ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች 35 አመት እስር ይጠብቃታል።

ሰኞ እለት ለፍርድ ቤት የቀረበው ደብዳቤም ላይ ባለቤቷ ለዋስ የሚሆነውን ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተጠቅሷል።

የቀረበው አባሪ ደብዳቤም ላይ ከአራት አመት በፊት ጀምሮ እንደተጋቡ ቢጠቀስም የትዳር አጋሯ ስም ግን አልተጠቀሰም።

ጠበቆቿ በበኩላቸው ሶስት ቤቶቻቸውን ጨምሮ ለዋሱ በማስያዣነት እንደተካተቱ ጠቅሰዋል።

"ጊዝላኔ በኒውዮርክ ቆይታ ራሷን ከቀረቡባት ክሶች በሙሉ ነፃ ለማድረግም ትከራከራለች። የ58 አመቷ ጊዝላኔ በሚዲያዎች ላይ እንደተሳለችው መጥፎ ሰው አይደለችም" ይላል።

የጄፈሪ ኤፕስተን ክስ ምን ነበር?

ጄፈሪ ኤፕስተን አስራ ስምንት አመት ያልሞላቸውን ታዳጊ ልጃገረዶች እንደ ጎርጎጎሳውያኑ አቆጣጠር 2002-2005 በማንሃተንና ፍሎሪዳ በሚገኘው ቤቱ እየከፈለ በወሲብ ንግድ አሰማርቷቸዋል የሚል ነው።

በግል አውሮፕላኑ ኒውጀርሲ ሲያርፍ ባለፈው ወር በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰቡ ከአስራ አንድ አመት በፊትም አነጋጋሪ በተባለው ሚስጥራዊ ስምምነት ጥፋተኛ መሆኑንም አምኖ ክሱን ማስቀረት ችሏል ተብሏል።

ይህ ምስጢራዊ ስምምነት በቅርቡ አነጋጋሪ ሆኖ የነበረ ሲሆን ባለፈው ወርም በዚህ የተነሳ የቀድሞው ጠቅላይ አቃቤ ህግ አሌክስ አኮስታ በፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ለቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አቃቤ ህግጋት ጄፈሪ ኤፕስቴይን ጥቃቱ ለደረሰባቸው ሁለት ግለሰቦች ችሎት እንዳይቀርቡ ለማባበል ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በመክፈል ወንጅለዋቸዋል።

ጀፈሪ ኤፕሰትን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ 45 አመታት እስር ይጠብቀው ነበር።