በናይጄሪያውያን ልብ ዘንድ የነገሰው የቦክስ ሻምፒዮኑ አንቶኒ ጆሹዋ

አንቶኒ ጆሹዋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቅዳሜ ምሽት እንግሊዛዊው አንቶኒ ጆሹዋ ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቦክስ ግጥሚያውን ከቡልጋሪያው ኩብራት ፑሌቭ ጋር ያደርጋል።

በርካታ ነገሮችን ከስረ መሰረቱ በቀየረው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ይህንን ፍልሚያ በቅርብ ሆነው ማየት የሚችሉት አንድ ሺህ ሰዎች ብቻ ናቸው።

ፍልሚያው ዝም ብሎ አይደለም አንቶኒ የሶስት ጊዜ ከባድ ሚዛን ሻምፒዮንነቱን የሚያስጠበቅበትም ነው።

ኤስኤስኤ በተባለው ትልቅ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን ሚሊዮኖች አድናቂዎቹም በቴሌቪዥን፣ ሬድዮ ይከታተሉታልም ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም በናይጄሪያ የሚኖረው ድጋፍ ይህ ነው የሚባል አይሆንም።

የ31 አመቱ ቦክሰና ለእንግሊዝ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ቢያስገኝላትም በናይጄሪያ ያለው የጀግነነት ቦታ ለየት ያለ ነው። በተለይም የቤተሰቡ የትውልድ ስፍራ ነው በሚባለው የደቡብ ምዕራብ ግዛት ሳጋሙ ከአምልኮት ባልተናነሰ መልኩ ነው የሚታየው።

ጅማሮው

የአንቶኒ ወላጆች ብቻ ሳይሆን ቅድመ አያቶቹም በሳጋሙ ስመ ጥር ናቸው።

ቅድመ አያቱ ዳንኤል አደባነምቦ ጆሹዋ የመሬት ከበርቴና ኃብታም ነጋዴ ነበሩ። እምነታቸውን ወደ ክርስትና ከቀየሩም በኋላ የመጨረሻ ስማቸውን እንደቀየሩ ይታመናል።

ዳንኤል አንደኛውን ልጃቸው አይዛክ ኦላሴኑ ጆሹዋን ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ላኩት። እሱም ትምህርቱን ጨርሶ አየርላንዳዊ ሴት አግብቶ ወደ ናይጄሪያ ተመለሰ። ሰባት ልጆችም ወለዱ።

የነሱም አንደኛው ልጅ ሮበርት እዛው የሳጋሙ ተወላጅ የሆነችውን የታ ኦዱሳንያን አግብቶ ቦክሰኛውን አንቶኒና እህቱን ጃኔትን ወለዱ።

አንቶኒ ትውልዱም ሆነ እድገቱ እንግሊዝ ነው

ለአያቱ ትልቅ ክብር ያለው አንቶኒ አጠቃላይ ትውልዱም በግዛቲቷም ሆነ በናይጄሪያ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው።

ናይጄሪያ በልቡ ያለችው ቦክሰኛ

አንቶኒ ጆሹዋ በናይጄሪያዊ ቤተሰቦቹ ትልቅ ክብርና ኩራት አለው። በቀኝ ጀርባው በኩል የአፍሪካ ካርታ ያለበትና ናይጄሪያ ደምቃ የምትታይበት ንቅሳት አለው።

በፍልሚያዎቹም ላይ የናይጄሪያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደርጋል።

ወደ ፍልሚያ ሜዳውም ሲገባ በናይጄሪያ ሙዚቃ ታጅቦ ነው። በቅርቡ ከአንዲ ሩይዝ ጁኒየር ጋር በነበረው ግጥሚያም የታዋቂዎቹን በበርና ቦይና ፌሚ ኩቲን ሙዚቃ ታጅቦ ነበር የገባው።

ፌሚ ኩቲ የአፍሮ ቢት ፈጣሪው ፌላ ኩቲ ልጅ ነው።

ለናይጄሪያ ሙዚቃ ጥልቅ ፍቅር ያለው አንቶኒ በማህበራዊ ሚዲያዎችም ላይ አብሮ እየዘፈነ ያሉ ቪዲዮዎች ማሳያ ናቸው።

የናይጄሪያ ምግብ እያበሰለም በርካታ ቪዲዮዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ለቋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለተጠቁ ቤተሰቦቹም በርካታ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችም ወደ ናይጄሪያ ልኳል።

በቅርቡም ናይጄሪያውያን የፖሊስ የጭካኔ በትርን በቃን ብለው በመቃወም ሲነሱ አንቶኒም ድጋፉን በማሳየት ከአገሪቷም ሆነ ከህዝቡ ጋር ያለውን ፅኑ ቁርኝት አሳይቷል።

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪም አድናቂው ናቸው። ከፕሬዚዳንቱ ጋር በባለፈው አመት የተገናኙ ሲሆን አንቶኒም የሻምፒዮንነት ቀበቶዎቹን አሳይቷቸዋል።

ታዋቂው የናይጄሪያ ቦክሰኛ

ሰውነቱ በጡንቻ የተሞላው፣ ስርአት የተላበሰ፣ ቀስ ብሎ መናገር የሚወደው አንቶኒ የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ፈገግታም አለው።

በቦክሱ ዘርፍ ዘንድ ያስመዘገበው ድል በአገሪቱ የስፖርት ታሪክ ትልቅ ስም የተከለ አድርጎታል።

በአሜሪካው ቅርጫት ኳስ ዘንድ የኤንቢኤ ጨዋታ ታዋቂነትን ካተረፈው ሐኪም ኦላጁዎን ቀጥሎ ናይጄሪያዊ ዝርያ ያለው ትልቁ ስፖርተኛ ነው።

ከአንቶኒ በፊትም ቢሆን ናይጄሪያዊ ዝርያ ያላቸው የከባድ ሚዛን ቦክስ ሻምፒዮኖች ቢኖሩም የአንቶኒን ያህል ተወዳጅነት ያገኘ የለም።

ሄንሪ አክንዋንዴና ሳሙኤል ፒተር ሁለቱም የከባድ ሚዛን ቦክሽ የሻምፒዮንነት ስፍራ ቢቆናጠጡም ዝናቸውም ሆነ ተወዳጅነታቸው ከአንቶኒ ጋር አይወዳደርም። አንቶኒ በናይጄሪያውያን ልብ ዘንድ ነግሷል።

የአንቶኒ ጆሹዋ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Punch Newspaper Nigeria

በሳጋሙ የአንቶኒ አድናቂዎች ክለብ ከሶስት አመት በፊትም ተመስርቷል።

"አንቶኒ ሳጋሙን በአለም ላይ አሳውቋታል" በማለት የአንቶኒ ጆሹዋ ደጋፊዎች ክለብ መስራች አዚዝ አደኩንሌ ኦኩኖረን ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል።

"መጨረሻ ላይ ከአንዲ ሩይዝ ጋር ያደረገውን ግጥሚያ ህዝቡ ሁሉ እንዲከታተለው ለማድረግ በትልልቅ ስክሪኖችና በፕሮጀክተር አሳይተናል"

"በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቹም ፍልሚያውን ሊያዩ ወጥተው ነበር። አንዳንዶችም ፍልሚያውን ለመታደም ከአዋሳኝ ግዛቶች ተጉዘዋል" ይላል አዚዝ

"የመጪውንም ውድድር ታሳያላችሁ ወይ የሚል በርካታ ጥያቄዎችም እየጎረፉልን ነው" በማለትም አዚዝ ያስረዳል።

የሚዲያን ቀልብ የተቆጣጠረው ቦክሰኛ

በናይጄሪያ የሚገኙት ቴሌቪዥን፣ ድረ-ገፅ፣ ጋዜጣ፣ መፅሄት በአጠቃላይ የትኛውም አይነት ሚዲያ ስለ አንቶኒ አውርተው አይጠግቡም።

በወላጆቹ ትውልድ ቦታም ግጥሚያው በበለጠ ድምቀት ይኖረዋል በሚል ነዋሪው ብቻ ሳይሆን ሚዲያዎቹም ወደ አካባቢው አቅንተዋል።

ውድድሮቹን በቴሌቪዥን መከታተል ለማይችሉም ማህበራዊ ሚዲያዎችን አማራጭ አድርገዋል፤ ደማቅም ነው፤ በውይይትና አስተያየት የተሞላ ምልከታም ነው።

በባለፈው አመት ወደ ሳጋሙ መጥቶ የነበረው አንቶኒ የአካባቢውን ባህላዊ መሪና ኃላፊዎች ቢያገኝም የአድናቂዎቹን ክለብ ግን አላገኛቸውም። ሆኖም ለነ አዚዝ ይኼ ምንም ማለት አይደለም፤ መውደዳቸውም ትንሽም ቢሆን አይቀንስም።

"ምንም ማለት አይደለም። አሁንም ቢሆን ልጃችንና ተወካያችን ነው" ይላል አዚዝ

"አባቱ፣ አያቱ፣ ቅድመ አያቱና ዘሩ ከዚህ መሆኑን እናውቃለን። እናም መቼም ቢሆን እንደግፈዋለን። አንድ ቀንም እሱም እኛን ተመልክቶ ይደግፈን ይሆናል" ይላል አዚዝ

አክሎም "ለስኬቱ መፀለያችንን አናቆምም። ግን አሻራውን የሚያስታውስ እንደ ጂም፣መዝናኛ ማዕከል ወይም ሆስፒታል ቢገነባ እንወዳለን። በርካቶች ተመልክተው ሊያስታውሱት የሚችሉት ነገር ቢሆን ጥሩ ነው" በማለትም ያስረዳል።

የወጣቱ አርዓያ

አንቶኒ አሻራውን በወጣቶች ላይ እያሳረፈ ይገኛል፤ በተለይም በንግድ መዲናዋ ከተማ ሌጎስ።

ወጣት ናይጄሪያውያን አንቶኒ አስደናቂውንና ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ጉዞውን ያውቁታል። በእንግሊዝ ከበጥባጭነትና ረባሽ ወጣት መንገዱን ፈልጎ ወደ ሙያዊ እንዲሁም የሃብት ስኬት መድረሱ በርካቶችን የሚያነቃቃ ነው።

የሱን ፈለግም በመከተል በርካታ የአማተር ቦክስ ሜዳዎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው። የመንግሥትና የህዝብ ትምህርት ቤቶችም ከትምህርት በኋላና ቅዳሜና እሁድ የቦክስ ሜዳዎችም ሆነው እያገለገሉ ነው።

ምንም እንኳን የተሟላ ቁሳቁስም ሆነ ብቁ አሰልጣኝ ባይኖርም በርካቶች የሱን ፈለግ በመከተል ላይ ናቸው።

ሌካን ሙይቢ

የፎቶው ባለመብት, Lekan Muibi

ሌካን ሙይቢ ወይም በቅፅል ስሙ 'ሞተሩ' በተስፋ ከተሞሉ አማተር ቦክሰኞች አንዱ ነው።

የ21 አመቱ የመኪና መካኒክ ቅፅል ስሙንም ያገኘው በጥንካሬው፣ በስራው፣ በሚሰነዝነረው ጡጫም ነው።

ከሳጋሙ በ35 ኪሎሜትር ርቀት ሞዌ በምትባል አካባቢ ነዋሪ የሆነው ሌካን አንቶኒን እንደ ጀግናው ነው የሚያየው።

"ወደ ቦከስ ስፖርት ያስገባኝ ማይክ ታይሰን ነው። ነገር ግን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል ደግሞ ያሳየኝ አንቶኒ ነው ምክንያቱም እሱም እንደ እኔ ናይጄሪያዊ ነው" በማለትም ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግሯል።

የፌስቡክ ገፁንም በማየት የአንቶኒ ምን ያህል አድናቂም እንደሆነና ያለውንም ፅናት መረዳት ይቻላል።

የአንቶኒ ጆሹዋ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች እንዲሁም የሌሎች ስፖርተኞች የፌስቡክ ገፁን ሞልተውታል።

ሌካንም ቦክስ ሲለማመድ፣ እንዲሁም እዚህ ግባ በማይባሉ የመለማመጃ መሳሪያዎች የሚያደርገው ዬየቀን ትግልም ቪዲዮ ለስፖርቱ ያለውን ፍቅር ያሳያል።

የአንቶኒንም ቪዲዮ ለሰዓታት በዩቲዩብ በመከታተተል ችሎታውንም ለማሻሻል ጥረት ያደርጋል።

"ከሱ ብዙ እማራለሁ። ከፍተኛ የሆነ ጉልበት ቢኖረውም ኃይሉን ለመቆጠብ የሚጠቀመው ቴክኒክ አለው" ይላል።

አክሎም " ጡጫ በሚሰነዝርበት ወቅት በተጠና መልኩ ነው። ተፋላሚውንም በደንብ ባወቀ መልኩም ነው የሚሰነዝረው። ቀድሞም በደንብ ይረዳቸዋል" ይላል።

"ህልሜ ከሱ ጋር አንድ ቀን መሰልጠን እንዲሁም መፋለም እፈልጋለሁ። ከሱ ብዙ የምማረው አለ" በማለትም ይናገራል።

ሌካን ከአንቶኒ ጋር መሰልጠንም ሆነ መፋለም ህልሙ ቢሆንም ለአብዛኛው ናይጄሪያዊ አድናቂዎቹ አንቶኒ ፍልሚያውን ናይጄሪያ ቢያደርግ ትልቅ ነገር ነው።