የጣልያኑ እግር ኳስ ኮከብ ቀብር ወቅት ቤቱ ተዘረፈ

የፓውሎ ሮሲ ቀብር

የፎቶው ባለመብት, EPA

በፈረንጆቹ 1982 የዓለም ዋንጫን ያነሳው የጣልያን ብሔራዊ ቡድን አባል የነበረው ፓውሎ ሮሲ ቀብር እየተፈፀመ ባለበት ወቅት ሌቦች ቤቱ ገብተው ዘረፉት።

የጣልያን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ትላንት [ቅዳሜ] የእግር ኳስ ኮከቡ ቀብር እየተፈፀመ መሆኑን አጥንተው የመጡ ሌባዎች ናቸው ቤቱን የመዘበሩት።

ባፈለው ሐሙስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ጣልያናዊው ፓውሎ ሮሲ ቀብር በሰሜን ምስራቋ ቪሴንዛ ከተማ ተፈፅሟል።

አንሳ የተባለው የጣልያን ዜና ወኪል እንደዘገበው የሮሲ ባለቤት ፌዴሪካ ካፔሌቲ ከቀብር ስትመለስ ቤቷ ተበርብሮ ነው ያገኘችው።

ሌቦቹ ከዘረፉት ንብረት መካከል የፓውሎ ሮሲ እጅ ሰዓትና ጥሬ ገንዘብ ይገኝበታል።

ፖሊስ ጉዳዩን ምርምሬ ዘራፊዎች ማን እንደሆኑ እደርስበታለሁ ብሏል።

ሮሲና ቤተሰቡ ፖጊዮ ሲዜና በተባለች የፍሎረንስ ገጠር አውራጃ ውስጥ ነው የሚኖሩት። ሮሲ በመኖሪያ አካባቢው አንድ የግብርና ኩባንያ አለው።

ሮሲ በጣልያን እንደ ጀግና ነው የሚቆጠረው። ለዚህም ነው ሞቱ ብዙዎችን ያስደነገጠው።

የጣልያን እግር ኳስ ወርቃማ ዘመን አባል የነበረው ሮሲ ሃገሪቱ ካፈራቻቸው ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።

ለጣልያን ብሔራዊ ቡድን 48 ጊዜ ተሰልፎ 20 ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል።

በ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ፓውሎ ሮሲ 6 ጎሎችን በማስቆጠር ሃገሩ ጣልያን ዋንጫ እንድታነሳ አግዟል።

በክለብ ደረጃ ደግሞ ለቪሴንዛ እና ጁቬንቱስ ተጫውቷል። ሁለት ጊዜ የሴሪ አ ዋንጫ ማንሳትም ችሏል።

ቅዳሜ ዕለት የነበረውን ቀብር በርካቶች ታድመውበታል። በተለይ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ የቪሴንዛ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ቀብሩን ታድመዋል።

በ1982 ከሮሲ ጋር የዓለም ዋንጫን ያነሱ የቡድን አጋሮቹ የሮሲን አስከሬን ተሸክመው ወደ ሳንታ ማሪያ አኑሲያታ ካቴድራል ወስደዋል።

ከቡድን አጋሮቹ መካከል ማርኮ ታርዴሊ፣ ጂያንካሪዬ አንቶጎኖኒ፣ አንቶኒዮ ካብሪኒ እንዲሁም ፉልቪዬ ኮሎቫቲ ይገኙበታል።

"የቡድን አጋሬን ብቻ ሳይሆን ወንድሜን ነው ያጣሁት" ብሏል አንቶኒዮ ካብሪኒ።

ከቀብሩ በፊት የሮሲ አስከሬን ቪሴንዛ ውስጥ ስታዲዮ ሮሜዬ ሜንቲ በተሰኘው ስታድየም እንዲቀመጥ ተደርጎ ነበር።

የተጨዋቾቹ ደጋፊዎችና አድናቂዎች ወደ ስታደየሙ በማቅናት አበባ ሲያስቀምጡ ታይተዋል።

ቅዳሜ ዕለት በተካሄዱ የሴሪ አ ጨዋታዎች ላይ ተጫዋቾች ለሟቹ ሮሲ ክብር ጥቁር አርማ ክንዳቸው ላይ አስረው ታይተዋል።

ጨዋታዎቹ ከመጀመራቸው በፊትም የአንድ ደቂቃ የሕሊና ፀሎት ተካሂዶ ነበር። የሮሲ ፎቶ በስታድየሞቹ ግዙፍ ስክሪን ላይ ተሰቅሎም ታይቷል።