እስራኤል ፡ አረቡ ባለሃብት በእስራኤሉ ዘረኛ ክለብ ላይ ገንዘባቸውን ለማፍሰስ ለምን መረጡ?

የቤይታር ጀሩሳሌም ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቀናት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፅንፈኛ የሚባለው የእስራኤሉ ቤይታር ጄሩሳሌም እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች የቡድኑን ልምምድ በማቋረጥ ሜዳውን ወረሩት።

ደጋፊዎቹ በቁጣና በንዴት ሜዳውን የወረሩት ክለቡ ከሚወዳደርበት የእስራኤል ሊግ ወደታች ለመውረድ እየተንገታገተ በመሆኑ አይደለም።

ነገሩ ወዲህ ነው። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሆኑት ቱጃር በክለቡ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ነው ቁጣቸውን የገለፁት።

ክለቡም ከሁለት ቀናት በፊት ከሼክ ሃማድ ቢን ካሊፋ አል ናይን ጋር የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ላይ መድረሱን አስታውቆ ነበር።

የቤይታር ደጋፊዎች በፀረ-አረብ፣ ፀረ-ሙስሊም፣ እብሪተኛና ፀበኛ ባህርያቸው የታወቁና ስምም አትርፈዋል።

ከሰሞኑም ሜዳውን ብቻ መውረር ሳይሆን በቤይታር ስታዲየምም ላይ አፀያፊ የሚባሉ የግራፊቲ ምስሎችን በግድግዳዎች ላይ ስለዋል።

ምንም እንኳን የቤይታር ደጋፊዎች ምላሽ የከፋ ቢሆን በአንዳንድ አረብ አስተያየት ሰጭዎች ዘንድ ስምምነቱ ተቀባይነት አላገኘም።

አል ናህያና ሞሼ

የፎቶው ባለመብት, Beitar Jerusalem

በሬድዮ የስፖርት ፕሮግራም አቅራቢው ሳይድ ሃስን ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገረው ስምምነቱ "አሳፋሪ" ነው በማለት ነበር።

በተለይም የክለቡ ደጋፊዎች ፀረ-አረብ አቋም እንዳላቸው እየታወቀ ክለቡ ላይ ኢንቨስት መደረጉን ተችቷል።

በስምምነቱም መሰረት አል ናህያን በሚቀጥሉት አስር ዓመታት 92 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ሲሆን 50 በመቶም የክለቡ የባለቤትነት ድርሻ ይኖራቸዋል።

ክለቡ በአሁኑ ወቅት በሊጉ ባለው ደረጃ ከአስራ አራት ቡድኖች መካከል አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የእስራኤል መንግሥትና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ በመስከረም ላይ ፊርማ ማኖራቸውን ተከትሎ እንዲህ አይነት የንግድ ስምምነቶች በሁለቱ አገራት መካከል እየጎረፉ ነው ተብሏል።

ባለ መጥፎ ስሙ ክለብ

የአሁኑ በሁለቱ አገራት መካከል የተከናወነ ቁልፍ ስምምነት ባያደርገውም የቤይታር ስምምነት በከፍተኛ ሁኔታ አወዛጋቢ ነው።

በእስራኤል ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ በተለያዩ ክለቦች የይሁዲና አረብ ተጫዋቾች በአንድ ላይ ቢኖሩም ቤይታር አንድም አረብ ተጫዋች በታሪኩ አስፈርሞ አያውቅም።

ሆኖም በክለቡ ታዳጊ ቡድን ውስጥ አረቦች አሉ። በጎሮጎሳውያኑ 2013 ክለቡ ሁለት ሙስሊም ተጫዋቾችን ከቺቺንያ ማስፈረሙን ተከትሎ የቤይታር ቢሮ በደጋፊዎቹ ተቃጥሏል።

የተቃጠለው የቤይታር ቢሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክለቡ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎችም ላይ "ሞት ለአረቦች" የሚሉ መፈክሮችና ዝማሬዎች እንዲሁም አፀያፊ የሚባሉ ፅሁፎችን ከደጋፊዎቹ በኩል መሰስማትና ማየት የተለመደ ነው። የክለቡ ባለቤት ይህንን ባህርይ ለመቀየር ቢሞክሩም ብዙ ፍሬ አላፈራም ተብሏል።

አዲስ ባለቤት፣ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉ ሚሊዮነር የሆኑት ሞሼ ሆጌግ የተባሉት ግለሰብ ከሁለት ዓመት በፊት ክለቡን ገዙት። ሞሼ የተወለዱት እስራኤል ቢሆንም አባታቸው ቱኒዝያዊ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ የሞሮኮም ዝርያ አላቸው ተብሏል።

ከዓመት በፊት የክለቡ ባለቤት ሞሼ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዘረኛ የሆኑ ጉዳዮችን እንደማይታገሱና ዘረኛ በሆኑ ደጋፊዎችም ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

"የማንንም ህይወት ማበላሸት እየሞከርኩ አይደለም። የአባታቸውና እናታቸውንም ሚና እየወሰድኩ አይደለም። ለማስተማርም እየሞከርኩ አይደለም ያ የኔ ሥራ አይደለም" ብለዋል ሞሼ።

አክለውም "ነገር ግን ያን ባህርይ ወደ ስታዲየም ሲያመጡት በተሰበሰበውም ሕዝብ ላይ ሆነ በአገራችን ላይ መጥፎ ነፀብራቅ ነው። ያንን ደግሞ አልቀበለውም" ብለዋል።

ሞሼም ቢሆኑ "ነጥብ ለማስቆጠር" በሚል አረብ ተጫዋች እንደማያስፈርሙ ቢናገሩም፤ ለስፖርታዊ ምክንያቶች ሲሉ ግን ለማስፈረም ወደኋላ እንደማይሉና ፍራቻም እንደሌላቸው አሳውቀዋል።

"የተጫዋች እምነቱ፣ ቀለሙ ምንም ይሁን ግድ አይሰጠኝም። ቡድኑን መርዳት ይችላል ወይ? ጥሩ ተጫዋች ነው የሚለው ጉዳይ ነው የሚያሳስበኝ" ብለዋል።

ሞሼ ሆጌግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"የአረቦቹ ተጫዋቾች ይፈርሙም አይፈርሙም እስራኤላዊ የሆጉ ጎበዝ አረብ ተጫዋቾች አሉ። አንደኛውን ልናስፈርም እንችላለን" ብለዋል ሞሼ።

በተለይም ከአረቡ ቱጃር አልናህያን ጋር የተረደገውን ስምምነት ሞሼ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለውታል።

"በአንድ ላይ ሆነን ክለቡን በአዲስ መልክ በመተባበር፣ ስኬትና ወንድማማችነት በተሞላበት መልኩ እናድሰዋለን" በማለትም ተናግረዋል።

ንግድና ጓደኝነት

አልናህያን በቤይታር ኢንቨስት እንዲያደርጉ ዋነኛ ምክንያታቸውም ከሞሼ ጋር ያላቸው የዓመታት የንግድ ሽርክናውና ወዳጅነት እንደሆነ ተናግረዋል።

ስምምነቱ መፈረሙንም ተከትሎ አል ናህያ የክለቡ አጋር በመሆናቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

"ክለቡ እያከናወነው ስላለው ለውጥ ሰምቻለሁ። በዚህም ተሳታፊ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።

የእስራኤልና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ስምምነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁን ግለ ህይወት የፃፈው ጋዜጠኛው አንሸል ፊፈር በበኩሉ የቤይታር ደጋፊዎች ከእስራኤል ገዢ ፓርቲ ሊኩዊድ ጋር ፅኑ ቁርኝት እንዳላቸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁም በጨዋታዎች ወቅት ከፅንፈኞቹ ደጋፊዎች ጋር አንድ ላይ ፎቶም ተነስተዋል።

"አል ናህያ በቤይታር ጄሩሳሌም ኢንቨስት ለማድረግ መወሰናወች ምንም ተቃርኖ የለውም። ቤተሰባቸው በአጠቃላይ ከእስራኤል መሪዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ቁልፍ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል" በማለትም ጋዜጠኛው ይናገራል።

ይሄ ብቻ አይደለም አል ናህያ ከሁለት ቀናት በፊት በተድበሰበሰ መልኩ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና እንደሆነች የሚጠቁም ንግግር አድርገዋል።

ለአስርት ዓመታት በዘለቀው የእስራኤልና ፍልስጥኤም ግጭትና የእየሩሳሌም ሁኔታ ዋነኛና አወዛጋቢ ጉዳያቸውም ነው።

እስራኤል መላው ኢየሩሳሌም ግዛቴና መዲናዬ ናት የምትል ሲሆን ይህ በአሜሪካ ቢደገፍም በርካታ አገራት ይቃወሙታል።

ፍልስጥኤማውያን በበኩላቸው እስራኤል በጎሮጎሳውያኑ 1967 በተካሄደው ጦርነት በወረራ የያዘችውን ምሥራቅ እየሩሳሌም መጪዋ መዲናችን ናት ይላሉ።

እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ግንኙነታቸውን ለማደስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ፍልስጥኤም መዲናዋን ምሥራቅ እየሩሳሌም ባደረገ መልኩ ግዛቷን የምትመሰርትበትን ሁኔታም እንደምታግዝ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አስታውቃለች።