የኳስ ሃሜት፡ 'ምባፔ ከፈረንሳይ ለመውጣት የቤተሰብ ፈቃድ ያስፈልገዋል'

ምባፔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እሁድ እንደመሆኑ የእግር ኳስ ዓለም ምን እያለ ነው የሚለውን እናስቃኛችሁ።

የፈረንሳዩ የ21 ዓመት እግር ኳሰኛ ኪሊያን ምባፔ በአንጋፋ የአውሮፓ ክለቦች እየተፈለገ ነው። ለፓሪስ ሰይንት ዠርሜይን የሚጫወተው ወጣቱ ምባፔ ግን ክለቡን ሊለቅ የሚችለው ከቤተሰብ ፈቃድ ካገኘ ነው ሲል ሰን የተሰኘው ጋዜጣ በእሁድ ዕትሙ አስነብቧል።

ዩቬንቱስ፡ ወደ ጣልያን ስናቀና አሮጊቶቹ ዩቬንቱሶች የማንቸስተር ዩናይትዱን አማካይ ፖል ፖግባ በሚቀጥለው ጥር በውል ለማስፈረም አቅደዋል ያለው ሚረር ነው።

ዩናይትድ ፖግባን ለዩቬንቱስ ሰጥቶ በምትኩ ብራዚላዊው የክንፍ ተጫዋች ዳግላስ ኮስታና ከባርሴሎና በውሰት ዩቬንቱስ የሚገኘው ሚራለም ፒያንቺን እንዲወሰድ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል ብሎ ያተመው ደግሞ ካልቺዮ መርካቶ ነው።

ዶርትመንድ፡ የቦሩሲያ ዶርትመንድ ቀንደኛ አጥቂ የሆነው የ20 ዓመቱ ኧርሊንግ አላንድ አባት አልፍ-ኢንግ ልጃቸው አሁን በዶርትመንድ ደስተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን ወደፊት ክለብ ሊቀይር ይችላል ይላሉ። አልፍ-ኢንግ ለእንግሊዙ ሊድስ ተከላካይ ሆነው ተጫውተዋል። ይህ ወሬ የተገኘው ከጣልያኑ ቱቶስፖርት ጋዜጣ ነው።

አርሴናል፡ የአርሴናሉ አሠልጣኝ ማይክል አርቴታ የ32 ዓመቱ ጀርመናዊ አማካይ ሜሱት ኦዚል የኮንትራት ውሉ ከመገባደዱ በፊት ለክለቡ ሊጫወት ይችላል ብሏል ያለው ስታር ነው። ኦዚል ከአርቴታ ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት ከቡድኑ መቀነሱ ይታወሳል። ኮንትራቱ ሳይጠናቀቅ ወደ ሌላ ክለብ ሊዘዋወር ይችላል የሚሉ ወሬዎች እየተሰሙ ነው።

ዎልቭስ፡ ዎልቨርሃምፕተን ዎንደረርስ የ23 ዓመቱን የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች ኦልክሳንደር በ19 ሚሊዮን ዩሮ ለማስፈረም የነበራቸው ተስፋ ጨልሟል። ነገር ግን በሚቀጥለው ጥር ሌላ ጥያቄ ያቀርባሉ ሲል ስታር ጋዜጣ በእሁድ ዕትሙ አስነብቧል።

ቶተንሃም፡ የቶተንሃም ሆትስፐርስ ሊቀ መንበር ዳኒኤል ሌቪ እንግሊዛዊው ዴሊ አሊ ክለቡን ለቆ እንዳይወጣ የ18 ወራት ገደብ ሊጥሉበት ነው ብሏል 90ሚን የተሰኘው የስፖርት ጋዜጣ። አሊ ከቶተንሃም ጋር ያለው ኮንትራት ከመጠናቀቁ በፊት ወደ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን ሊያመራ ይችላል የሚሉ ወሬዎች አሉ።

ዩናይትድ፡ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ሃል የኔዘርላንዱ አማካይ ቫን ደ ቢክ ዩናይትድን መቀላቀሉ ትክክለኛ ውሳኔ አልነበረም ብለዋል ያለው ደግሞ በደች ቋንቋ የሚታተመው ዚጎ ስፖርት ነው።

ቼልሲ፡ ሰማያዊዎቹ ግብ ጠባቂያቸው ኬፓ አሪዛባላጋን የሚገዛ አጥተዋል እየተባለ ነው። ወሬው የሰንደይ ኤክስፕረስ ነው። ቼልሲ ኬፓን ለመሸጥ ቢያቅዱም ገዥ አልተገኘም። ከኬፓ ሌላ የ29 ዓመቱ ስፔናዊ ማርኮስ አሎንሶን የሚፈልገው ክለብ ጠፍቷል ተብሏል። ኬፓ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ ውዱ በረኛ ቢሆንም ከቼልሲዎች ልብ ወጥቷል።

በሌሎች ወሬዎች ዌስትብሮም የኒውካስትሉን ድዋይት ጌይል ለመግዛት ዕቅድ ላይ መሆናቸው፤ አርሴናል ደግሞ ዊሊያም ሳሊባን ከገዛ ዓመት ሳይሆን ለሽያጭ ሊያቀርብ መሆኑ ተሰምቷል።

ሊቨርፑል ደግሞ ለገና በዓል ለወትሮው የሚደረገውን የምሳ ግብዣ ዘንድሮ በኮቪድ-19 ምክንያት እንደማይኖር ዩርገን ክሎፕ አሳውቀዋል።