ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡አሜሪካ ሶስት ሚሊዮን ዜጎቿን በሳምንት ለመከተብ አቅዳለች
አሜሪካ የፋይዘር/ባዮንቴክ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲውል ፍቃድ መስጠቷን ተከትሎ ከነገ ጀምሮ ክትባት እንደሚጀመር ተገልጿል።
የመጀመሪያው የተባለው ለ3 ሚሊዮን ዜጎቿ የሚሆን ክትባቶችም በመላው የአሜሪካ ግዛቶች እየተከፋፈለ እንደሆነ ስርጭቱን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የአሜሪካ ጦር ጀነራል ጉስታፍ ፔርና አስታውቀዋል።
የኮሮናቫይረስ በሽታን በመከላከል 95 በመቶ ድረስ አስተማማኝ መሆኑ የተገለፀው ክትባት ደህንነቱንም በተመለከተ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርም (ኤፍዲኤ) ማረጋገጫ ሰጥቷል።
በኮሮናቫይረስ ክፉኛ እየተጠቃችው ባለው አሜሪካ በትናንትናው ዕለት ብቻ 3 ሺህ 309 ዜጎቿን አጥታለች።
አኃዙን ሪፖርት ያደረገው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ድረገፅ የበለጠ እንደሚያስረዳው በአለም ላይ ከፍተኛ በቀን የተመዘገበ ሞትም አድርጎታል።
በአሜሪካ ከህዳር ወር ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ሞቶች እየጨመሩም እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የፋይዘር/ባዮንቴክ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለአስቸኳይ ጊዜ መጠቀም ፍቃድ እንዲያገኝ በከፍተኛ ሁኔታ በትራምፕ አስተዳደር ጫና የተደረገበት የምግብና መድኃኒት አስተዳደርም ውሳኔውን የወረርሽኙ "አዲስ ምዕራፍ" ብለውታል።
ይኸው ተመሳሳይ ክትባት በዩኬ መሰጠት የተጀመረ ሲሆን አሜሪካም ፍቃድ መስጠቷን ተከትሎ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ጀነራል ጉስታፍ ፔርና በቀጣዩ 24 ሰዓታት ወደተለያዩ ግዛቶች መላክ ይጀመራል ብለዋል።
"በመጪው ሰኞ በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ 145 ቦታዎች ክትባቱ እንደሚደርሳቸው ጠብቁ፣ በቀጣዩ ቀን ማክሰኞ በ425 ቦታዎች እንዲሁም የመጨረሻው በ66 ቦታዎች ረቡዕ ይከፋፈላል" በማለትም የመጀመሪያው ምዕራፍ ክትባት ፕሮግራም አስረድተዋል።
በዚህም የመጀመሪያው ምዕራፍ ሶስት ሚሊዮን አሜሪካውያንን ለመከተብ ዕቅድ ተይዟል። ጀነራል ጉስታፍ ለጋዜጠኞች አክለውም እንደተናገሩት የኮሮናቫይረስን ለመግታት የሚያስፈልገው መጠንም ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንደሚጓጓዝ "መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።
በመጀመሪያው ሳምንት ለሁሉም አሜሪካዊ ማዳረስ ባይቻልም " ሁሉም አሜሪካዊ ክትባቱን እስኪያገኝ አናንቀላፋም" በማለትም አክለዋል።
የፋይዘር ክትባት በዩኬ ፣ ካናዳ፣ባህሬንና ሳዑዲ አረቢያ ፈቃድ አግኝቷል። ልክ እንደነዚህ አገራት የአሜሪካ ባለስልጣናትም ቢሆን ለክትባቱ ቅድሚያ የሚሰጡት ለጤና ባለሙያዎችና በእንክክብካቤ ማዕከላትም ላሉ ነው ተብሏል።
ተጋላጭ ማህበረሰብ ከተባሉት ውጭ ያሉ አሜሪካውያን ክትባቱ ይደርሳቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው ጥር ወር ላይ ሳይሆን በአጠቃላይ በተትረፈረፈ መልኩም በሚያዝያ ወር አቅርቦት እንደሚኖርም ይጠበቃል።