ኮሮናቫይረስ ፡ የኮቪድ-19 ክትባት በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ አገኘ

የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር የፋይዘር/ባዮንቴክ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ አገልገሎት እንዲውል ፈቃድ ሰጠ።

ተቋሙ እንዳለው ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ መስጠቱ አስካሁን በአሜሪካ ውስጥ ከ295 ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገውን ወረርሽኝ በመከላከል በኩል "ታላቅ እርምጃ" እንደሆነ አመልክቷል።

በሽታውን በመከላከል በኩል አስከ 95 በመቶ ድረስ አስተማማኝ እንደሆነ የተነገረለት ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ መሆኑን የምግብና መድኃኒት አስተዳደር መስክሯል።

የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕም የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት "ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መስጠት ይጀመራል" ብለዋል።

"አገራችን በህክምናው ዘርፍ ታላቅ የሚባል እመርታን አስመዝግባለች" በማለት የተናገሩት ፕሬዝደንት ትራምፕ "በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ውጤታማና ደኅንነቱ የተጠበቀ ክትባት መስራት ችለናል" ብለዋል።

የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር አርብ ምሽት ለክትባቱ ፈቃድ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ ከፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር በኩል ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ እንዲሰጥ ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት ቆይቷል።

የድርጅቱ ዋና ኃላፊ ስቴፈን ሃህን "ሐሰት ነው" ቢሉም ክትባቱ በቶሎ ለአስቸኳይ ጊዜ ግልጋሎት እንዲውል እንዲያጸድቁት ወይም ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ በዋይት ሐውስ መጠየቃቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአሜሪካ ጤናና የሰብአዊ አገልግሎት ኃላፊ አሌክስ አዛር ትናንት እንዳሳወቁት፤ መጠነ ሰፊ የኮሮናቫይረስ ክትባት ፕሮግራም ሰኞ ወይም ማክሰኞ ለማስጀመር መስሪያ ቤታቸው ከፋይዘር ጋር ይሰራል ብለዋል።

ይህ የፋይዘር ክትባት አስካሁን ድረስ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በካናዳ፣ በባህሬንና በሳዑዲ አረቢያ ፈቃድ አግኝቷል።

በእነዚህ አገራት ውስጥ እንደታቀደው በአሜሪካም ክትባቱ በቀዳሚነት ለአዛውቶች፣ ለጤና ሠራተኞችና ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሚሰጥ ይሆናል።

ከታህሳስ ወር ጀምሮ በአሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰበብ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ካለፈው ወር ጀምሮ ጨምሯል።

ባለፈው ረቡዕ ብቻ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ሳቢያ እንደሞቱ የተነገረ ሲሆን፤ ይህ የኮሮናቫይረስ ሞት አሃዝ ከፍተኛነቱ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ከፍተኛው ተብሎ ተመዝግቧል።